ህገ መንግስታዊው በጀት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት የ2011 ዓ.ም በጀት አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ ከአጠቃይ በጀቱ 64 በመቶው ለድህነት ተኮር የልማት ስራዎች መያዙን ገልፀዋል። ይህ የበጀት ድልድል እንደ እኛ ላለ ድህነትን ለመቀነስ እየተረባረበ ላለ ሀገር ትርጉሙ ከፍተኛ ነው።

በጀቱ የኢትዮጵያን ዕድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ፤ ድህነትን ለመቅረፍ ለሚያስችሉ የልማት ስራዎች የሚውልና የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲያድግ የሚያደርግ ነው። በተለይም ለበጀት ዓመቱ ከተዘጋጀው አጠቃላይ በጀት፤ 16 በመቶው ለክልሎች የሚፋፈልና የታዳጊ ክልሎችን ልዩ ፍላጎት መሙላት የሚያስችል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይም የያዘ ነው። ይህም በህገ መንግስቱ ላይ ታዳጊ ክልሎችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች ከኢኮኖሚ አኳያ ያላቸውን እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው።

ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዩችን በሚዳስሰው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 41 (3) ላይ እንደተመለከተው፤ የኢትዮጵያ ዜጐች ሁሉ በመንግስት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ ማንኛውም ኢትዮጰያዊ መንግስት በሚመድበው ማናቸውም በጀት በእኩልነት መጠቀም እንደሚችል የሚያሳይ ነው። የ2011 ዓ.ም በጀትም ይህን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው። እንዲያውም ከዚያም በላይ ጋምቤላን፣ አፋርንና ቤኒሻንጉልን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከግማሽ ቢለዮን ብር በላይ ልዩ ድጎማ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያደርግ ነው። ይህም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 89 (4) ላይ፤ መንግስት በዕድገት ወደኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ በተቀመጠው መሰረት ገቢራዊ የሆነ ነው።  

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 89 (2) ላይ የተቀመጠው ኢኮኖሚያዊ ድንጋጌም፤ መንግስት የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሃብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ እንዳለበት ያስረዳል። የ2011 ዓ.ም በጀት ይህን ህገ መንግስታዊ ግዴታ ያሟላ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝቦች በሀገሪቱ ከተፈጠረው ሃብት እኩል እድል ኖሯቸው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ስለሆነ ነው። የሀገራችን ሃብት መገለጫ ደግሞ መንግስት በየዓመቱ የሚይዘው በጀት ነው። ይህ ሃብት ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግና የነፍስ ወከፍ ገቢውም እንዲጨምር ያደርጋል።

ክልሎች በውክልና ለሚያከናውኗቸው ተግባሮች ወጪያቸው በወካዩ አማካኝነት የሚፈፀም ነው። እዲሁም ከፌዴራል መንግስት የሚመደብላቸው ድጎማን ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን አለው። ይህን ሁኔታ በተመለከተም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 94 ንዑስ ቁጥሮች አንድና ሁለት ላይ በሚገባ ተቀምጧል። በአንቀፁ ላይ የተመለከቱት ንዑስ ቁጥሮች፤  የፌዴራሉ መንግስትና ክልሎች በሕግ የተሰጧቸውን ኃላፊነቶችና ተግባሮች ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በየበኩላቸው እንደሚሸፍኑ እንዲሁም ማንኛውም ክልል በውክልና ለሚፈፅመው ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ ሌላ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ውክልናውን በሰጠው ወገን መሸፈን እንደሚኖርበት ይገልፃሉ።

በተጨማሪም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ ለመልሶ መቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ እርዳታ ሊሰጥ እንደሚችል ብሎም የፌዴራሉ መንግስት ክልሎች ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጐማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን እንደሚኖረው የሚያብራሩ ናቸው። ይህም በህገ መንግስቱ መሰረት ለክልሎች የተመደበው በጀት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲመጣና በጀቱም ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች የሚሰጠው ድጎማ ቀመርም ህገ መንግስታዊ ነው። እንደሚታወቀው ክልሎች የሚያገኙት ድጎማ የተለያዩ ጉዳዩችን ታሳቢ ያደረገ ነው። እነርሱም ለሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፣ ለጤና፣ ለውሃ፣ ለከተማ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለገጠር ልማትና ለመሳሰሉት የወጪ ፍላጎቶች ናቸው። እንዲሁም የክልሎች ገቢ የማመንጨት አቅም ሌላው የበጀት ቀመሩ መመዘኛ ነው።

