ኢህአዴግ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ደረሱ

ጉዳዩ የተጀመረው፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነሀሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ በዚያ መግለጫው ላይ ይፋ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የገለፀበት ነጥብ አንዱ እንደነበር አይዘነጋምና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል ውይይት ለማድረግና እንዲሁም የምርጫ ሕጋችንን ለማሻሻልም ጭምር መታሰቡን የሚያወሳው መግለጫ ትኩረት ማስታወስ ይቻላል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ማስፈፀሚያ ፈቃድ ከምርጫ ቦርድ ወስዶው ሕጋዊ ዕውቅና ያገኙትን ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚያቀራርብ የውይይትና የድርድር መድረክ ስለመፍጠር አስፈላጊነት የሚናገሩ የመንግስት አካላት በየአጋጣሚው ስለጉዳዩ የሰጡትን ማብራሪያ ስናደምጥ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ፤ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባሳለፍነው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2009 ዓ.ም የስራ ዘመንን በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት መክፈቻ ንግግር ፤ የኢፌዴሪ መንግስት በሕጋዊ መንገድ መታገልን እንደአማራጭ ወስደው ከሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አስፈላጊውን  ውይይትና ድርድርም ጭምር ለማድረግ  ስለማቀዱ ገልፀው እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ይህን የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መሰረት በማድረግ ከጥቂት ወራት በፊት 21 ያህል የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኢህአዴግ የውይይት መድረክ ለማካሄድ ዓላማ ያለው የጋራ ጥረት ወደ ማድረግ እንቅስቃሴ ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለመደው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ አሉታዊ ገፅታ የሚመነጩ በሚመስሉ ጥቃቅን ሰበብ አስባቦችን ሳይቀር፤ እንደምክንያት እያቀረቡ ከመግባባት ይልቅ አለመግባባትን፤ ከመተማመን ይልቅ ስጋት፤ ለማባባስ የመሞከር አባዜ የተጠናወታቸው አንዳንድ ወገኖች፤ የፖርቲዎቹ የውይይትና የድርድር መድረክ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጀመር ያደረገ መጓተትን ፈጥረው መሰንበታቸው የሚካድ ጉዳይ አይሆንም፡፡

ከዚህ ምክንያት ኢህአዴግና 21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግንባር ተገናኝተው “የውይይቱ ወይም  የድርድሩ አጠቃላይ ሂደት ምን መምሰል ይኖርበታል?” በሚለው ቀዳሚ ጥያቄ ዙሪያ ሃሳብ መለዋወጥ ከጀመሩበት ቀን አንስተው እስከ ዛሬ ድረስ አለመግባባት የተስተዋለባቸውን ተደጋጋሚ ስብሰባዎች አድርገዋል፡፡ ሰሞኑን ለስምንተኛ ጊዜ ፓርቲዎቹ በተገናኙበት የስብሰባ መድረክ ላይ ለእስከዛሬው መጓተት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ እንደቆየ የሚነገርለትን “የውይይቱንና የድርድሩን ሂደት መምራት የሚገባው አካል ማን ይሁን?” ከሚል ጥያቄ ጋር የተያያዘ አለመግባባት ወደ ጋራ ግንዛቤ ስለመድረሳቸው  መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

እነዚሁ ሰሞነኛ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም፤ ህብረ ብሔራዊ ቁመናን መሰረት ባደረገ መልኩ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱት መ.ኢ.አ.ድ እና ሰማያዊ ፓርቲ፤ እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ የተባለው ስብስብ ከስምምነቱ ራሳቸውን ከማግለላቸው በስተቀር ቀሪዎቹ ግን አሁን በተባለው ነጥብ ተስማምተው ውይይቱን ለመጀመር መዘጋጀታቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል ላለመግባባቱ ምክንያት ሆኖ የቆየውን “የውይይት ወይም ደግሞ የድርድር መድረኩን በአወያይነት የሚመራው ገለልተኛ አካል ከኢትዮጵያ ውጭ የሚመጣ ካልሆነ በስተቀር አንሳተፍም” የሚል አቋም ይዘው እንደነበርና አሁን ላይ  ይህን የመከራከሪያ ሃሳባቸውን ቀይረው “የለም በጉዳዩ ውስጥ የውጭ እጅ እንዲገባበት መፍቀድ የለብንም” ወደሚለው የኢህአዴግ አቋም እንደተመለሱ ታውቋል፡፡

