አንዳንድ ወገኖች ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከሌበራላዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር የመረረ ጠብ ያለው ይመስላቸዋል፡፡ እናም ከዚሁ ግርድፍ ግንዛቤያቸው በሚመነጭ ኢ- ምክንያታዊ ተቃውሞ፤ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር፤ የለየለት ግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ አድርገው ለመፈረጅ ሲቃጣቸው የሚስተዋሉ ወገኖችን ማየት የተለመደ ነገር ነው ማለት ይቻላል፡፡
እንደ እኔ አረዳድ ከሆነ ግን፤ በዚህ መልኩ የሚገለፀውን ትችት ሲሰነዝሩ የሚስተዋሉት የተቃውሞ ጎራ ፓለቲከኞች ፤እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው፤ አንድም ተጨባጩን ሁኔታ ሳይገነዘቡ ዝም ብለው ማውገዝን የመረጡ ናቸው፤ አልያም ደግሞ ስለ ትክክለኛው ጉዳይ የማወቅ ፍላጎቱም የላቸውም ብሎ ማጠቃለል ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ይህን የምልበት መሰረታዊ ምክንያትም፤ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የሚያራምደው የፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚ አጀንዳ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ አማራጭ ፕሮግራም ወስዶ እርሱን ተግባራዊ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ርእዮተ ዓለማዊ አተያይ ስላለው ብቻ ‹‹ግራ ዘመም ነው›› ብሎ መደምደም፤ ምንአልባትም የሀገራችንን የማይስተባበሉ ነባራዊ ጥሬ ሀቆች ፤ አምኖ ላለመቀበል ከመፈለግ የሚመነጭና ‹‹ዓይኔን ግንባር ያርገው›› እንደማለት ያህል የሚቆጠር እብለት እንጂ ማንም ሊያሳምን የሚችል አይደለምና ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን፤ የዛሬዋን ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ በመምራት ላይ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የሚታወቅበትን መሰረታዊ የአስተሳሰብ አቅጣጫ መነሻና መድረሻ በቅጡ ስለመረዳት ጉዳይ እውነቱን መነጋገር አለብን ከተባለ፤ ጥሬ ሀቁ አንዳንድ የተቃውሞ ጎራው ሀይሎች ጥቅል ድምዳሜያቸውን ተአማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሞክሩ የሚስተዋልበት አግባብ ውሃ አያነሳም ባይ ነኝ እኔ በግሌ ፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘላቂ የጋራ እጣ ፈንታቸው መቃናት ይበጃል ብለው ተስፋ ያሳደሩበትን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ ወደፊት የማስቀጠል ያለማስቀጠል ጉዳይ እንጂ አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ የሚመለከት አይደለም የሚል እምነት እንዳለኝ እየገለፅኩ፤ ለምን ይሄን እንደምልም በምክንያታዊ የመከራከሪያ ነጥብ አስደግፌ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
እንግዲያውስ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት አካሒዶት ለነበረው የተሀድሶ መድረክ መወያያ እንዲሆን ‹‹የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ከ400 ገጽ በላይ ያለው የፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ የቀረበበት መፅሀፍ ለዚህ ርዕሰ ጉዳያችን የተሻለ ማጣቀሻ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ ስለሆነም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለሀገር መንግስታዊ የፖለቲካ ሥልጣን ለማን እና ለምን አይነት ተልዕኮ ማስፈፀሚያነት አስፈላጊ ሆኖ እንደሚገኝ የገባኝን ያህል ለማስረዳት ልሞክር፡፡ ከዚህ አኳያ የጋራ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የራሴን የሃሳብ ተዋጽኦ ለመጨመር ከመሻት በመነጨ መንፈስ ለማዘጋጃት ሃተታየ የመረጃ ግብዓት እንዲሆነኝ የመረጥኩትም ተጠቃሹን መፅሀፍ ነው፡፡
