ፅኑው አቋም

በማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ያጋለጡት የመንግስት ሚዲያዎች መሆናቸው ሊበረታታ የሚገባው አዲስ ጅምር ነው። ይህም መንግስት ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ያለውን ፅኑ አቋም የሚያሳይ ነው። በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አካባቢ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ህገ መንግስቱን የሚጻረሩና ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ የተጎናጸፏቸውን መብቶች የሚጋፉ ናቸው።

በተለይ ሰብዓዊ መብቶች ዜጎች ሰው ስለሆኑ ብቻ በተፈጥሮ የተጎናጸፏቸው መብቶች በመሆናቸው ሊነፈጉ አይገባም። የትኛውም አስፈጻሚ አካል እንዳሻው ሊጥሳቸው አይቸልም። ያም ሆኖ እንደዚህ ዓይነት ጥሰቶች በተደራጀና አስተማሪ በሆነ መንገድ ህዝቡ እንዲያውቃቸው ማድረግ አሁንም አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ፈጻሚዎችም ዳግም ችግሩን እንዳይፈጥሩ ማስተማሪያ ሊሆኑ ይገባል።

ስለሆነም ችግሮቹን በቅድሚያ በፌዴራል ደረጃ መመልከትና ከዚያም ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው አራቱ ክልሎች (ማለትም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ) አንጥሮ በመፈተሽ ተገቢው ትምህርት እንዲወሰድ ማድተግ ያስፈልጋል። ይህም ህገ መንግስቱን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶችንና የተጠያቂነትን አሰራር በየደረጃው ለማንገስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

እርግጥ ባለፉት ጊዜያት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይፈፀምበት እንደነበር መካድ  አቻይልም፣ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ተግባሮች አረጋጋጭ ናቸውና።  በዜጎች ላይ ሲፈፀም የነበረው የመብት ጥሰት ከፍተኛ መሆኑን የሚዲያዎቹ ዘገባዎች እያረጋገጡ ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በህገ መንግስቱ ላይ ያረጋገጠ ህዝብ በዚህ ሁኔታ መብቱ የሚገፈፍ መሆን የለበትም። 

ዜጎች በገዛ አገራቸው ውስጥ (ለዚያውም በህግ ጥላ ስር ሆነው) አካላቸው ሊጎድል፣ ስቃይ ሊደርስባቸው፣ የዘር ፍሬያቸው ከጥቅም ውጭ ሊሆን አይገባም። አንድን ግለሰብ በተጠርጣሪነት አሊያም በወንጀለኝነት ይዞ መልሱ ሰብዓዊ መብቱን መግፈፍ አስነዋሪ ተግባር ነው። የጉዳዩ ፈፃሚዎች በህግም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል። ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የዜጎች ህይወትና የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባም።

ዜጎች በህገ መንግስቱ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ተደርጓል። ሰው በመሆናቸውም በሁሉም መስኮች በእኩልነት መስተናገድ ይኖርባቸዋል። ከሰብዓዊ መብቶች ውስጥ አንዱ መገለጫ የሆነው ታራሚዎች መብቶቻቸው ሳይነካ መያዝ ነው።

መንግስት የዜጎቹን ሰብዓዊ መብቶች ካላከበረ አገራዊ ሰላምን እውን ማድረግ የሚችል አይመስለኝም። ሰላም ካለተረጋገጠ ደግሞ የአገራችን ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም። ስለሆነም መንግስት ሰብዓዊ መብቶች በየትኛውም አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ውስጥ እንዳይፈጸሙ መከላከልና አስተማሪ እርምጃም መውሰድ አለበት።

የዴሞክራሲያዊ መብቶች ትግበራም ከዚህ የተለየ አይደለም። መንግስት እንደ ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብረው እንዲሁ የህልውና ጉዳይ ስለሆነበት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የሚከበረው የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አይደለም።

