በሕዝብ የተደገፈው ትግል

የጸረ ሙስና ትግሉ በስፋት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ሙስና ሀገርና ትውልድ ገዳይ በሽታ በመሆኑ ሊታገለው፣ ሊዋጋውና ሊያስወግደው የሚገባው ሕዝቡ ነው፡፡ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት የሞት ሽረት ትግል መሆኑን ደግሞና ደጋግሞ አስታውቆአል፡፡ በአሁኑ ሰአት በተጠናከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የጸረ ሙስና ትግልም ረዥም ርቀት መሄድ እንዳለበት ይታመናል፡፡

ትግሉን ከዳር ለማድረስ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ሙሰኞችን በተጨባጭ ማስረጃ እያጋለጠ የተዘረፈውን የሀገርና የሕዝብ ንብረት በመጠቆም ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብና መንግስት አምኖአቸው በከፍተኛ መንግስታዊ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች እምነትን አጉድለው፣ በዘረፋ ተሰማርተው እና ሕገወጥ ሀብት አከማችተው መገኘታቸው የከፋ የወንጀል ድርጊት ነው፤ ህዝብ ደግሞ የዚህ አይነቱን ወንጀል የሚሸከምበት ትከሻ የለውም፡፡

በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ግለሰቦችን የማሰር ፍላጎት ሳይሆን በሰሩት ወንጀል በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለ፣ ማንኛውም ኃላፊም ሆነ ግለሰብ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ውስጥ ተዘፍቆ ከተገኘ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡

በሕዝብ ተወክሎ፣ በሕዝብ ተመርጦ ወደስልጣን የመጣ መንግስት ለሕዝብ ተጠያቂነት ያለበት እንደመሆኑ መጠን በግለሰብ ደረጃ ያሉ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚገኙ ሰዎችም ስራቸው በሕዝብ የሚገመገም በመሆኑ፤ ከወንጀል የፀዱ ሆነው ካልተገኙ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና ቅሬታዎች፤ በተጨባጭ የሚያቀርባቸውን ማስረጃዎች መንግስት ሰምቶ በዝምታ የሚያልፋቸው አይደሉም፤ ጉዳዮቹ በጥልቀት ይፈተሻሉ፤ ይመረመራሉ፤ ለሕግና ፍትህም ይቀርባሉ፡፡

 

የጎለበተና የተጠናከረ የሕዝብ ተሳትፎ እየተጠናከረ ሲሄድ የሀገር ልማትና ግንባታ እንዲሁም የተጠያቂነት መርሕ አብሮ ያድጋል፡፡ በሀገር ደረጃ ባሉት ተቋማት ውስጥ በስፋት የተንሰራፋው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሀገራዊ የልማትና እድገት ስራዎችን በስፋት ጎድቶአል፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ መመረርና መከፋትን አስከትሎአል፡፡ ኢሕአዴግ ይህን የሀገር ጸር የሆነ ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት የተነሳ ለመሆኑ የሰሞኑ እርምጃዎቹ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢው የቁርኝት ሰንሰለት በተለያዩ ደረጃዎች ወደላይ፣ ወደጎን፣ ወደታችም ጭምር የተንሰራፋና የተስፋፋ በመሆኑ ይህንን መረብ በጣጥሶ ለመጣል አግባብ ባለው ስርአት መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡ ለመበጣጠስ የሚቻለው አሁን እንደተገኘው አይነት ሰፊ የሕዝብ ድጋፍን በማቀፍና በመያዝ ብቻ ነው፡፡

ሙሰኛው ማስረጃዎቹን አርቆ ከመቅበር እስከ መሰወር ከአካባቢው ውጭ በሩቅ ቦታዎች በወዳጅና ዘመድ አዝማዶቹ እጅ እንዲቀመጥለት፤ በዚህም ማስረጃ ለመሰወርና ደብዛ ለማጥፋት ሲሰራ መኖሩ ይታዋቃል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከሕዝብ የተደበቀ፣ የተሰወረ፣ የሚጠፋ አንድም ምንም ነገር የለምና ዞሮ ዞሮ ማንም ከመያዝ አያመልጥም፡፡