አሁን እየተሰራበት ያለው ይህ ቀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ መስተካከል የሚገባው ነገር ካለም የሚስተካከል ነው—ፌዴሬሽን ምክር ቤትም እንደ ማንኛውም መንግስታዊ ተቋም በሪፎርም ውስጥ ያለ ነውና። ርግጥ በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ ሀገር የህዝቡን ፍላጎት እየተከተለ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዩች ካሉ እንዲታረሙ ያደርጋል። የ2011 ዓ.ም በጀት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ደግመው ደጋገመው ፈትሸውታል። ተወያይተውበታል። ሁሉም መስፈርቶች በጥንቃቄ ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል። በጀቱ በየደረጃው መስፈርቶችን አልፎና ተጠንቶ ስራ ላይ እንዲውል የተወሰነ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።    

ርግጥ ክልሎች የራሳቸውን በጀት የህዝቡን ህገ መንግስታዊ ተጠቃሚነት ባማከለና ብክነትን በሚያስወግድ መንገድ በአግባቡ አብቃቅተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። በተለይም በጀቱ ሙስናን ከመሰሉ እጅግ አስነዋሪ ተግባሮች ፀድቶ ህዝቡን እግር ተወርች የያዘውን ድህነትን ለመቅረፍ ለሚደረገው ሁለንተናዊ ርብርብ ማዋል ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ስራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም ህገ መንግስታዊ መብት አለው።

በጀቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ ዕድገት የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን እንዲያረጋግጥ ተደርጎ የተያዘ ነው። በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ልማት የመሳተፍ እንዲሁም በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት ስላለው የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋልና አለመዋሉን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

በሀገራችን ውስጥ በመንግስት ገንዘብ የሚካሄዱ ማናቸውም የልማት ተግባሮች፤ የዜጐችን ዕድገትና መሰረታዊ ፍላጎትን እንዲያሟሉ ታስበው የሚከናወኑ ናቸው። በጀቱም ዕድገትን የሚያረጋግጥና ዜጎች ካላው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ እንዲፀሙላቸው የሚፈልጓቸውን ጉዳዩች ለመፈፀም የተያዘ ስለሆነ ቁጥጥርና ክትትል የሚያስፈልገው ነው። ከፋይናንስ ኦዲት ባሻገር፤ ምን ታቅዶ ምን ተከናወነ?፣ አፈፃፀሙስ ምን ይመስላል? የሚሉ የክዋኔ ኦዲት ስራዎችም መከናወን አለባቸው። የፋይናንስ ኦዲት ፍተሻ አንድ ጉዳይ ቢሆንም፤ መሳ ለመሳም የክዋኔ ኦዲት ስራውም መከናወን አለበት። ገንዘብ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ገንዘቡ ምን ሊሰራ ቻለ? የሚለው ጉዳይም አብሮ መመለስ አለበት። ይህም አላስፈላጊ ወጭንና ቁጠባዊ የገንዘብ አጠቃቀምን ለመለካት የሚያስችል አሰራር ይመስለኛል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመንግስት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ህገ መንግስቱ እንደሚያስረዳ ከላይ ገልጫለሁ። ይህም ታዳጊ ክልሎች በሚሰጣቸው ልዩ ድጋፍ መላ አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም በድጋፉ የህዝባቸውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም ታዳጊና ሌሎች ክልሎች በጀቱን ድህነትን ለመቀነስ ተግባሮች በቁጠባ አብቃቅተው ከተጠቀሙ፤ በክንዋኔ ድምር ውጤታቸው የእያንዳንዱን ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ በመጨመር የሀገራችንን ዕድገት እያሳለጡ ወዳለምንበት ህዳሴ እንድናመራ የሚያደርጉን መሆናቸውን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል።