ሀገራችን በግብርና ላይ ተወስኖ የቆየውን ኢኮኖሚዋን ወደ ኢንዱስትሪ መርነት ለማሸጋገር ዘርፈ ብዙ ጥረት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ከ2003ዓ.ም ጀምሮ የኢፌዴሪ መንግስት የሀገሪቷን የኢኮኖሚ መሰረት፤ ከኋላ ቀር ግብርና በማላቀቅ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ መርነት ለማሸጋገር የሚያደርገውን ጥረት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚረዳ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን፤ ከ2003-2007 ድረስ በነበሩት አምስት የትግበራ ዓመታት ተፈፃሚ ለማድረግ ታቅዶ፤ አበረታች የሚባል ሀገር አቀፋዊ ርብርብ ሲደርግ መቆየቱ የሚታወስ ጉዳይ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተቀመጠለት የትግበራ ዘመን ለማሳካት ሲባል እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጥረቶች በተደረጉበት ወቅት የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በግብዓት በመውሰድ የተዘጋጀው ሁለተኛው የአምስት አመት ዕቅድ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ መግባቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ሁለተኛው ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (2008-2012) ተነድፎ ተግባራዊ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረት ላይ ከተሰማራን፤ እነሆ አንድ ዓመት ከመንፈቅ አስቆጥረናል፡፡ ይህም የ2008በጀት ዓመት እና እየተገባደደ ያለው የ2009 በጀት ዓመት ታሳቢ ያደረገ ነው ፡፡ በመሆኑም የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ አላማ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ለማሳካት የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስሉ ነበር? እስካሁን በተካሄደው ርብርብ በመጀመሪያው አምስት አመት የዕቅድ ዘመን ያጋጠሙ የልምድ ማጣት ችግሮችን አስተካክለን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችለንን የማስፈፀም ጥረት በማድረግ ላይ ስለመሆናችን የሚያመለክት ነው? የሚሉ ነጥቦች ለመመልከት ነው፡፡
ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ማሳያ ነጥቦችን በማንሳት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ተግባራት የሚያስቃኘን ዳሰሳ አቀርባለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ የተሻለ የመረጃ ግብአት ሊሆን የሚችለውም፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ባለፈው መጋቢት 8 ቀን 2009ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረብት ሪፖርትና ‹‹በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርት›› የሚል ርዕስ ያለው ሰነድ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በዚሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ባቀረቡት ፅሁፍ መሰረት፤ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የማስፈፀም መርሐ-ግብር በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ይሳካል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚህ የመንግስት አቋም እንደ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ከታመነባቸው ተጨባጭ ተግባራት መካከልም፤ የግንባታ ሂደቱ ለአንድም ቀን ተስተጓጉሎ እንደማያውቅ የሚነገርለትን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ጨምሮ፤ ሌሎችም የሀገሪቱን ህዝቦች መፃኢ ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተሻለ ፍጥነት እየተገነቡ የሚገኙበት እውነታ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሌላው በኩል፤ በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ተጀምረው የግንባታ ሂደታቸው በመቀጠል ላይ ከነበረው ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን መካከል የሚመደቡት፤ የግልገል ጊቤ ሶስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብንና የትንዳሆ የመስኖ እርሻ ልማት ፕሮጀክት የመሳሰሉት ተጠናቀው አገልግሎት ወደ መስጠት ተግባር እንዲገቡ የተደረገበት ጥረት ከዚሁ ከሁለተኛው ዙር የእድትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን ስኬቶቻችን ተርታ ሊመደብ እንደሚችል ተወስቷል፡፡ በአጠቃላይ ሀገራችን ለዘመናት የኋላ ቀር አመራረት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ግብርና ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን ኢኮኖሚዋን፤ ትርጉም ባለው መዋቅራዊ ለውጥ ወደ ኢንዱስትሪ መርነት ለማሸጋገር ስትል ቆርጣ የተነሳችበትን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በየአምስት ዓመቱ የሚሰላ የአፈፃፀም ወይም ደግሞ የአተገባበር ጊዜ ገደብ እያስቀመጠች ወደ ፊት መራመዷን እንደቀጠለች ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ከተያያዘችው መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ጉዞዋን ሊያስቆማት የሚችል ፈተና አይኖርም ብለን ተስፋ እንድናሳድር የሚያደርግ አቅም ያለው ሆኖ የሚሰማኝ የዘርፉ አመርቂ ስኬት ደግሞ፤ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ነው፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያትም፤ የደቡብ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው የሀዋሳ ከተማ ተገንብቶ ወደ ተግባር ከገባ ወራትን ያስቆጠረው ግዙፉ የኢንዱስትሪ መንደር፤ በይዘቱ ለሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር የሚተርፍ ተሞክሮ ሊቀስምበት የሚችል ስለመሆኑ ገና ከወዲሁ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ የሚደመጡ የአህጉሪቷ መሪዎች ተበራክተዋልና ነው፡፡
