በኢኮኖሚ የፈረጠመችን ኢትዮጵያ መገንባት የሚቻለው በዜጎቿ አቅም ብቻ ነው!!

የንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የንግድ ቢሮዎች የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲስፋፋና ህጋዊ የንግድ አሠራር እንዲሰፍን፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ፣ ለላኪዎች ድጋፍ እንዲሰጡ፣ የወጪና ገቢ እቃዎች በትክክለኛ ዋጋ ስለመሸጣቸው ወይም ስለመገዛታቸው ለማረጋገጥ እና ፀረ ውድድር ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል የተሟላ ሥርዓት እንዲዘረጉ – አፈፃፀሙንም እንዲከታተሉና በህግ አግባብ ለሸማቾች ጥበቃ እንዲያደርጉ የሚያስችል ተግባርና ሃላፊነት በአዋጅ እንደተሰጣቸው፤ በተለይ ለንግድ ሚኒስቴር ማቋቋሚያ የወጣወ አዋጅ ላይ በግልጽ ተመልክቷል። በተለየም፣ የንግድ ሚኒስቴሩ የውጪ ንግድ ግንኙነቶችን እንዲመሰርት እና የንግድ ድርድሮችን እንዲያስተባብር፣ ስምምነቶችን እንዲፈርም፣ አግባብ ባላቸው ህጎች መሠት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጥ፣ የተሰጡ የንግድ ሥራ ፈቃዶች ለተሰጡበት ዓላማ መዋላቸውንም እንዲቆጣጠር፣ የዋጋ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ዋጋ እንዲያጠናና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያቀርብ ሲፈቀድም ተግባራዊነታቸውን እንዲከታተል፤ በአጠቃላይ የአገሪቱን የንግድ ሁኔታ በበላይነት እንዲመራና እንዲቆጣጠር በአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 691/2003 የተቋቋመ አካል ስለመሆኑም በራሱ የመረጃ መረብ ላይ በግልጽ ተመልክቷል።

 

በዚህ አግባብ እና ከዚሁ የማቋቋሚያ አዋጅ በመነጨ በጥቅሉ በየደረጃው የሚገኙ የንግድ ቢሮዎችና ጽህፈት ቤቶች የተገልጋይና ባለድርሻ አካላትን እርካታና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ፣ ዕድሳት፣ ማሻሻያ፣ ምትክ አገልግሎት ወዘተ በመስጠት ላይ መሰረት ያደረገ ተግባርና ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ደግሞ የመንግስትን ደንብ፣ መመሪያና ስርዓት ጠብቆ ከተከናወነ ፍትሀዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ከማድረግ አኳያ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ መሆኑ አያጠያይቅም። ስለዚህም ነው የንግድ ዘርፉ ወደ ትክክለኛው ስርዓት እንዲገባ መደረጉ።

የዛሬው አቢይ ጉዳያችን እስከ ነሃሴ 10/2009 የተራዘመውን የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን እና ቀጥሎ የሚመጡትን ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የተመለከተ ሲሆን፤ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን የቀን ገቢ ግምት ተከትሎ የተስተዋለውን ቅሬታና ከቅሬታው በስተጀርባ የነበሩ የአመጻ ሙከራዎች እንዳይደገሙ ማስቻል ነው። ስለሆነም ገቢ ሲነሳ ንግድና የንግድ ስርአቱን ጨምሮ የገቢ ሰብሳቢ ጽህፈት ቤቶች የተሰጣቸውን ሃላፊነት ለመነሻ ወስዶ ማሄስ ያስፈልጋል። ለዚህም፣ ከላይ በየደረጃው ለሚገኙ የንግዱ ዘርፍ መዋቅሮች የተሰጡ ተግባራትን እና ሃላፊነቶችን በተመለከትነው አግባብ የገቢ ሰብሳቢውን መዋቅር ደግሞ ቀጥለን እንመልከት።

 

