የፖለቲካፓርቲዎች ውይይት፣ ክርክርና ድርድር የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጥለቅ እንዲሁም እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ሃሳብ እንዲወከል በማድረግ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑ አያከራክርም። ስለሆነም በዚህ ድርድር ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሁሉ አስቀድሞ የአገርንና የህዝብን ፍላጎታ ታሳቢ ማደረግ እንደሚገባቸው አያጠያይቅም። ለዚህ ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት መኖር ጤናማ መሆኑን ፓርቲዎቹ ሊገነዘቡ ይገባል። ጤናማ የማይሆነው ልዩነትን በሃይል ወይም በኹከት ለማሳካት መሞከር ነው። ከላይ ስለተመለከተው ፋይዳ ገዥውን ጨምሮ ወደ 22 የሚጠጉ ፓርቲዎች በድርድር ሂደት ላይ መሆናቸው ቢታወቅም ሁለት ፓርቲዎች አሁንም የሃገርን እና የህዝብን ፍላጎት አማካይ ካደረገ አስተሳሰብ መውጣታቸው ሊያነጋግረን ይገባል። ምክንያቱም ስለመውጣታቸው ያቀረቧቸውን ምክንያቶች መመዘን ከድርድሩ ውጤት ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝብ ማንነታቸውን አውቆ አሰላለፉን ለማሳመር ያስችለዋልና።
ስለሆነም ጉዳዩን ኢሕአዴግ ለአገር አቀፍ ፓርቲዎች ባደረገው የእንወያይ ግብዣ መሠረት ከጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረጉትን 7 ዙር ከፈጁ ውይይቶች ተነስተን ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄዱት ውይይት በመጠቅለል ፓርቲዎቹን መመዘን ተገቢ ይሆናል፡፡
የውይይቶቹ ጅማሬ ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች መወሰንን አጀንዳ ያደረገ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። በዚሁ መሰረት የሃገርን እና የህዝብን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ፓርቲዎች 12 ጉዳዮችን በመለየት ለስኬታማነቱ ገና ከጅምሩ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል። እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደር፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ናቸው፡፡
ተሳታፊ ፓርቲዎቹ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የውይይቱ፣ የክርክሩ ወይም የድርድሩ ዓላማዎች ላይ መስማማታቸውም ከሂደቱ ስለሚዛናችን ሊታወስ ይገባል፡፡ ይልቁንም በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ግና ከጅምሩ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው የሃገርን እና የህዝቡን ፍላጎት ታሳቢ ስለማድረጋቸው አረጋግጦ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን ለድርድር፣ ለክርክርና ለውይይት ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶችንና ደንቦችን ለመቅረፅ ሰባት ዙር ውይይት ያደረጉት ፓርቲዎቻችን እሰየው ብለን አመስግነናቸው ሳንጨርስ ውይይቱ በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይደረግና ማን ያደራድር በሚሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልዩነት ሌሎቹ ስለሃገርና ህዝብ ፍላጎቶች ሲያጠቡ በዋናነት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ማጥበብ ተስኗቸው ረግጠው ወጥተዋል፡፡
ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ላይ በስድስት ዙሮች ከተሳተፈ በኋላ፣ በሰባተኛው ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፣ ኢሕአዴግ ይህን የሐሳብ ልውውጥ ማዕቀፍ ያዘጋጀው በጫና ምክንያት ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ ሕዝብ ሞት ሳይፈራ እምቢኝ ብሎ ድምፁን ሊያሰማ የደፈረበት፣ በሚሊዮኖች ወጥቶ ያንን ተዓምር የሠራበትና መንግሥት ላይ ጫና የፈጠረበት ጊዜ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ገዥው ፓርቲ እንዲነጋገር ጫና የፈጠረው ይኼው ነው፡፡ እኛ ደግሞ ያንን ሆ ብሎ የወጣውን ሕዝብ ጥያቄ የምንወግን ነን፡፡ ከሕዝብ እየሰማን ተግባራዊ ለማድረግ የምንታገል ነን፤›› በማለት የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከላይ ከተመለከተው አላማ ጋር ተጻራሪ የሆነና ሁከትን የሚያበረታ አስተያየት መስጠታቸው ነው እንግዲህ መድረክን ከህዝብና የሃገር ፍላጎት አኳያ እናሄሰው ዘንዳ ያስገደደን ፡፡
ኢሕአዴግ ግን አስቀድሞ እና መድረክም በተሳተፈባቸው 6 መድረኮች ላይ የምንወያየውና የምንደራደረው የዚህን አገር ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ስለምናምን ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡ ይልቁንም መድረክ እራሱን ቆልሎ ለሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቅና በመንፈግ ለብቻዬ ልደራደር ማለቱ ጸረ ዴሞክራሲያዊ እና ያፈጠጠ አምባገነን መሆኑን እንጂ ከላይ በተመለከተው አግባብ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ህዝባዊነቱን አይደለም። ሃገሪቱ የመድረኩ ሊቀመንበር መድረኩ ስለመሸፈቱ ያቀረቡት የአጣብቂኝ ምክንያትም ውስጥ እንዳይደለች ህዝቡ ያውቃል፡፡ እውነታው እና የድርድሩን ወሳኝነት የሚያጠይቀው የመድበለ ፓርቲ ስረአቱ መጠናከር በሚገባው ደረጃ ያልተጠናከረ መሆኑ ነው፡፡
የመድረኩ የሽፍትነት ምክንያት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር የተረጋጋ አገርና የበለፀገ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ካለማመን የሚመነጭ ነው፡፡ ስለሆነም ገዥው ፓርቲ አሁን በአገራችን በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የፖለቲካ ትግል ለማድረግና እንወክላለን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል ጥቅሞችና መብቶች ለማስከበር፣ በአገሪቱም የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰፋ ከሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር በማድረግ ለእነሱ ትግል የማይመች ሁኔታን ለመፍታት ወደ ድርድሩ የገባ መሆኑን ለመገመት አይከብድም፡፡
አብዛኞቹ ፓርቲዎች በትክክለኛው መንገድ ለመሥራት ሲሞክሩ የራሳቸው የድጋፍ መሠረት ስላላቸውና የህዝብና የሀገርን ፍላጎት ስላስቀደሙ መሆኑንም መገመት አይከብድም፡፡ ምድረክና ሰማያዊን የመሰሉት ደግሞ ያለተጨባጭ መሥፈርት ሌሎችን ውድቅ ማድረጋቸው በየትኛውም መሥፈርት የማያሳምንና ጤነኛ ያልሆነ ዕርምጃ ከመሆንም አልፎ ለህዝብና ሃገር ያላቸውን ንቀት የሚያመላክት ነው፡፡ መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች እራሱን አግዝፎ ቢመለከት መብቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በሥርዓቱ ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎችን ብቸኛ ተወካይ አድርጎ ራሱን መቁጠሩ የነባራዊና የሞራል መሠረት የለውም፡፡