ምክንያቱም ‹‹የዴሞክራሲ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ዓብይ ርዕስ በ1993ዓ/ም የመጀመሪያ ወራት ውስጥ ታትሞ የወጣውንና ለያኔው የግንባሩ አባል ድርጅቶች የተሃድሶ መድረክ መወያያ ሆኖ የቀረበውን የኢህአዴግ ፖለቲካዊ ድርሳን ያነበባችሁ ወገኖች ልትፈርዱኝ እንደምትችሉት፤ መንግስታዊ ስልጣን በኛ ሀገር ነባራዊ እውነታዎች ውስጥ እንዴት ባለፍትሀዊ ክፍፍል ለብሔሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መዳረስ እንደሚኖርበት መብራራቱን ነው እኔ የማስታውሰው፡፡ እናም ገዢው ፓርቲ በዚያ ለተሀድሶ መድረክ ውይይት በቀረበ የፅሁፍ ሰነድ ላይ እንደ ቁልፍ ሀገራዊ የጋራ መግባባትን የሚሻ ነጥብ አድርጎ ላነሳው የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ መብት በዕኩል መጠን ስለማረጋገጥ ጉዳይ የሚያትት መሰረተ ሃሳብ ማንፀሪያነት የተጠቀመባቸው ምክንያታዊ ማጣቀሻዎች በሙሉ፤ ለምን የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ርዕዮተ አለማዊ እሳቤ መከተል ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ሲገናዘብ ተራጭ ሆኖ እንደተገኘ የተተነተነበት አግባብ አሳማኝ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
በግልፅ አማርኛ ለመናገር፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት የታገሉላቸውን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መሰረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የተሻለው ቀና መንገድ የትኛው ነው? የሚል ጥያቄ አንስቶ በመመርመር የራሱን አጥጋቢ ምላሽ መፈለግ ይጠበቅበት ስለነበር ነው እንጂ ኢህአዴግ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ወደ መፈተሽ ይገባ ዘንድ የተገደደው፤ ሌላ የተለየ ምክንያት ኖሮት አይደለም፡፡ እናም የመጀመሪያው የመወያያ ነጥብ ሆኖ መቅረብ የነበረበት፤ “ለመሆኑ ሌበራል ዴሞክራሲ በመባል የሚታወቀውን የመንግስታዊ አስተዳደር ዘይቤ የሚከተሉት ሀገራት አሁን ወደደረሱበት ተመራጭ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ቁመና ከመሸጋገራቸው በፊት ማሟላት የነበረባቸው ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ አድርገው የወሰዱት ጉዳይ ምን ነበር?” በሚል ጥያቄ ዙሪያ የተሟላ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል መሰረተ ሃሳብ ላይ ያተኮረ እንደነበር፤ የተጠቀሰውን የኢህአዴግ መፅሐፍ ፈልጎ በማየት ማረጋገጥ አያዳግትም፡፡
ስለሆነም፤ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ህዝቦች የሰለጠነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መገለጫ አድርገው የሚወስዱትን የሌበራል ዴሞክራሲ መንግስታዊ አስተዳደር ዘይቤ ለመከተል መሟላት ይኖርባቸዋል ተብሎ ከሚታመንባቸው ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎቸ መካከል፤ በተለይም ትርጉም ያለው የኢንዱስትሪ መር ክፍለ ኢኮኖሚን የማስፈን ጉዳይ ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው መስፈርት ስለመሆኑ የጋራ ግንዛቤ እንደተወሰደበት ነው የሚታወቀው በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዘንድ፡፡
ይህን የሌበራላዊ ዴሞክራሲ የመንግስት አስተዳደር ዘይቤን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ፖሊሲ ለመከተል እንችል ዘንድ የግድ መሟላት ያለበት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ አጠቃላይ እውነታ አምጥተን ስናየውም ደግሞ፤ ጉዳዩን “ጋሪው ከፈረሱ መቅደም ይኖርበታል” ብሎ የማመን ያህል የማይታሰብ ሆኖ መገኘቱ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም እንኳንስ ትርጉም ባለው መልኩ የሚገለፅ ኢንዱስትሪ መር ክፍለ ኢኮኖሚ ልንገነባና በሬ ጠምዶ ማረስን ጭምር እንደ ስልጣኔ የሚቆጥር ብዙ ሚሊዮን አርብቶ አደር ህዝብ ለሚኖርባት ሀገራችን ጉዳዩ በቀላሉ የሚሞከር ሊሆን እንደማይችል ይታወቃልና ነው፡፡