  በዚሁ መሠረት ከሁሉም  በውይይቱ አሊያም ደግሞ በድርድሩ ሂደት ለመሳተፍ ውሳኔ ላይ እንደደረሱ ከታመነባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥውንም ሆነ ተቃዋሚዎቹን) የአመራር አካላት መካከል የአወያይነቱን ኃላፊነት ቢወስዱ የሚጠበቀውን ያህል የጋራ ጠቀሜታ እንዲገኝ የሚያደርግ አወንታዊ ተፅእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚባሉ ሦስት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መርጠው ሊሰይሙ መስማማታቸውን  የየፓርቲዎቹ ተወካዮች አሳውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያም 21 የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች የተካተቱበት ስብስብ ቀደም ሲል “ውይይቱ ወይም ደግሞ ድርድሩ መመራት ያለበት ለጉዳዩ ገለልተኛ ተደርገው በሚወሰዱ የውጭ አገር ሰዎች ነው” የሚል መከራከሪያ አንስተው ሲያራምዱት የቆየውን አቋም ቀይረው፤ “ጉዳዩ የኛው የኢትዮጵያውያን  የውስጥ ጉዳይ እንጂ ሌሎችን የሚመለከት አይደለም” ወደሚል ቀና አስተሳሰብ የመጡበት ለውጥ “ጎሽ ይልመድባችሁ በርቱልን!” የሚሰኝ በጎ ጅምር  ሆኖ  አግኝቼዋለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አብዛኛዎቹ የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለወትሮው የሚታወቁበት የጋራ ባህሪ፤ ለኢትዮጵያና ለመላው ህዝቦቿ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኘውን መሰረታዊ ጉዳይ ከማስቀደም ይልቅ፤ ከተለመደ አጉል ድርቅናቸው በሚመነጭ ግትር አቋም ላይ ሙጭጭ! ማለትን እንደመልካም ባህል የቆጠሩት ያስመሰልባቸው ስለነበር ነው፡፡

ስለዚህ “በእውር ቤት አንድ አይን ያለው ሰው ማግኘት ብርቅ ነው” እንዲሉ አበው ኢትዮጵያውያን፤  ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝብና  ለዚች የጋራ ህልውናችን መሠረት አድርገን ለምንቆጥራት ሀገር ዘለቄታዊ ጥቅም የሚበጀውን ከማይበጀው በውል ለይቶ የመረዳት ፍላጎትን ከሚጠይቅ ቅንነት የሚመነጭ አቋም ላይ በመድረስ ረገድ አሁን ያሳዩትን በጎ ጅምር እናደንቅላቸው ዘንድ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡ ምንም እንኳን እርምጃቸው ያለቅጥ መዘግየቱ ባያከራክርም ፤ ምናልባትም ካረጀ ካፈጀው የፖለቲካ ባህላችን ለመላቀቅ የመሻት አዝማሚያ እየታየ ነው ብለን ተስፋ እንድናሳድር የሚጋብዝ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡

ሀገራችን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦችና  ለዓለማችን ጥቁሮች ጭምር የአርአያነት ፋና የወጋችበትን ታላቁን የዓድዋ ድል ገድል በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ላይ ተቀዳጀችበት ነው፡፡  በዚህ  የጀግኖች አያቶቻችን አንፀባራቂ ታሪክ በምንናገርበት አንደበታችን “ፀጉረ ልውጥ የውጭ ዜጋ መጥቶ በማይዳኝበት የውይይት መድረክ አንሳተፍም” ስንል መደመጣችን ለሰሚው ግራ ነው ፡፡ እውን ለባለተራው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ማስተማር ያለብን ለባዕዳን ልዕልና መስገድ ነውን? ወይስ እኛ  አገር ህዝቦች የኢኮኖሚያዊ ድህነት ስለባ ሆነን ብንቆይም እንኳን ከጥንታዊ ታሪካችን የወረስነውን የመንፈስ ኩራትና የማይገስስ ነፃነታችንን አሳልፈን ለመስጠት የማንፈቅድ ስለመሆናችን ነው?  የሚል ጥያቄ በውስጣችን እንዲያጭር የሚያደርግ አቋም መያዝ በእውነቱ ያስተዛዝባል፡፡

ለማንኛውም ግን፤ ዋናው ቁም ነገር ለምን ተሳሳቱ? የሚለው ጥያቄ ሳይሆን፤ ከስህተታቸው  ለመታረም ዝግጁ ናቸው ወይ? የሚለው ቁልፍ ነጥብ ላይ የጋራ መግባባትን መፍጠር መቻል ይመስለኛል፡፡ እንደኔ አስተያየት ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የውይይቱን ሂደት የሚታዘቡ የውጭ ኃይሎች በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ያቀረቡትን ጥያቄ ዘግይተውም ቢሆን ማንሳታቸው፤ የሰለጠነ የተቃውሞ አካሔድን አዝማሚያ የሚያመለክት ብስለት ተደርጎ መወሰድ ያለበት የአቋም ለውጥ እንጂ፤ ለኢህዴግ ፍላጎት የመሸነፍ ምልክት ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡

በሌላው ለሀገራችንና ለመላው ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት የሚበጀውን የሰላማዊ ትግል አቅጣጫ ለመከተል የመፈለግ አዝማሚያን ማሳየት የህብረተሰቡን የልብ ትርታ ከማዳመጥ የሚመነጭ ነው የሚል ድጋፍ ሊያስገኝላቸው ይችላል፡፡ ስለሆነም  እንዲህ ዓይነቱን ስልጡን አካሄድ  ፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደ ባህል ሊወስደው ይገባል እላለሁ፡፡ ነገር ግን የአሁኑን ስምምነት ተከትሎ እንደሚጀመር የሚጠበቀው የፓርቲዎቹ ውይይትና ድርድር የዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከለየለት ጽንፈኛ አቋም የሚመነጭ መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ ሰሚ ጆሮ እንዲያጣ የሚያደርግ የጋራ መፍትሔ የሚያስገኝልን ይሆን ዘንድ እመኛለሁ፡፡

 

መዓሰላማት!