ለውጥ አምጭው

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት መሰረቱ የግብርናው ዘርፍ ነው። ግብርናው የአገራችንን የኢኮኖሚ መሪነት በመዋቅራዊ ለውጡ ሳቢያ ለኢንዱስትሪው እስኪያስረክብ ድረስ የዕድገታችን መሰረት ሆኖ ይቀጥላል። እንደሚታወቀው ሁሉ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን ውስጥ ነዳጅ ተገኝቷል። ነዳጅ መገኘቱ አንድ ነገር ነው። ሆኖም የተገኘው ነዳጅ ለአገራችን ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም ፈጣሪ እንጂ ወሳኝ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ‘ነዳጅ ተገኘ’ በሚል የተሳሳተ ስሌት ህብረተሰቡ ያልተገባ ተስፋ ውስጥ መግባትም ያለበት አይመስለኝም።

እርግጥ ይህን ለማለፍ የፈለግኩት ያለ ምክንያት አይደለም። አንዳንድ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ሆን ብለው የነዳጁን ጉዳይ በማጦዝ በህዝቡ ውስጥ የማይጨበጥ ተስፋ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት በማስተዋሌ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መሰሪ ተግባር ህዝቡ የጠበቀውን ነገር በሚያጣበት ወቅት በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ ታልሞ የሚከናወን መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይደለም።

የነዳጁን የሙከራ ምርት መጀመር አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት እንዳስታወቁት ከዛሬ ጀምሮ በሙከራ ደረጃ በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣቱ ስራ ይከናወናል። አሁን የማውጣቱ ስራ ሀገሪቱ ያላትን አቅም ማወቅን ታሳቢ ያደረገ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል። ወደፊት ያለን አጠቃላይ አቅም ታውቆ በቀጣይ በሙሉ አቅም ድፍድፍ ነዳጁን የማውጣት ስራ እንደሚከናወንም ማስረዳታቸው ይታወሳል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ አባባል የሚያሳየንም ነዳጁ አሁኑኑ የአገራችንን ችግር ይቀርፋል ማለት እንዳልሆነ ነው።

እርግጥም ነዳጅ መገኘቱ ከረጅም ጊዜ አኳያ ተስፋ ሰጪ ካልሆነ በስተቀር አሁን የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍትሔ የሚሰጥ ሊሆን አይችልም። በተገኘው ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ከአቅም፣ ከመጠን፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከማጣራትና ከሽያጭ እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ተጓዳኝ ስራዎች አኳያ ረጅም ጊዜን የሚወስድ ነው። ይህ ሃቅም አንዳንድ ወገኖች በነዳጅ ምክንያት የአገራችን ችግሮች ዛሬውኑ መፍትሔ እንደማያገኙ ማወቅ አለባቸው።

አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የእድገታችን መሰረቱ ግብርና ነው። የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምንና ኢኮኖሚውን እንዲያሳድግ መንግስት ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል። ዘርፉ ጠንክረን ከሰራን በህዝቡ የነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ2010/11 በአገር አቀፍ ደረጃ ከመኸር እርሻ ለማግኘት የታሰበውን 370 ሚሊየን ኩንታል ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ለዚህም የኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ለ2010/11 የመኸር እርሻ ቀደም ብለው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይገልፃሉ።

የኦሮሚያ ክልል በመኸር 6 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በሰብል በመሸፈን 203 ሚሊየን ኩንታል ለመሰብሰብ አቅዷል። ክልሉ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል ያቀደ ሲሆን፥ እስካሁን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ማዳበሪያ ማሰራጨቱ ታውቋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የአማራ ክልልም በመኸር እርሻው 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 110 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዷል። ይህን ለማሳካትም ከሶስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ማህበራት አሰራጭቷል። በዚህም ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ችሏል።

በምስራቅ የአማራ ክፍል ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ከታየው የዝናብ መዘግየት ውጭ ያለው በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዝናብ ስርጭት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ምቹ መሆኑም ተገልጿል። በዚህም ከ157 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደ በቆሎ እና ማሽላ ባሉ ሰብሎች እንደተሸፈኑም ያገኘኋቸው መረጃዎች ያስረዳሉ።

በበልግ እርሻ ምርቱ የሚታወቀው የደቡብ ክልልም በመኸር እርሻው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ከ38 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰራ ነው። ከዋና ዋና አዝዕርት ሰብሎች በተጨማሪ በሆልቲካልቸር ሰብሎች ከ55 ሚሊየን ኩንታል በላይ ለመሰብሰብም አቅዷል።

በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010/11 የመኸር እርሻ 370 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱ ምርትን በተቢው መንገድ የሚያስገኝ ነው። መንግስትም በያዝነው ዓመት 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሰራ ነው።

የማዳበሪያ አቅርቦቱም ከአምናው ጭማሪ ያሳየ ነው። በተለይም በቅርቡ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም የበልግ ምርትን በማሳደግ የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ከላይ ከጠቀስኳቸው አሃዞች ብቻ በአገራችን ውስጥ የግብርናው ዘላቂ መሰረትነት ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን ለመገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል። እርግጥም የግብርናው ዘርፍ በአግባቡ ከተያዘ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው።

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ቅዱ ላይ የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ዕድ ተይዟል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ይሁንና እስካሁን የተመዘገቡ ለውጦች ቢኖሩም በቂ ናቸው የሚባሉ አይደሉም። በተለይ የግብርናው ዘርፍ የምርት መጠን ቢጨምርም በቂ አለመሆኑ በተለያዩ መድረኮች ተወስቷል። ይህም በዘርፉ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።

አሁንም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተወሰኑ ተግዳሮቶች አሉ። እርግጥ የግብርና ምርት የጥራት ችግርና ብክነት አሁንም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች መሆናቸው ይታወቃል። በተለይ በድህረ- ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ሶስተኛው የግብርና ምርታችን ይባክናል። መባከን ብቻም ሳይሆን በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።

በተጨማሪም ምርት በወቅቱ ባለመታጨዱ ምክንያትም ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ተበላሽቶ ለብክነትና ለጥራት መጓደል የሚጋለጥበት ሁኔታም አለ። እነዚህን ችግሮች ስር ከስር እየተከታተሉ በበመፍታት ምርትን መጨመር ይቻላል። ይህም የዕድገታችን ምንጭ የሆነው ግብርና ለውጥ በማምጣት ተጠቃሚነታችን ያረጋግጣል። እናም አሁን ባለንበት ደረጃ የአገራችን ዕድገት ነዳጅ ሳይሆን የግብርናው ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ መረባረብ ይኖርብናል።