“ታጋይ” የሚለው ቃል ለአንድ ዓይነት የትግል መስክ ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ብዙ ማብራሪያ የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ታጋይነት ማለት ሰዎች በተናጠልም ሆነ በቡድን አንድን ለብዙሃኑ ህብረተሰብ መብትና ጥቅም መረጋገጥ ሲባል የታቀደ ግብ ለማሳካት ባለመተልዕኮ ላይ ተሰልፈው ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚስተዋሉበት አግባብ ነው እንጂ፤ የግድ ነፍጥ አንስቶ ፋኖ መሰማራትን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡
ለዚህም ደግሞ በዓለማችን ታሪክ ውስጥ “የነፃነት ታጋይ” ወይም “የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ታይጋ” ወዘተ የሚል የክብር ስፍራ የሚሰጣቸው ግለሰቦችን እንደ አብነት ማስታወስ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር የምንሰለፍበት ዓላማ የሰው ልጆችን መፃኢ ተስፋ ለሚያለመልም በጎ ተግባር ተፈፃሚነት ሲባል የሚደረግ ጥረት መገለጫ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ እንጂ፤ የግድ “ፋኖ ተሰማራ”ን እየዘመርን ወደ የኢቢምባ ተራራ ማቅናት፤ አልያም ደግሞ ወደ ደደቢት ጫካ መውረድ ሳይጠበቅብን በያለንበት እንዳለን ታሪክ የማይዘነጋው ትግል ማካሔድ የማንችልበት ምክንያት አይኖርም ለማለት መፈለጌን ልብ በሉልኝ፡፡
ስለሆነም፤ ይህን መሰረተ ሃሳብ ሳንለቅ፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተጨባጭ እውነታ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ ሆኖ ስለሚሰማኝ እውነቱን የመናገር ድፍረት የተላበሱ ታጋይ የሚዲያ ሰዎችን ስለማፍራት የሚያወሳ ሀተታ አንስተን፤ አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦችን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እንግዲያውስ እኔን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሃሳብ ለመሰንዘር ስል ብዕር ከወረቀት እንዳናኝ ካደረጉኝ ወቅታዊ ምክንያቶች መካከል፤ በተለይም ሁለት ሰሞነኛ ተያያዥ አስተያየቶችን ስለማሰማሁበት አግባብ በማስታወስ ነው የምጀምረው፡፡ እናም አሁን በቀጥታ የማስበውም ወደ ቀዳሚው የፅሁፌ ማጣቀሻ ነጥብ ይሆናል፡፡
ስለዚህም፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘርአይ አስገዶም ከሰሞኑ በተለይ ለፋና ብሮድ ካስትንግ ኮርፖሬት የሰጡትን ሚዲያ ነክ አስተያየት ስለማድመጤ ልብ ትሉልኝ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡ ታዲያ እርሳቸው ለፋና ኤፍ. ኤም 98.1 ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኞች በሰጡት ሰሞነኛ አስተያየት ላይ “አብዛኛዎቹ የሀገራችን የሚዲያ ተቋማት ብሔራዊ የጋራ መግባባትን ለማስፈን የሚያስችል ስራ እየሰሩ አይደለም” የሚል ቅሬታ አዘል ሃሳባቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ ዘርአይ አስገዶም በዚያው አስተያየታቸው “እስካሁን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሕጋዊ ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ከገቡት የብሮድካስት ሚዲያ ተቋማት መካከል አንዳንዶቹም ጭራሽ ብሔራዊ መግባባትን ለማጥፋት ያለመ የሚመስል አፍራሽ ፕሮግራም እያዘጋጁ እንደሚያሰራጩ ነው የደረስንበት” ሲሉ ማከላቸውንም ሬዲዮ ጣቢያው ዘግቧል፡፡