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጠንካራና ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ሥርአት በመገንባት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት በመሰብሰብ ለልማታችን የሚያስፈልገውን ወጪ በአገራችን ገቢ መሸፈንን እንደ ግብ ይዞ የተቋቋመ ስለመሆኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተመልክቷል። ከዚህ አንፃር መስሪያ ቤቱ ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ስድስት (በሰው ሃብት ስራ አመራርና ልማት፣ በዘመናዊ የመረጃ ስርአት አስተዳደር፣ የተገልጋዮች ትምህርትና ግንኙነት፣ የተገልጋዮች አገልግሎትና ድጋፍ እና የታክስ ህግ ማስከበርና ገቢ አሰባሰብ) የትኩረት መስኮችን አስቀምጦ በመስራት ላይ የሚገኝ ስለመሆኑም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ባሳተመው (2009) አመታዊ መጽሃፍ ላይ ተመልክቷል።

 

ግብር መክፈል የዜጎች የውዴታ ግዴታ መሆኑን ከመናገር ተቆጥቦ የማያውቀው የንግዱ ማህበረሰብ በተለይ ከደረጃ “ሐ” ጋር ተያይዞ ሰፊ ቅሬታ ያሰማ መሆኑ ይታወቃል፤የእለት ገቢ ግመታው ችግር ያለበት መሆኑን መጥቀስ ጭምር። ነገም ይህ እንዳይሆን ከላይ ከተመለከቱት የሁለቱ ተቋማት ተግባርና ሃላፊነት አንጻር የቅሬታዎቹን ምንጮች መፈተሽ ያስፈልጋል።

 

ስለዚሁ ጉዳይ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ካደረገው የሬዲዮ የቀጥታ ስልክ ውይይት እንደተረዳው፤ የቅሬታው ምንጭ ሆነው የተነሱት አብዛኞቹ ጉዳዮች ከላይ የተመለከቱት የሁለቱ ተቋማት ተግባርና ሃላፊነት ወደመሬት ሲወርዱ ሌላ ሆነው መገኘታቸው፤ በሌላ በኩልም ከላይ ስለተመለከቱት የተቋማቱ ተግባርና ሃላፊነቶች የተቋማቱ ፈጻሚና አስፈጻሚዎች አለመናበባቸው መሆኑን የሚያጠይቁ ናቸው።

 

የተገልጋይና ባለድርሻ አካላትን እርካታና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ፣ ዕድሳት፣ ማሻሻያ፣ ምትክ አገልግሎት ወዘተ የመስጠት ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም አሰራሩ ወጥነት የጎደለው መሆኑ የመጀመሪያው ነው። ለምሳሌ ህገወጥ ለሆኑ ንግድ ቤቶች (ለነዋሪዎች ማህበራዊ አገልግሎት በተሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የኮሙዩናል ቤቶች) ንግድ ፈቃድ መስጠት፤ ለተመሳሳይ የንግድ አገልግሎት በተለይ ጥቃቅን ለሆኑ የጉሊት መቸርቸሪያ መደቦች አንዱን ንግድ ፈቃድ እንዲያወጣ ማድረግና ሌላኛውን መዝለል፤ ለተመሳሳይ ህገወጥ ንግዶች የአንደኛውን ማሸግ ካጠገቡ ያለውን መክፈት፤ ለተከለከሉ የንግድ አይነቶች (ለምሳሌ ጫት ማስቃሚያ ቤቶች) የአንዱን ማሸግ የሌላውን መተው፤ በየንግድ መደብሩ የሚገኙ ሸቀጦችን እና ቁሶችን ህጋዊነትና ጤናማነት ሳያረጋግጡ ንግድ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ማደስ ወዘተርፈ የንግድ ውድድሩን የተዛባ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር በማድረግ ህጋዊ ነጋዴው ግብር የመክፈል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት እንዲያንገራግር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በጥቂቶቹ መሆናቸው በቀጥታ ውይይቱ ወቅት የተወሱ ናቸው።

 