እንግዲህ ኢህአዲግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል አብዮታዊ ዴሚክራሲን እንደተቀዳሚ ለኛ ሀገር ነባራዊ እውነታ የሚስማማ ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤ ሆኖ ያገኘውም ከላይ ለማመልከት በተሞከረው መሰረት መክሮ-ዘክሮበት ሲያበቃ እንጂ፣አንዳንድ ወገኖች ሊያሳምኑን እንደሚቃጣቸው “ግራ ዘመምነት የተጠናወተው ስለሆነ” አይደለም፡፡ስለዚህም እንደኔ እምነት፤ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ የትግል መስመር ከሚከተለው የሀገራችንን አጠቃላይ እውነታ መሰረት አድርጎ የተቀረፀ የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ አኳያ ሲታይ፤ፖለቲካዊ ስልጣን መጨበጥ የሚያስፈልግበት ዋነኛው ምክንያት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ እንብዛም አይከብድም፡፡
እንዴት ቢባል ደግሞ፤የትግሉ አልፋና ኦሜጋ፣መላው የሀገራችን ህዝቦች አበክረው የተስማሙበት ሕገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን ላይ በማያሻማ መልኩ የተቀመጠውን አንድ ጠንካራ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የጋራ ግብ ለማሳካት የሚያስችል አጠቃላይ የስር ነቀል ለውጥ ጉዞ እያካሔደች ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የመንግስት አካል ምን ዓይነት የአመራር ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት መካሪ የሚያሻው አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም ጉዳዩን ከዚህ በተሻለ ምክንያታዊ ማብራሪያ ግልፅ ማድረግ ቢያስፈልግ፤እንደሚከተለው ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለሀገር ውስጥ የግድ መታለፍ የሚኖርባቸው ፈተናዎች ተደርገው የሚወሰዱትን መሰረታዊ ችግሮቻችንን በሚመለከት፤በተለይም የፖለቲካዊ ስልጣን ክፍፍሉን አስፈላጊነት አምነው በሚቀበሉ የስር ነቀል ለውጡ ደጋፊዎች መካከል ትርጉም ያለው የጋራ መግባባትን የመፍጠር ጉዳይ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነጥብ እንደሆነ ደፍሮ መናገር ይቻላልና ነው፡፡
ይሄን ስል ደግሞ፤እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ የአንድ ሀገር ህብረተሰብ፤በተያያዝነው ስርነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ አማካኝነት ካለፈው ታሪካችን በወረስናቸው አሉታዊ የዕርስ በርስ ግንኙነቶች ምክንያት ተፈጥረው የቆዩ ችግሮችን እየፈታን በመካከላችን መስፈን ያለበትን ጤናማ የወንድማማችነት መንፈስ ለማስፈን ያለመ ፈርጀ ብዙ ጥረት ማድረግ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ፤ያስመዘገብናቸው በርካታ ጠቃሚ ውጤቶችን እንዲገኙ ያደረግንበት አጠቃላይ ሂደት እንደሚያመለክተው፤ልማትና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማረጋገጥ ተግባር በእርግጥም ሊነጣጠሉ የማይችሉ ናቸው ብሎ መደምደም ተገቢነት ይኖረዋል ማለታችን ነው፡፡
ስለሆነም፤የፌደራሊዝም ስርዓቱ ዓይነተኛ መገለጫ ተደርጎ በሚወስደው ያልተማከለ የመንግስት አስተዳደር መዋቅርን የተከተለ የፖለቲካዊ ስልጣን ክፍፍል ጉዳይም፤መታየት ያለበት የመላው የሀገራችን ህዝቦች አንገብጋቢ ጥያቄ ከሆነው ልማትና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማረጋገጥ ጉዳይ ጋር በጥብቅ ተቆራኝቶ ሊታይ የሚገባው እንጂ ሌላ መመዘኛ አያስፈልገውም የሚል ነው የኔ እምነት፡፡ምክንያቱም፤ እያንዳንዱ የመንግስት አካል የሚያደርገው ጥረት ሁሉ፤የፌደራላዊት፤ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን ሀገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ ባለመ መልኩ የተቃኘ መሆን እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ከተባለ፤ ፓለቲካዊ ስልጣን ለነማንና ለምን ተግባር ማስፈፀሚያ እንዲሆን ያስፈልጋል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አይከብድምና ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ሀገር ትኩረት ሰጥተን ማረጋገጥ የሚጠበቅብን ጉዳይ ሆኖ የሚሰማኝ፤ከፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን እርከን ጀምሮ፤እስከ የብሔራዊ ክልል መስተዳደሮችና እንዲሁም ደግሞ እስከ ታችኛው የወረዳና የቀበሌ አስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ በሚዘልቅ ተዋረድ የሚቀመጡ አስፈፃሚ አካላት የየራሳቸውን ሃላፊነት ተወጥተው ለመገኘት የሚያደርጉት ድምር ጥረት ወደ አንድ ሀገራዊ ግብ የሚወስደን ጉዞ ስለመሆኑ የምንናበብበት አግባብ ምን ያህል ነው? ከሚለው ጥያቄ አኳያ መነሳት ያለበት ነጥብ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
በሌላ አነጋገር፤አብዛኛው ህዝብ በሁዋላ ቀር የእርሻ ስራ ላይ የተመሰረተ ህይወት እየመራ በሚኖርባቸው ክልሎች ውስጥ ስልጣን መጨበጥ ያለበት እያንዳንዱ አካል አርሶ አደሩን ህብረተሰብ ከእጅ ወደ አፍ ሊባል በሚችል መልኩ ሲዳክር ከቆየበት ያረጀ ያፈጀ የግብርና ዘዴ አላቆ ወደ ሰለጠነና ዘመናዊ (ገበያ ተኮር) አመራረት ሊያሸጋግር የሚችል ብቁ አመራር መስጠት እንደሚጠበቅበት የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፡፡እንዲሁም አብዛኛው ህብረተሰብ የቤት እንስሳትን በማርባት ላይ የተመሰረተ ህይወት እንደሚመራ በሚታመንባቸው ክልሎችና ዞኖች ባለው የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሃላፊነቱን ቦታ የሚይዙት አካላትም፤ አርብቶ አደሩን ህዝብ በአንድ በተወሰነ አካባቢ የማስፈርና ወደ የግብርና ስራ ተሰማርቶ በምግብ እህል ራሱን የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠርለት የማድረግ ተግባርን እንዲከውኑ ሲባል ነው ስልጣን የሚሰጣቸው፡፡እናም የጨበጡት ስልጣን ባለቤት ለሆነው ህዝብ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ባደረጉ ቁጥር ልማትንና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትን በማፋጠን ረገድ ታሪክ የማይዘነጋውን አወንታዊ ተፅእኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ይሁን እንጂ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትመራበትን ሕገ መንግስት መሰረት ባደረገው የፌደራሊዝም ስርአት አወቃቀር ላይ የተዘረጋውንያልተማከለ አስተዳደር ተከትሎ፤ በተቋቋሙት የህዝብ ምክር ቤቶችና በሌሎቹም ቁልፍ ሚና ለመጫወት የሚያስችል ስልጣን በተሰጣቸው መሰል መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚቀመጡ አንድ አንድ አስፈፃሚ አካላት፤ የተጣለባቸውን ታሪካዊ ሀላፊነት እየተወጡ ናቸው ለማለት እንደማይቻል ነው አንድ ከሰሞኑ ይፋ የሆነ ጥናታዊ መረጃ የሚያሳየው፡፡ ማለትም የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ተቋም የኢህአዴግ መራሹን መንግስት በጥልቀት የመታደስ ግምገማ ተከትሎ፤ ባካሔደው ሰፊ ጥናት ላይ የተመሰረተ ወቅታዊ ግኝቱን ይፋ ያደረገበት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ አብዛኛዎቹ አስፈፃሚ አካላት የሚጠበቅባቸውን ያህል አወንታዊ ሚና እየተጫወቱ አይደሉም፡፡
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋሙ ባቀረበው መረጃ ለተጠቃሾቹ አስፈፃሚ አካላት ድክመቶች መከሰት ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የተወሰደውም ደግሞ፤ በተለይም ፖለቲካዊ ሥልጣን ለማንና ለምን እንደሚያስፈልግ እንደ ሃገር የጠራ ግንዛቤ ያልጨበጥን ህዝቦች መሆናችን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ችግሮቻችንን ከምንጫቸው ለማድረቅ የሚያስችለንን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ብዙ አልረፈደምና ልብ ያለው ልበ ሊለው የሚገባ ጠቃሚ ጥናት ነው በተቋሙ ይፋ የተደረገው እላለሁ እኔ፡፡ በተረፈ ግን በዚሁ የጋራ ጉዳያችን ዙሪያ ሌሎቻችሁም የየራሳችሁን ሃሳብ ትሰጡበት ዘንድ መልካም መስሎ ይሰማኛል፡፡
መዓ ሰላማት!