በእስከአሁኑ ጅምር እንቅስቃሴ ብቻ በተጠረጠሩት ሙሰኞች እጅ ያሉ ንብረቶች ታግደዋል፤ ተገቢ የሕግ እርምጃ ነው፡፡ ይህ እርምጃ ተጀመረ እንጂ ገና እልፍም አላለ፡፡ ይቀጥላል፤ ሙሉ በሙሉም በሕዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ ውጤታማ ይሆናል፡፡

በሕዝብ ድጋፍና ሰፊ ተሳትፎ የተጀመረው ይህ የፀረ-ሙስና ትግል ለአንዲትም ሰከንድ አይገታም፡፡ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሀገርን በማልማት ረገድ ግዙፍ ታሪክ ያስመዘገበ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ የዚህን ድርጅት ታላላቅ ስራዎች ለማቆሸሽ የተነሱት በውስጡ ተሸጉጠውና ተንሰራፍተው የነበሩት ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢ  ኃይሎች ሕዝብ ይሰራሉ ብሎ በኃላፊነት ወክሎ ባስቀመጣቸው ቦታዎች ላይ መንግስትንና የድርጅቱን ወንበርና ስም በመጠቀም የፈጸሙት አሳፋሪ አይን አውጣ ድርጊት ነው ሕዝቡን ምሬት  ውስጥ ከቶት የቆየው፡፡

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እኛ የምንሰራው አንድ እጃችን ታስሮ በአንድ እጃችን ነው ያሉት በስርአቱ ውስጥ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ምን ያህል ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነፍስ ዘርቶ እንደነበር አመላካች ነው፡፡ መለስ የእኛ ሌቦች ያሉትም በታሪካዊነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ የእኛ ሌቦች ያሉዋቸው በስርአቱ ውስጥ ሁነው በመንግስትና ሕዝብ ወንበር ላይ ተቀምጠው የሚዘርፉትን ነበር፡፡

ትግሉ መልክና ደረጃውን እየቀያየረ ሲንከባለል ቆይቶ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ አሁንም ሀገርንና ሕዝብን ያስመረረ፣ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ሙስናና ምዝበራ የፈጸሙት ፈሪሀ ሕዝብ የሌላቸው፤ ነገ በሕግ ተጠያቂ መሆን ሕዝብ ፊት መቅረብ ይመጣል ብለው ለማሰብ ያልቻሉ፤ የዘረፉትንም ገንዘብ የት ሄደን እንበላዋለን ብለው ለማሰብ ያልቻሉ በራሱ በስርአቱ ውስጥ የነበሩ፣ በመለስ አገላለጽ የእኛ ሌቦች ናቸው፡፡

አዲስ ራእይ መጽሄት በአንድ ወቅት እንደገለጸችው የስልጣን ምንጭ መሪ የፖለቲካ ድርጅቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ወደስልጣን ለመውጣት ሕጉም ደንቡም አይፈቅድም፡፡ ይህንን ሕዝብን አገልግሉ ለሕዝብ ስሩ ተብለው የተሰጣቸውን የኃላፊነት ወንበር ተጠቅመው ነው ወደብልሹ አሰራርና ወደዘረፋ የተሰማሩት፡፡ ግዜ ቢወስድም ይሄው በሕግ የመጠየቁ ጉዳይ አይኑን አፍጥጦ መጣ፡፡

ትልቁ ነገር ከግለሰቦች መታሰርና አለመታሰር ጋር የተያያዘው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሕግ ተላልፈው እስከተገኙ ድረስ በሕግ መጠየቃቸው የነበረና ያለ ነው፡፡ ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ በሀገር ደረጃ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት መስራት ከፊት ለፊታችን ያለ ወሳኝ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ፤ ለዚህ ውጤታማነትም ሁሉም ዜጋ ለመስራት በቁርጠኝነት መነሳት ግድ የሚለው መሆኑን ግንዛቤ መውሰዱ ላይ ነው።

ሀገራዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ሕብረተሰቡን በአዲስ አስተሳሰብ መቅረጽ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር በትጋት መሰራት አለበት፡፡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ደካማና መናኛ አስተሳሰብ መወገድ ይገባዋል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ስሩ ሲባሉ መዝረፍና ሌብነት ውስጥ መግባት ነውረኛና አዋራጅ ድርጊት መሆኑን ለማሳወቅ ሚዲያው ጠንካራ ስራ መሰራት አለበት፡፡

በሀገርና በሕዝብ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች የግዴታ የሕግ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ የሚያዙት ሀብትና ንብረት የግላቸው አይደለም፤ የሀገር፣ የሕዝብና የመንግስት ሀብት እንጂ፡፡ በስራ ኃላፊነታቸው ዘመን ተጠንቅቀው መስራት፣ ከአድልዎ፣ ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት፣ ከደላሎችና ከአቀባባይ ከበርቴዎች መጥመድ ራሳቸውን መጠበቅ፣ በተቃራኒው ከሕዝብና ከመንግስት ፍላጎት ውጪ የሆኑ ብልሹ ድርጊቶችን አጥብቀው መታገልና መከላከል የሚጠበቀውም ከእነሱው ነው፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት የመንግስት አሰራር ሁኖ በጎለበተ መልኩ መቀጠል አለበት፡፡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ለመንግስትም፣ ለሕዝብም ሆነ ለሀገርም ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ የወንጀል ድርጊት ውስጥ የተነከሩትን በማሰር ብቻ አይፈታም፡፡ ሰንሰለቱ እርስ በእርሱ ሲጓተት ገና ብዙዎች ከተጠበቀው በላይ እንደሚታሰሩ መገመት ይቻላል፡፡ ማንም ሆነ ማንም ከሕግና ከሕዝብ በላይ አይደለም፡፡ ማስረጃና መረጃው እስከተገኘ ድረስ በሕግ መጠየቁ አይቀርም፡፡

ሰፊ የሆነው የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢው መረብ ተንሰራፍቶ የሚገኘው በተለይ መረቡን በስፋት የዘረጋው ወደታች ነው፡፡ በየደረጃው ያለው የፈጻሚና የአስፈጻሚ፣ የደላላውና የአቀባባዩ መረብና ድር በመንግስታዊ መዋቅሮች ውስጥ ሆነ በውጭ ሁነው በግላቸው በሚሰሩ ድርጅቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ያሉት ትእዛዝ በመስጠት በመፈረም ወዘተ ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው፡፡

ይህ ጉዳይ በውል ስለሚታወቅ ማስረጃው እስከተገኘ ድረስ ከላይ ከፍተኛ ኃላፊውና አመራሩም ሆነ ከታች ያለው በየደረጃው የሚጠየቁበት አሰራር በስራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ የምርመራው ሂደት መሄድ እስከቻለበት ርቀት ድረስ በመሄድ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጌታቸው አምባዮ የገለጹትም ለዚህ ነው፡፡

ባጠቃላይ፣ በመንግስት የተጀመረው የጸረ ሙስና እርምጃ የረዥም ግዜ ጥናት ውጤት ነው፡፡ የአንድ ጀምበር ስራ አይደለም፡፡ አሁን እንደሚታየው በጸረ ሙስና ትግሉ ውስጥ ሕብረሰተሰቡ መረጃዎችን በመስጠትና ሙሰኞችን በማጋለጥ ሰፊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የተጀመረውን ትግል ለታላቅ ውጤት የሚያበቃው ሕዝቡ በመሆኑ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በስፋት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