እናም እኔ በግሌ ይህን የብሮድካስት ባለስልጣኑን ስሞታ ሳደምጥ “ዘገየ እንጂ ጉዳዩ ተገቢና እውነትነት ያለው ነው” የሚል ንግግር ለገዛ ራሴ ብቻ ማንሾካሾኬ አልቀረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ፤ በተለይም እዚህ መዲናችን ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፌደራላዊ ስርዓቱን በአመፅ ለመናድ ያለመ ድብቅ አጀንዳ የሚያራምዱ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችን እንደሚደግፉ አጉልቶ የሚያሳብቅባቸውን ፕሮፖጋንዳዊ ቅኝት በተከተለ መልኩ ለአንድ ወገን የአስተሳሰብ ጎራ ልሳን ወደመሆን ከገቡ ሰነባብተዋልና ነው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚና አሳሳቢም ጭምር እንዲሆን የሚያደርገው ደግሞ፤ የቀለም አብዮት ናፋቂዎቹ ፅንፈኛ የተቃውሞ ጎራ ፖለቲከኞች የሚታወቁበትን የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ የሚንፀባርቅ አመለካከትን ማጉላታቸው ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ ይሆነን ብለው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ አስፈላጊነት እንዲዘነጋ የሚደርግ ግልጽ ተፅእኖ በማሳደር ላይ ያሉትን “ተባባሪ አዘጋጅ” ተብየዎች፤ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን ላይ እንዳሻቸው ሲፈነጩ፤ አንድም እንኳን “ሀይ” ሊላቸው የደፈረ አካል አለመስተዋሉ ነው፡፡
ከዚህ የተነሳም፤ በተለይ የመዝናኛውን ክፍለ ጊዜ የአየር ሰዓት እየዘጉ በእነርሱ ቁጥጥር ስር አስገብተው ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል የእነርሱ አስተሳሰብ ሰለባ እንዲሆን የሚያደርግ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳድሩ መቆየታቸውን ለመረዳት ዕውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ እንግዲያውስ እኔም ይህን በመሳሰለ መልኩ በሚገለፅ የሚዲያ ተቋማት ያልተገባ ተግባር ምክንያት ሀገራችን የምትመራበትን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት በተራ የጎዳና ላይ ነውጥ መደርመስ ይቻላል ብለው የሚምኑ ወጣቶች ሲበራከቱ የሚስተዋሉበትን አግባብ አምርሮ ለመተቸት የሚደፍር ታጋይ ጋዜጠኛ ሊኖረን አለመቻሉ ሆድ ሆዴን ስለሚበላው ነው በፅሁፌ ርዕስ የተመለከተውን ጥያቄ ለማንሳት መገደዴ፡፡ስለሆነም ርዕስ ጉዳዩን አንስቼ የበኩሌን የመፍትሔ ሃሳብ ለመሰንዘር እንድሞክር ገፋፍተውኛል ካልኳችሁ ምክንያቶች ሁለተኛውን ላቅርብና ከዚያም ወደ የማጠቃለያው ነጥብ አመራለሁ፡፡ በዚህ መሠረትም፤ ኢህአዴግ መራሹ የትግል መስመር ለመላው የሀገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዕኩል መጠን የሚበጅ ተጨባጭ የስርዓት ለውጥ ያመጣ ስለመሆኑ በማያሻማ መልኩ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ከማውቃቸው፤ ጥቂት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ በቅርቡ ሲናገር የሰማሁትን እውነት አስታውሼ አካፍላችሁ ዘንድ ወድጃለሁ፡፡