ለዚህም የላይቤሪያዋ ፕሬዘዳንት ሔለን ጆንሰን ሰርሊፍና እንዲሁም የሱዳኑ አቻቸው ሪል ማርሻል ኦማር ሐሰን አልሽር በቅርቡ ወደ ሀገራችን መጥተው የሀዋሳውን የኢንዱስትሪ መንደር ከጎበኙ በኋላ፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የፈጣን ልማት ጉዞ አርአያነት ያለው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የተከተለ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጋቸው ስለመሆኑ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን ከኋላ ቀር የግብርና ለመላቀቅና በምትኩም ወደ ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሀብታዊ መሰረት ለመሸጋገር ያለመ ዘርፈ ብዙ ጥረት በእጅጉ የሚፈታተኑት ተጨባጭ ተግዳሮቶች መኖራቸው ሊስተባበል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡
የመጀመሪያውም ሆነ የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ላይ የተነደፉት እጅጉን የሚያማልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂዎች ሁሉ ያለ አንዳች መጓተትና መንዛዛት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተግባራዊ ተደርገው ለመታዘብ በበቃን ነበር፡፡ እንዲያውም እንደኔ እምነት ከሆነስ የበለጠ ትኩረት ልንስጠው የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ፤ ከተሳካው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ይልቅ ከሚጠበቀው በላይ ሲጓተቱና ምናልባትም ከነአካቴው ‹‹የውሃ ሽታ›› ሆኖ የመቅረት ዕጣ ሲገጥማቸው ለሚስተዋሉ ነው ባይ ነኝ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሰሞነኛ ሪፖርት፤ በተለይም ኤሊኖ የተሰኘው የአየር ንብረት ቀውስ እያስከተለ ካለው አሉታዊ ተፅእኖ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰት ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ በሀገራችን የግብርና ምርት ዕድገት ላይ እየፈጠረ የሚገኘውን እክል፤ የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ችግሮች ከአጠቃላይ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የማድረግ ጥረታችን አኳያ፤ የሚኖራቸው ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከዚህ በተቃራኒ የሚስተዋሉ ሰው ሰራሽ ድክመቶችን በተቻለ መጠን በማስተካከል ተገቢ ትኩረት እንደሚጠበቅብን ሳልጠቁም አላልፍም ፡፡ ምክንያቱም ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር የሞት ሽረት በሚባል መልኩ ትግል ገጥማ የምትገኝ ሀገራችን፤ በተደጋጋሚ ሲከሰት የሚስተዋለውን የድርቅ አደጋ ማስቀረት የማትችለውን ያህል፤ ፈጣን የልማት ጉዞዋን ይበልጥ አጠናክራ ማስቀጠልና ድርቅ በመጣ ቁጥር ለምግብ እጥረት ችግር የሚጋለጡ ዜጎቿን ከረሀብ ቸነፈር መታደግ እንደማያቅታት ማረጋገጥ ችላለች፡፡
በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገው ዋና መሠረታዊ ነጥብ ቢኖር፤ በተለይም አሁን ሁለተኛ የትግበራ አመቱን በማገባደድ ላይ በሚገኘው የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን፤ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ታስቦ የተነደፉ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በታቀደላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲሳኩ የማድረግ ጉዳይ የተለየ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ነው፡፡ ካልሆነ ግን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን በታለመለት ስፋትና ጥልቀት ተግባራዊ የማድረጉን አስፈላጊነት እምብዛም የተገነዘቡት የማይመስሉ አንዳንድ አስፈፃሚ አካላት አጠቃላይ ሂደቱ እንዲጓተት በሚያደርግ የተለመደ ዋዛ ፈዛዛቸው ምክንያት እያሳደሩ የሚገኙት አሉታዊ ተፅዕኖ ባለበት ሁኔታ፤ ዕቅዱ በተሻለ መልኩ እናሳካለን ብሎ ማሰብ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡
ሀገራችን በየአምስት ዓመቱ የምትነድፋቸው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች በተቀመጠላቸው የትግበራ ዘመን ተፈፃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ አላስፈላጊ እንቅፋት በሚፈጥሩ አካላት ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ አለመውሰድ ማለት፤ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር የዕለት ጉርስ፤ የዓመት ልብስ፤ እየተቸገረ የመንግስትን እጅ ለመጠበቅ ሲገደድ ለሚስተዋለው አርሶና አርብቶ አደር ህዝባችን አለማሰብ ነው ቢባልም እውነታውን በተሻለ መልኩ ይገልጸዋል፡፡ ስለዚህ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ተግባራዊ እንዲደረጉ የተቀመጡትን የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ሁሉ፤ በታቀደላቸው የጊዜ ወቅትና እንዲሁም ደግሞ በተመደበላቸው የበጀት ወጪ ብቻ አሳክተው የሚያሳዩንን አስፈፃሚ አካላት ማግኘት እንሻለን፡፡ ለህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያዊነት ያን ማድረግ እምብዛም የሚያዳግት ጉዳይ እንደማይሆንም ደግሞ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ እቅድ መሳካት ‹‹ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም›› ነውና ሁላችንም የየድርሻችን በመውስድ እንዳለብን ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
መዓ ሰላማት!