አገራችን የምትከተለው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ስለሆነ ብቻ ነው። እናም እንደ ማረሚያ ቤት ያሉ ተቋሞች የዜጎችን ሰብዓዊ መበት ጥሰው ሲያበቁ ዜጎች የደረሰባቸውን መግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ነገ ይህ ተግባር እንዳይቀጥል የሚያደርግ ስለሆነም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ህገ መንግስቱ ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የግለሰብና የቡድን መብቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ መብቶች በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

መብቶቹ ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው። በሀገራችን ውስጥ የሚታየው ተደራጅቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያመላክትና ለፖለቲካ ሂደቱ አዲስ መንገድ በፍጥነት እየታየ ነው። ዜጎች በግልም ይሁን በቡድን መብታቸውን መጠቀም ይችላሉ። ሰልፎችንም ማካሄድ ህጋዊ መብታቸው ነው። ታዲያ እነዚህን መብቶች መከልከል አይቻልም። መብቶችን መከልከል ማለት መልሶ ህገ መንግስቱን በመጻረር እንደመቆም ይቆጠራል።

ይህ ሁኔታም መንግስት ማናቸውም ዓይነት ድምፆች ተሰምተው ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ሌላኛው ጉዳይ ነው። ማናቸውም የቡድንና የግለሰብ ፖለቲካዊ መብቶች ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት የሚከናወኑና ከበሬታ የሚቸራቸው ብሎም በመንግስት ጉልህ ጥበቃ የሚደረግላቸውም ለዚሁ ነው ማለት ይቻላል።

ሰብዓዊና መብቶች የሚነጣጠሉ አይደሉም። በዓለም አቀፍ ደረጃም ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው። አገራችን የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም መብቶቹ እንዲከበሩ ያዛሉ። እነዚህን መብቶች መተላለፍ ለተጠያቂነት የሚዳርግም ነው።

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በተቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ዜጎችን ያሰቃየ ማንኛውም ሰው እንደሚጠየቅ ግልጽ ነው። መንግስት ችግሩን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ የሚያስመሰግነው ነው። ይሁን እንጂ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው አስተማሪ እርምጃ ከላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መቅረት የለበትም።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እየተወሰዱት ያሉት እንቅስቃሴዎች ተገቢና አስተማሪ ናቸው። የጥሰቶቹ መጠንም በተለይ ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች ውስጥ መታወቅ አለበት።      

ከዛሬ 3 ወር በፊት አገራችንን ለቀውስ ዳርገዋት ከነበሩ ጉዳዩች መካከል አንዱና ዋነኛው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው። ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሳይሸራረፉ እንደምታከበር አስፍራ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ለመፈጸም ፈርማ ስታበቃ፤ ህገ መንግስቷ በመጻረር የዜጎችን መብቶች መጋፋት የምትችልበት አሰራር እንደሌለ በየደረጃው የሚገኝ አስፈጻሚ ማወቅ ይኖርበታል።

ሰብዓዊ መብቶች የአገራችን መንግስትም ይሁን ስራውን የሚፈፅሙት አስፈፃሚ መስሪያ ዜቶች ስለፈለጉ ለዜጎች የሚሰጧቸው፣ ሳይፈልጉ ደግሞ የሚነፈጓቸው ሊሆኑ አይችሉም። ቀደም ሲል እንዳልኩት በአገራችን የነበረው ግጭት መነሻው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖር ነው። ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት ዜጎች ቢገደሉና የህሊና ቁስለት እንዲሁም አካላዊ ጉድለት ሰለባ ቢሆኑም ዛሬ እነዚያ ሁኔታ ሊደገሙ አይገባም። ህግ አስከባሪ ነው ተብሎ የሚታሰብ ተቋም ራሱ ህግን በመጣስ የዜጎችን መብቶች ሊደፈጥጥ አይችልም። እናም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የታየው የመብት ጥሰት ሁኔታ ገዥው ፓርቲ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች ውስጥም በመፈተሽ ህብረተሰቡም ይሁን አስፈጻሚው አካል እንዲማርበት ማድረግ ያስፈልጋል። መንግስትም በአሁኑ ሰዓት የያዘውና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያፍረጠረጠ በራሱ ሚዲያዎች እንዲቀርቡ እያደረገ ያለው የሚመሰገን ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።