በነጋዴዎችም በኩል ከአከራይ ጋር በሚደረግ መሞዳሞድ ዋጋ አሳንሶ የቤት ኪራይ ከመዋዋል ጀምሮ ለተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ የተከራዩት የቤት ስፋት፣ ጥራትና ያለበት አካባቢ በራሱ የቀን ገቢያቸውን የሚናገር ሆኖ ሳለ የንግድ ፈቃድ መዝገባቸው ላይ የሚያስመዘገቡት ካፒታል ምን ያህል በአቋራጭ የመበልጸግ ሴራቸውን እና ህጋዊውን ወደ ህገወጥ ድርጊት እንዲገባ አስገዳጅ ተጽእኖ የሚፈጥር እንደሆነም በውይይቱ ላይ ተመልክቷል። ከላይ በተመለከተው አግባብ ፀረ ውድድር ተግባራትን እንዲከላከል የሚያስችል የተሟላ ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ አፈፃፀሙንም እንዲከታተሉና በህግ አግባብ ለሸማቾች ጥበቃ እንዲያደርጉ የሚያስችል ተግባርና ሃላፊነት በአዋጅ የተሰጣቸው፣ ከላየ የጠቀስናቸው ቢሮዎችና ፈጻሚዎቻቸው በደንብና መመሪያው መሰረት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለመቻላቸው፤ በተቃራኒው ጸረ-ውድድር ተግባራት እንዲስፋፉ ከማስቻሉም በላይ ከማይቆጣጠሩት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምክንያት በመሆናቸውም፤ ከንግዱ ማህበረሰብ የቀረቡ ቅሬታዎችን እንኳ ለመፍታት አዳጋች የሆኑ ሁኔታዎችን የፈጠረ መሆኑም ተመልክቷልና እነዚህ ቢሮዎች ወደፊትን ታሳቢ ያደረገ አሰራር በመዘርጋት ጉዳዩን ሊያጠሩ እና ህጋዊና ህገ-ወጡን በመመንጠር ለተሻለ እና ፈጣን ለሆነ አሰራር የሚያመች ስርአት ሊዘረጉ ይገባል።

 

ወደ ገቢ ሰብሳቢ ተቋማቱ እንመለስ፤ በእርግጥ በቀን ገቢ ትመና የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በውይይትና በመግባባት እየተፈቱ ስለመሆኑ መንግስትና በማእቀፉ ውስጥ የሚገኙ የንግዱ አካላት እየገለጹ ነው። ይህ እንዲሆን ያስቻለውም በዕለት ገቢ ትመና ላይ የሚፈጸም ስህተትን ለማረም አሳታፊና ህጋዊ የቅሬታ አፈታት ስርዓት በመዘርጋቱ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል። በዚህ ሂደት እስከነጫጫታውም ቢሆን የትናንትን፣ የዛሬን እና የነገን የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ዋነኛው አቅም ግብር ከፋዩ ህዝብ መሆኑም ተረጋግጧል። አዲሱ የግብር አሠራር በርካታ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ለዓመታት የቆየውን የህጋዊ ነጋዴዎች ጥያቄ መመለስ አስችሏል። ያም ሆኖ ግን የዚህ ፅሁፍ ግብ ወደፊት ያለአንዳች ጫጫታ ግብር ከፋይ የሆነው ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን መክፈል የሚያስችለውን አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችሉ የህዝብ አስተያየቶችን መጠቆምና በንግድ ቢሮዎች ተግባርና ሃላፊነት ልክ የጫጫታዎቹን ምንጮች ከተቋሙ አንጻር ማሄስ ነውና ጥቂቶቹን እና መሰረታዊ የሆኑትን እንመልከት።

 

ጠንካራና ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ሥርአት በመገንባት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት በመሰብሰብ ለልማታችን የሚያስፈልገውን ወጪ በአገራችን ገቢ መሸፈንን እንደ ግብ ይዞ የተቋቋመ ስለመሆኑ ከላይ በተመለከተው አግባብ የተነገረለት የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን በተቋቋመበት አግባብ ጠንካራና ዘመናዊ ሆኖ አለመገኘቱ የጫጫታው መነሻ ነው።ዘመናዊ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ግምት ያመራው ባለስልጣኑ የግመታን ጽንሰ ሃሳብ እና ለግመታ የሚረዱ የመነሻ ምክንያቶችን ባልተረዱ ዘፈቀዳዊ ባለሙያዎች መሞላቱም ከላኛው እና መሰረታዊ ከሆነው ችግሩ ጋር ተያያዥ የሆነው የጫጫታ ምንጭ ነው።

 

ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ስድስት የትኩረት መስኮችን አስቀምጦ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑ የተነገረለት የቋም ከዘመናዊ የመረጃ ስርአት ጋር የማይተዋወቅ፤ ፈፃሚ/አስፈፃዎቹም ተገልጋዩን ከመደገፍና ህግ ከማስከበር ይልቅ ተገልጋዩን በሚያማርሩ እና ህጋዊውን አሰራር ለኪራይ ሰብሳቢነት የግል አጀንዳቸው የሚቀለብሱ ሆነው መገኘታቸውም የጫጫታው መነሻ ስለመሆናቸው ጉዳዩ በሚመለከታቸው ወገኖች ተነግሯል።

 

በተለይ ከቀን ግምቱ ጋር ተያይዞ የተነሳውንና ኢ-ምክንየያታዊ የነበረውን አሰራር እዚህ ጋር በመሰረታዊነት ማንሳት ጠቃሚ ይሆናል። የቀን ገቢ ግመታው በነጋዴው እና በገማቾቹ የሁለትዮሽ መረጃ እና ምልከታ ላይ ተመስርቶ የሚወሰንና እዚያው ከንግድ ቤቱ ላይ የሚፈራረሙ እንደሆነ በዚያው ሰነዱ ላይ በግልጽ ተመልክቶ ሳለ የነጋዴውን መረጃ በመውሰድ ገማቾቹ ከቢሯቸው ተቀምጠው በመወሰን በደብዳቤ ለነጋዴው የሚያሳውቁበት አሰራር የህግም ሆነ የአሰራር ድጋፍ የሌለው ከመሆኑም በላይ ከላይ ከተመለከተው እና ተቋሙ እያከናወናቸው ነው ከተባሉት ተግባራቱ ጋር ፍጹም ተጣራሽ፤ ግብር ከፋይ የሆነውን ህብረተሰብም ያስከፉ መሆናቸው በውይይቱ ላይ ከተነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ሲሆን፤ ወደፊትም የዚህ አይነቱ ጫጫታ አይደገም ዘንድ ሊታረም የሚገባው መሆኑ ላይ በመግባባት ነው።

 

ይህም ሆኖ ግብር ከፋይ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ እየከፈለ ነው። ከላይ የተመለከቱት፣ መፈጸም ያልነበረባቸው ስህተቶች እንዳሉ ሆኖ በአሰራር አግባብ በገቢ ትመና ወቅት አልፎ አልፎ ስህተት መፈጠሩ ይጠበቃልና ስህተቱን በተቀመጠው አሰራርና ስርአት ብቻ ካለመፍታት ባሻገር ቅሬታ አቅራቢውን ህብረተሰብ በአግባቡ እና በሚገባው መንገድ አለማስረዳት ያመጣውን ጣጣ ለወደፊት ማሰብና ከዚህም ተሞክሮ በመቀመር የተሻለ፤ በተለይ ፈጻሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል።

 

ከዚያም ባሻገር የግብር መሰብሰቡ ዓላማና የመንግሥት ፍላጎት አንዲት የጠነከረች አገር ለመገንባት የሚቻለው በእርዳታ ብር ሳይሆን በዜጎቿ አቅም ስለሆነ ብቻ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል። የአገራችንን ልማት ከወደፊት የአገር ተረካቢ ልጆቻችን ጥቅም ጋር በማያያዝ የልማቱ መፋጠን፣ የሰላሙ በዘላቂነት መቀጠል ከእኛ አልፎ ለልጆቻችን የሰመረ ህይወት ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑንም ማጤን ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ይጠበቃል። ከዚህ ባሻገር ይህንን እንደመነሻ በማድረግ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሲታይ የነበረው ከቅሬታ የዘለለ ድርጊት የጽንፈኞች ሴራ ነው። ለነጋዴው ማኅበረሰብ ከመቆርቆር የመነጨ ሳይሆን አጋጣሚውን ተጠቅመው አመጽ በማነሳሳት በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ ነው። የግብር አከፋፈል ሂደቱ በደረጃ እየተከፋፈለ እስከ ታህሳስ ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ እነርሱም ሴራቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። በመሆኑም፣ እነርሱ የሚቀሰቅሱት አመጽ የነጋዴውን የተረጋጋ ህይወት ለማወክ፣ ንግድ ቤቱን ለማዘጋትና ከመንግስት ጋር ለማጋጨት መሆኑን ግብር ከፋይ የሆነው ህብረተሰብ ጠንቅቆ ሊገነዘብ ይገባል፡፡