ማን ከማን ይደራደር የሚለው አጀንዳ መድረኩን ከጫወታ ውጪ አድርጎ ሲያበቃ የአደራዳሪ ማንነት ጉዳይ ደግሞ በተቀሩት ዘንዳ ሌላው የልዩነት ምንጭ የነበረ መሆኑም ይታወሳል፡፡ አደራዳሪ ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ኢሕአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች ግን ድርድሩን ተሳታፊ ፓርቲዎች በፈረቃ ሊያደርጉት እንደሚገባ አቋም ይዘው 7ኛውን ዙር ሊያጠናቅቁ ችለዋል፡፡ ይህንኑ የድርድሮቹ ወሳኝ ምእራፍ የሆነ አጀንዳ ይዞ ሚያዚያ 2 ላይ የተሰየመው ጉባኤና የጉባኤ ውጤት አስቀድሞ እራሱን በራሱ ስለበላው መድረክ የሚነግረን ቁምነገር አዝሏል። በሃያ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተካሄደ የነበረው የቅድመ ድርድር ስምንተኛው ዙር ውይይት ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተካሄደ ሲሆን ከስድስተኛውና ከሰባተኛው ዙር ውይይቶች ሲንከባለል የመጣው ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ድርድር ላይ አደራዳሪው ማን ይሁን የሚለው አጀንዳ ብዙ አወያይቶ ህዝብና ሃገርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መቋጫውን አግኝቷል።
በዚህ መድረክ ገዥው ፓርቲ እና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ በሚለው አማራጭ ሃሳብ ፈንታ፤ ድርድሩ በዙር በተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመራት አለበት የሚል አቋም ሲይዙ፤ “ስድስቱ” እየተባሉ የሚጠሩት (ሰማያዊ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ ኢራፓ እና አብአፓ) ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪዎች መኖር አለባቸው የሚል አቋም አራምደዋል።
እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚባለው አስተሳሰብ በእውቀት መለወጥ ይገባዋል። ስድስቱ ፓርቲዎች በዚህ አስተሳሰብ ለውጥ ያምናሉ። በዚህ በሃያ አንደኛ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን የቆየው የባሕላችን ውጤት ጎድቶናል። . . . የሰጥቶ መቀበልን መርህ መቀበል የግድ ነው። ከስሜት ነፃ ሆነን፣ ለሀገር እና ለወገን አስበን፣ ታሪክ በበጎ ጎን ሊያስታውሰን፣ ትውልድ ሊያመሰግነን በሚያስችል ደረጃ ድርድሩን እንድናካሂድና መልካም ደረጃ ላይ እንድረስ የሚለው አስተሳሰብ ከመኢአድ የተንጸባረቀ፤ ስለህዝብና ሃገር ፍላጎቶች በመድረኩ ጎልቶ የወጣና ስለአጀንዳችን ሊወሳ የሚገባው አቋም ነው። ስለህዝብና ሃገር ፍላጎቶች ከችግሩ ሳይሆን ከመፍትሄው ሁን ለሚለው የቻይናውያን አባባል መኢአድ ተገዢ መሆኑም ሊያስመሰግነው ይገባል።
በውይይቱ ላይ አማራጮች ይዞ የቀረበው ኢዴፓ ገለልተኛ አደራዳሪ ይኑር የሚለው አቋሙ የጸና መሆኑን ከማስታወቅ አልፎ ስለህዝብና ሃገር ፍላጎቶች በልዩነት እንዲሰፍርለትም ጉባኤውን ጠይቋል። ድርድሩ እየተካሄደ ያለው በሞዳሊቲው መሰረት በአስራ ሁለት አጀንዳዎች ነው። አንዱ የአደራዳሪዎችን የተመለከተ ነጥብ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ ስምምነት አልተደረሰም ተብሎ ድርድሩን አለመሳተፍ ወይም ማቋረጥ እንደኢዴፓ ተገቢ አለመሆኑን አስምሮ ድርድሩን ለመቀጠል አቋም እንደያዘ ያረጋገጠበት ቁርጠኝነት በተመሳሳይ ልክ እንደመኢአድ ሊያስመሰግነው የሚገባ ይሆናል።