እንደኔ ግንዛቤ ከሆነ፤ ጎጃም ተወልዶ ስለማደጉ የሚነገርለት አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ፤ ለሌሎች አርአያ መሆን የሚችል የመርህ ሰውና ያመነበትን ፖለቲካዊ አቋም ያለ አንዳች መሸማቀቅ የመግለጽ ድፍረት ያለው ጭምር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበርን ከሚመሩት የስራ አስፈፃሚ አባላት አንዱ በመሆኑ ምክንያት “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” የሚል ርዕስ ባለው የዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ ሳምንታዊ የውይይት ፕሮግራም ላይ እየተገኘ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡
ስለዚህ እኔም ጋዜጠኛ መሰረት አታላይን የመጣጥፌ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ ላነሳው መሠረተ ሃሣብ ማጠናከሪያ እንዲሆነኝ የመረጥኩት በዚህ ጎጠኝነት እንደ ሰደድ እሳት መዛመት በያዘበት አስተዛዛቢ ወቅት ላይ ሆነን፤ እንደርሱ ዓይነት ለአስተሳሰብ ወገንተኝነት በጽናት ሲቆሙ የሚስተዋሉ እውነተኛ ታጋይ ጋዜጠኞችን ማግኘት መቻል በራሱ ለምሳሌነት የሚበቃ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋልና ነው መሲን አንስተን ጥቂት እንል ዘንድ የወደድኩት፡፡ ስለሆነም ዕሁድ ሚያዚያ 1 2009 ዓ.ም ቀን አየር ላይ በዋለው “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” የተሰኘ የዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ ሳምንታዊ ፕሮግራም ከእርሱው አንደበት ከተደመጡ ጥቂት ተሃድሶ ተሃድሶ የሚሸቱ ነጥቦችን ለማስታወስ ያህል እጠቅሳለሁ…
“ይቅርታ አድርጊልኝና ሚሚ የኢህአዴግ ምክር ቤት ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ በቂ ሆኖ አላገኘሁትም እኔ በግሌ” ሲል በክብ ጠረጴዛው አብራው ከተሰየመችው ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሐቱ ጋር የነበረውን ቆይታ የጀመረው መሰረት አታላይ “ለምን ብትይኝ የሀገራችንን ችግሮች ትክክለኛ ገፅታ በደንብ ያሳየ ነው ከተባለለት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ይፋ ካደረገው ወቅታዊ የመረጃ ግኝት ላይ የተመለከቱትን የአስፈፃሚው አካል ችግሮች ጉዳይ ስራ አስፈፃሚው ደፍሮ አላነሳቸውምና ነው” በማለትም ትችቱን በምክንያት አስደግፎ አቅርቧል፡፡
“በኔ እምነት ጥልቅ ተሃድሶው ያመጣል ብለን የምንጠብቀውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ሆኖ ያገኘሁት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ግኝት ላይ የተብራራውን መረጃ ነው” ያለው ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ፤ ይህን አስተያየቱን ሲያጠቃልልም “ስለዚህ በተለይ አስፈፃሚው አካል የተቋሙን ጥናት አምኖ ሊቀበልና ለሀገሪቱ አንገብጋቢ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ በመፈለግ ረገድ አንደ ጠቃሚ የመረጃ ግብዓት ሊገለገሉበት ይጋባል” ካለ በኋላ “አለበለዚያ ግን ከጥገኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ሃይል ጋር የሞት የሽረት ትግል ገጥመን ቁርጡ ይለይልናል እንጂ፤ በምንም መልኩ ስርዓቱን ለአደጋ የሚያጋሚጥ አካሔድ ለማስቀጠል ከሚፈልጉ ቡድኖች ጋር የምንሰለፍበት ምክንያት አይኖርም!” የሚል ቁርጠኛ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡
