የዋጋ ንረትና የህብረተሰቡ ሚና

መልካም አስተዳደር ለውጥ ቢኖረውም አሁንም ችግር ሆኖ እየቀረበ ነው። በአሁኑ ወቅት እንደ ስኳርና ዘይት እንዲሁም ብረትን በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አሁንም ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያያዙ ችግሮች መኖራቸው ግልፅ ነው። አንድ ችግር እስካለ ድረስ መፍትሔውንም አብሮ ማመላከት ያስፈልጋል።

በአሁኑ ሰዓት መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው። ሆኖም መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም። እናም ችግሩን ለመከላከል የህብረተሰቡ ወሳኝ ሚናውን መጫወት አለበት። በተለይ ሸቀጦች በስውር እጅ በኮንትሮባንድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በውድ ዋጋ እየተቸበቸቡና በዚያው ልክም ህብረተሰቡን እያማረሩት ስለሆነ ህዝቡ እንዲህ ዓይነት ችግርን አይቶ እንዳላየ ማለፍ አይኖርበትም። በጥቆማ ከመንግስት ጎን መሰለፍ አለበት።

እርግጥ መንግስት የዋጋ ንረትን ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ ነው። እንደሚታወቀው መንግስት ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያ ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር እያደረገ ነው። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም እንዳይደረግም እየተቆጣጠረ ይገኛል።

የተደረገው የገንዘብ ማሻሻያ አገሪቱ ለድርቅ ያልተጋለጠችበትና ከፍተኛ የመኸር ሰብል ምርት በሚገኝበት ጊዜ እንዲደረግ መወሰኑ በገበያው ያለውን የምርት መጠን እንዳይጓደል እና የእህል ዋጋ ንረት እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።

ቀደም ሲል ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች  ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ ይደረጋል።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሃዝ በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት አከፋፍሏል።

እንዲሁም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበትን እንደ የጅምላ መሸጫና የሸማቾች ማህበርን በማደራጀት የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግስት ነው። ይህም የኢፌዴሪ መንግስትን ህዝባዊነትና ሁሌም ቢሆን ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እርግጥ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ምሳሌዎች እጅግ ከሚበዛው የመንግስት ተግባራት ውስጥ ጥቂቶቹን ነው። ምንም እንኳን እነዚህ መንግስታዊ ህዝባዊነት ምሳሌዎች ቢሆኑም፤ ዋናውንና መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍና ሁሌም ተግባሮቹን የሚያከናውነው ህዝቡን ጥያቄ ተነስርቶ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለምርት መጠኑ ማደግ መንግስት ከፍተኛ ተግባራት ፈፅሟል። አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያንና ሌሎች አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ አግኝቶ ወደ ምርት ተግባር እንዲገባ በማድረግ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ልዩ ልዩ የቴክኒክ ድጋፎችን የመስጠት ስራዎችን በመከወን ውጤታማ ተግባራትን በመፈፀሙ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ እንዳይንር ለመቆጣጠር ችሏል፡፡

ሌላው የባንኮች የፋይናንስ ሥርዓት የማስተካከል ሁኔታና የዜጎች የቁጠባ አቅም እንዲያሳድጉ በመደረጉ ሳቢያ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተቻለበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የብድር ሥርዓቱን የመቆጣጠር ተግባር በገበያው ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ መረጨቱ የዋጋ ንረት እንዲስተካከል የሚያደርገው የቁጥጥር ዘዴ የመፍትሄው አንዱ አካል አድርጎ በመንቀሳቀሱ ስኬታማ ሆኗል፡፡

ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚው የማምረት አቅም የተሻሻለ፣ ቀጣይና ተከታታይነት ያለው እንደነበር አይካድም፡፡ በርግጥ ይህ ልዩነት እምብዛም የገነነ ነው ብሎ መጥቀስ ግን አይቻልም፡፡ ይህ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የዋጋ ንረቱን እየተቆጣጠረው ነው፡፡

የገበያ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲል ከራሱ ካዝና በመደጎምም ይሁን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በበጀቱና ገቢው ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንዳለው አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም እነዚህን ተፅዕኖዎች እንዳሉ እየተገነዘበም ቢሆን፣ ተገቢ እርምጃዎችን ከመውሰድ ወደ ኋላ አላለም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስት ሩቅ አሳቢነትን አጉልቶ የሚያሳይ ሃቅ ነው፡፡

መንግስት የዋጋ ንረቱን በማስተካከል የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ የሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉን በተጨባጭ ለመመልከት ችለናል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው ካሉ ርምጃዎች መካከል የብድር ሥርዓቱን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ሌላው ከነጻ ገበያ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ በገበያው ውስጥ የተሰራጨውን ከፍተኛ መጠን ያለው የብር ተመን ንረት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡

ለዋጋ ንረቱ መባባስ ምክንያት ሆነው የቆዮት ከላይ የጠቀስናቸው ጉዳዮች ብቻ አይደሉም። ከንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ብቻ በዋጋ በመመሳጠር ክፍተት ሲፈጥሩ የቆዩበት የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የኮንትሮባንድ አሰራር ሁኔታም አንዱ ነው። በስኳር፣ በዘይትና በብረት ምርቶች ላይ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው።

እንቅስቃሴዎቹ መልሰው የሚጎዱት ህብረተሰቡን ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ምንም ዓይነት ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሲመለከት ያለ አንዳች ማመንታት እርምጃ እንዲወሰድ ማመልከት ይኖርበታል። ይህን ሲያደርግም አገሩን ከኪሳራ ራሱንም ከተጎጂነት ይከላከላል።

አገራችን የምታመርታቸው ምርቶች እንዲሁም ከውጭ የምታስገባቸው እቃዎች በኮንትሮባንድ ገበያ ላይ መዋል የለባቸውም። ምንም ዓይነት የምርት ሂደት ከህጋዊ አሰራሩ ውጭ ግብይት ሊካሄድበት አይገባም። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሊወገዝ ይገባል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ምንም ዓይነት የወንጀል ተግባር ባለመኖሩ ህበረተሰቡ ህገ ወጦችን በማጋለጥ የድርሻውን ተግባር ሊወጣ የግድ ይለዋል።