እንዲህ እንዲህ እያለ የሰፉትን ልዩነቶች በማጥበብ ወደመጨረሻው ምእራፍ የደረሰው 8ኛው ዙር ውይይት የሁሉንም ሃሳብ ባማከለ መልኩ በኢሕአዴግ ሃሳብ ተጠቃሏል። ስድስቱ ፓርቲዎች በሕገደንባቸው መሰረት ተወያይተው ላቀረቡት ሃሰብ አክብሮት እንዳለው ያወሳው ኢህአዴግ፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ባሕል በዚህ መልኩ ነው ማደግ ያለበት ሲል አክሏል። በሁሉም ጉዳዮች ላንስማማ እንችላለን … በሒደት በምናደርገው ግን ለዴሞክራሲ መጎልበት የራሱ አስተዋፅዖ አለው በማለት የማጠቃለያ ሃሳቡን የቀጠለው ኢህአዴግ … አደራዳሪ ይኑር፣ አይኑር የሚለውን ተወያይተንበታል፤ ሆኖም ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው ድርድሩ ለመቀጠል የመጣው ሃሳብ በአዎንታዊ የሚወሰድ መሆኑንም አስምሮበታል።
አስቀድሞ በውይይቱ መጀመሪያ አካባቢ የልዩነቶች ምንጭ የነበሩት የትኞቹ ፓርቲዎች በድርድሩ ይሳተፉ የሚሉት ጉዳዮች ነበሩ። አንደኛው፣ የመሪ ተደራዳሪ ፓርቲ፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች ድርድሩን ይወክሉ እና ሃያ ሁለቱ ፓርቲዎች በድርድር ይሳተፉ የሚሉ ናቸው። መሪ ተደራዳሪ እና የተወሰኑ ፓርቲዎች ይወክሉ የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት አላገኘም። … በዙር የሚለውም አማራጭ መድረክ የሚመሩ ሰዎች ድርድሩን ከማመቻቸት ውጪ የተለየ ሚና ሊሰጣቸው አይችልም ። ሌላው ቢቀር የሚነሱ ሃሳቦች ላይ ፖለቲካዊ አስተያየት ማቅረብ አይችሉም። ሚናቸው ለተደራዳሪዎች እድል መስጠት ብቻ ነው የሚሆነው። ስለሆነም ኢህአዴግ ያቀረበው አማራጭ ውድቅ ሲሆን መውደቁንም መቀበሉ እና ለስድስቱ ፓርቲዎች አማራጭ (በድርድሩ በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈቃድ በተመረጡ ቋሚ አደራዳሪ ሰዎች ድርድሩ እንዲመራ ስምምነት የተደረሰበት ሃሳብ) ተገዢ መሆኑ ዴሞክራሲያዊነቱን ሲያጠይቅ እዚሁ ጋር ሳለም የመድረክን አምባገነንነት እና ከመፍትሄው ይልቅ በችግሮች የቆረበ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም መድረክን ተከትሎ እራሱን ያገለለው ሰማያዊም ወጣንበት ሲሉ ያቀረቡት ምክንያት ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ የሚወክሉት ሕዝብን ሳይሆን ራሳቸውን መሆኑ ተይቷል፡፡
በእርግጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በውይይት ወቅት ልዩነት መፈጠሩ አዲስ ነገር አይደለም፤ ይልቁንም የጤናማነት ምልክት ነው። ያም ሆኖ ግን በያንዳንዱ ጉዳይ ተቀራርቦ መነጋገር የሚቻልባቸው እድሎች እያሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ አሻፈረኝ ማለት ጸረ ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ሳይሆን የለየለት አምባገነንነት ነው። ከሌሎቹና ከላይ ከተመለከቱት ስምምነቶች መገንዘብ የሚቻለው በአካሄድ ጉዳዮች ላይ የሚኖር ልዩነት መሰረታዊ ችግር እንዳልሆነ ነው። ይልቁንም በፓርቲዎች መካከል ያለውን መሰረታዊ የመወያየት ፍላጎትን ያሳየን መሆኑን ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ድርድርና ክርክር ማካሄድ ሲባል ከድርጅት ጥቅም በላይ ለህዝብ ጥቅም ዋጋ መክፈልን የሚጠይቅ መሆኑን ነው። ከስምምነት ላይ የደረሱት ፓርቲዎች ያረጋገጡልን ከራሳቸው በላይ የህዝብና የሃገርን ፍላጎት ወደማስቀደም መሸጋገራቸውን ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ሰጥቶ መቀበልን እንደመርህ ሊይዙት መቁረጣቸውንም አረጋግጠውልናልና የሚገባቸውን እውቅና ልንቸራቸው፤ ጥረታቸውንም ልናግዛቸው ይገባል።