ስለዚህ እኔ ራሴምብሆን ከመሰረት የተለየ አቋም እንደሌለኝ እየገለፅኩ፤ ይልቁንም ደግሞ “ይህ ስርዓት እኮ ለማመን የሚያዳግት ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነትን አስከፍሎ የመጣ እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት ዝም ብሎ በቀላሉ የተገኘ አይደለም” የሚለውን አስተያየቱን ከልቤ እንደምደግፈውና ሊሰመርበት የሚገባ ቁልፍ ነጥብ ነው ብዬ እንደማምንም በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም፤ የፌደራሊዝም ስርዓታችን ፈርጀ ብዙ ትሩፋቶች መገለጫ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሕገ መንግስታዊ መብቶች እንደተራ ነገር እየተሸራረፉ፤ ለእነርሱ የግል ጥቅም የሚውል የሙስና ተግባር ማስፈፀሚያ እንዲሆኑ ሲያደርጓቸው የሚስተዋሉ ኪራይ ሰብሳቢ የስራ ሃላፊዎች የሚያሳዩት ዋዛ ፈዛዛ፤ የትግሉ ሰማዕታት ለወደቁለት መሰረታዊ ዓላማ ቅንጣት ያህል ክብር እንደሌላቸው ያመለክታልና ነው፡፡
ስለዚህ፤ የፌደራል ስርዓቱ ምን ያህል ለሸክም እንኳን የሚከብድ ዘርፈ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት የመጣ ስለመሆኑ የተረዱ ያማይመስሉና እንዲሁም ደግሞ ለመረዳት የማይፈልጉም ጭምር አስፈፃሚዎችን አምርሮ ለመታገል የሚቻለው እንደመሰረት አታላይ ዓይነቶቹን በእምነታቸው ለመፅናት እንብዛም የማይቸገሩ ታጋይ ጋዜጠኞችን ለይቶ ማወቅና ከፊት ረድፍ እንዲሰለፉ ማድረግ ይጠበቅብናል ባይ ነኝ እኔ በግሌ፡፡ አለበለዚያ ግን፤ የወቅቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጦርነት መገለጫ፤ በሚዲያ ነክ አውደ ውጊያ የሚካሔደው የሃሳብ ለሃሳብ ፍልሚያ ሆኖ ሳለ፤ እውነቱን አፍረጥርጠው እያወጡ ለህዝብ የማሳወቅ ድፍረት ያላቸውን ታጋይ ጋዜጠኞች አለማፍራት ማለት የሁዋላ ሁዋላ “ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ!” የሚያሰኝ ድምር ውጤት ማስከተሉ እንደማይቀር ለመተንበይ የተለየ ዕውቀት አይጠይቅም፡፡ ምክንያቱም ከላይ በዚህ መጣጥፍ መግቢያ ግድም፤ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘርዓይ አስገዶም ሰሞነኛ አስተያየት የሚያረጋግጥልን እውነትም ይህንኑ ነውና ነው፡፡
ለማንኛውም ግን፤ ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ ዕሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም አየር ላይ በዋለው የዛሚ ሬዲዮ የ“ክብ ጠረጴዛ” ውይይት “ይቺ ሀገር የጀመረችውን የፀረ ድህነት ትግል በዋዛ ፈዛዛ እንዲቀለበስ የማድረግ አዝማሚያ ከሚያሳዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አመለካከትና ተግባር ከተጠናወታቸው ቡድኖች ጋር የሞት የሽረት ትግል ገጥመን ማንኛውንም ዓይነት ዋጋ እንከፍላለን እንጂ ስርዓቱን እንደተራ ነገር ለእነርሱ ጠባብ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሊያደርጉት የሚሹ ጥገኞችን በቸልታ አናልፋቸውም!” ሲል አጠናክሮ ያስቀመጠው ቁልፍ ነጥብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እኔ ራሴ እንደ አንድ የትግሉ ሰማዕታት ለወደቁለት ክቡር ዓላማ ተገቢ አክብሮት የሚሰጥ የዚች አገር ዜጋ፤ እንደመሰረት አታላይ ሁሉ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ ተራማጅ አስተሳሰብን ደግፈው በመቆም ለሚታወቁት ተጋይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያለኝን ልባዊ አድናቆት እየገለጽኩ፤ አቋማቸው አቋሜ ስለመሆኑም ጭምር በዚህ አጋጣሚ ሳላረጋግጥላቸው አላልፍም፡፡ በተረፈ ግን ወቅቱ ስለእውነት በፅናት እንድንቆም ግድ የሚል ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡
መዓሰላማት!