ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ጥልቅ ውጤቶችና ተግዳሮቶች ስሜነህ

በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት ከሞላ ጎደል መፈፀማቸውን መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡ የተሃድሶ ንቅናቄው በአመራሩ፣ በአባሉ፣ በሲቪል ሰርቫንቱና በመላው ህዝብ ደረጃ መካሄዱም ይታወቃል።ለበርካታ ወራት በቆየው በዚህ ተሃድሶ  ሰፊና ተከታታይ የሆነ ውይይት መደረጉና  በመሰረታዊ አጀንዳዎቹ ላይ  የጋራ መግባባት መፈጠሩ ትልቁ  ውጤት ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ወኪል ሆኑት የትምክህትና ጠባብነት አመለካከትና ተግባራት ሀገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም አስገድደዋት እንደነበር ከተሃድሶ መድረኮቹ የግምገማ ውጤቶች መገንዘብ የተቻለ ሲሆን ለዚህ ተሃድሶ መነሻ በነበረው ሁከት የወደመው ንብረትና የሰው ህይወት የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው።

በአጠቃላይ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ባለፉት 15 የተሃድሶ ዓመታት በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ መስኮች የተመዘገቡ አንጸባራቂ ድሎች ላይ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ህዝብ  የትምክህትና ጠባብነት አመለካከቶችና ተግባራት የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ዋነኛ አደጋዎች በመሆናቸው ላይ  የጋራ መግባባት መፍጠሩም የጥልቅ ተሃድሶው ጥልቅ ውጤት ነው፡፡  

ሌላኛው የጥልቅ ተሃድሶው ጥልቀት ያለው ውጤት አስከፊውን ሁኔታ በመቀልበስ የተጀመረውን ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት መራራ ትግል፤ በከፈሉት ውድ መስዋዕትነት ጭቆናና አድሎአዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ በመገርሰስ አዲስ በመፈቃቀድ፣ በመከባበር፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተና  ከአድልዎ የጸዳ ፌዴራላዊ  ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት መስርተዋል፤ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በየአካባቢያቸው ተፈጥሮ ያደላቸውን ጸጋ፣ መሬት፣ ጉልበታቸውን እውቀታቸውን በማስተባበር በየአካበባቢያቸው በነጻ የመልማት እድል ተጎናጽፈዋል፤ ከዛም በላይ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወሱንበት የራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብትም ተጎናጽፈዋል፡፡

በጋራ ጉዳዮቻቸውም ላይ በፍትሃዊና በእኩልነት መርህ የሚወስኑባቸው ተቋማትን በገዛ ፈቃዳቸው መስርተዋል፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ስርዓቱ አድላአዊ እንደሆነ በማስመሰል በትምክህትና በጠባብ ኃይሎች ዘንድ  አንዱን የበላይ ሌላኛው የበታች በማስመሰል የሚቀርበው ፕሮፓጋንዳ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ በህዝቦች ትግል የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ስርዓቱን ለማጥቃት ያለመ መሆኑን በመገንዝብ በኃላ ቀር አመለካከቶቹና ተግባራቱ ምህረት የለሽ ትግል መደረግ የሚገባ መሆኑም ላይ የጋራ መግባባት መደረሱ የጥልቅ ተሃድሶው መሰረታዊ ውጤት ነው፡፡

የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ቁልፍ ስራ ነው። የወጣቶችን የስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተም ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ጥልቅ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ነባሩን የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በመሰረታዊነቱ እንዲመልስ ሆኖ ተዘጋጅቷል ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት  ወጣቶችን የማሰልጠን፣ የማደራጀት፣ ብድር የማመቻትና በተወሰኑ ቦታዎችም ወደ ስራ የማስገባት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡  

በጥልቅ ተሃድሶው ከተቀመጡት አቅጣጫዎች አንዱ ድርጅትና መንግስትን መልሶ ማደራጀት መሆኑ ይታወቃል፡፡በዚሁ አግባብም መልሶ የማደራጀቱ ተግባር ከላይ እስከ ታች ባሉ የድርጅትና የመንግስት መዋቅሮች የተከናወነ መሆኑም የሚታወቅና ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ጥልቅ ውጤት ነው። በአመራር ስምሪቱ ላይ ህዝቡ ቀጥተኛና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን ባረጋገጠ አኳሃን አመራሮችን ተችቷል። ያገለግሉኛል ለሚላቸውም ይሁንታውን ሰጥቷል። አያገለግሉኝም ለሚላቸው ደግሞ ይሁንታውን ነፍጓል። ይህ ደግሞ ህዝቡ የስልጣን ባለቤትነቱን ያረጋገጠበት መሆኑን ያመላከተ ነው።

የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር ለማድረግ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሰቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ አካላት ጋር ነጻ ሀሳብ እንዲሸራሸር ውይይቶችና ድርድሮች እንዲካሄዱ መደረጉም ሌላኛው የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ነው። በዚሁ መሰረት የመድብለ ፓርቲ ዴሞከራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶች ተጀምረው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ እስከአሁኑ በተደረጉ ውይይቶችም ለድርድሩ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር  ገንቢ ሚና እየተጨዋቱ ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን ከመልካም አስተዳደር፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በጥልቅ ተሃድሶው መድረኮች የተቀመጡ አቅጣጫዎች በአግባቡ በተግባር ላይ የዋሉ አይመስልም።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያስጠና የቆየውን የጥናት ውጤት ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳሮማሪያ ሆቴል ይፋ ባደረገበት ጊዜ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ ውስንነት እንዳለበት አረጋግጧል፡፡ ሕዝብ ይወክሉኛል፣ የእኔን ችግር፣ ሐሳብና አስተያየት እንደኔ ሆነው ለመንግሥት አካላት ያቀርቡልኛል፣ አስፈጻሚው እኔን ማገልገሉን ይከታተሉልኛል፣ ይቆጣጠሩልኛል የሚላቸው የሕዝብ ምክር ቤቶች የሕዝብ እንደራሴነታቸውን በትክክል ሲወጡ፣ የሕዝብ ተሳትፎን በሚያረጋግጥ ሁኔታ መሥራት ሲችሉና አስፈጻሚውን በሙሉ አቅሙና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መቆጣጠር ሲችሉ ሕዝብ በተወካዮቹ በኩል ተሳትፏል ማለት ይቻላል፤ ሲልም ሪፖርቱ የተሳትፎን መሟላት ቅድመ ሁኔታ ይገልጻል፡፡

የብዙኃንና የሙያ ማኅበራትም በጀርባቸው ያለውን በርካታ አባላቸውን ወክለው የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስና በመልካም አስተዳደር ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ በማሳደግ መንግሥትና ሕዝብን የማገናኘት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት፣ ሚዲያው ትክክለኛ የሆነውን ሚናውን መጫወት ሲችል እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ቁልፍ ሆነው ከወጡ የአመራር ችግሮች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ አንዱ ሲሆን፣ አሁን በአገሪቷ ውስጥ ያለው የሕዝብ ተሳትፎ ውስንነቶች እንዳሉበት ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በራሱ ከሚያመጣው ችግር በበለጠ ለሌሎች ችግሮች መንስዔ ከመሆን ባሻገር የዴሞክራሲ ባህል እንዳያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍንና ሕዝብ ባለው ሁኔታ እንዳይረካ በማድረግ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሻክር ያደርጋል በማለትም ይገልጻል፡፡

ስለሆነም ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር ተያይዞ በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ያሉትን ስራዎች ይበልጥ ማስፋትና ማጥለቅ ያስፈልጋል፡፡