በሠላም ተምሳሌቶቻችን ቅሬታ ላናይ …

መንግስት በሃገር ደረጃ ሰላም፣ ዲሞክራሲንና አንድነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የጀመረዉን የለዉጥ ጉዞ መሰረት በማድረግ እየተከተለ ያለዉ አዲስ የለዉጥ መንገድ ከፍቅር፣ ይቅርታና መደመር ጋር በማስተሳሰር በሃገር ዉስጥ ያሉ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚቋጩበትን አማራጭ በመከተል ዉጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

በዚሁም መሰረት በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት እና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አካላት መካከል ተፈጥሮ የነበረዉን አለመግባባት በገለልተኝነት የማደራደር መንግስታዊ ኃላፊነትን ከሁለቱ ቡድን ወኪሎች ጋር በተናጠልና በጋራ ባደረጋቸዉ ዉይይቶችና ምክክሮች የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች አፈቱሊላሂ ወይም ይቅር እንዲባባሉ ያስቻለ መድረክ መፍጠር ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸዉ ያለዉ ልዩነት በዘላቂነት ሰላማዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ከሁሉም የተወጣጡ ወኪሎችን ያካተተ መፍትሄ አፈላላጊ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡

መንግስት የተቋቋመዉ ይህ የጋራ ኮሚቴ የህዝበ ሙስሊሙን እዉነተኛ ችግሮች ለይቶ በማዉጣት ከዚህ ቀደም እንደነበረዉ በጠንካራ የወንድማማችነት መንፈስ በጋራ አብሮ በመቆም ለተጀመረዉ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ እና ለልማት መረጋገጥ የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ በፅኑ ያምናል፡፡

በተመሳሳይ በክርስትና ኃይማኖት የኦርቶዶክስ እምነት አባቶች መካከል ያለዉን ልዮነት በመንፈሳዊ ፀጋ በረከት በመመራት የለዉጥ መርሃችን ባደረግነዉ በፍቅር፣ በይቅር ባይነት እና በመደመር ሃገራዊ ሰላምና ብልፅግናን ወደ ሚያረጋግጥ ከፍታ ማድረስ የሚያስችል የእርቅ እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር የመሪነቱን ሚና በመዉሰድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ልኡካንም ተልከው በውይይት ላይ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አመራር እና የጋራ የእርቅ ኮሚቴ አባላት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር ጥልቅ የጋራ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ዘጠኝ አባላት ያሉትና ሁሉም የተስማሙበት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

የኮሚቴው አባላት ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ ከመጅሊስ የተወከሉ ሦስት ሰዎች ማለትም ሙፍቲ ሐጂ ዑመር፣ የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሐጂ ሙሐመድ አሚን እና ሐጂ ከድር፣ ከምሑራን እና ሽማግሌዎች ሦስት ሰዎች ማለትም ዶ/ር ኢድሪስ ሙሐመድ፣ ዶ/ር ሙሐመድ ሀቢብ እና ሼኽ ሙሐመድ ጀማል አጎናፍር ናቸው፡፡ 

አባል የሆኑት ሙፍቲ ሀጂ ኡመር በዚህ ዕለት በሁለቱ ወገኖች የተደረሰዉን ስምምነት አስመልክተዉ ሲገልፁ “ማንም ሰው እስከተደማመጠ እና እስከ ተቀራረበ ድረስ የማይፈታው ችግር የለም ካሉ በኋላ ይህ ጅምር ፍሬ አፍርቶ ሙሰሊም ክርስቲያኑ የሚደሰትበት ውጤት እንደሚያመጣ እምነቴ ነው” ብለዋል፡፡ ሌሎቹ የጋራ የእርቅ ኮሚቴው አባላት የሆኑት ሀጂ መሀመድ አሚን፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል እና ኡስታዝ አቡበከር አህመድም በበኩላቸዉ የተደረሰውን ስምምነት አስመልክተው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም የኮሚቴው አባላት በመፍትሄ አፈላላጊ የጋራ ኮሚቴው ደስተኛ መሆናቸውን እና ውጤት እንደሚያመጣም ሙሉ እምነታቸውን በመግለጽ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ አንድም ሰው ቢሆን ሰላም እስካልሆነ ድረስ ሁላችንም ሰላም ልንሆን አንችልም፡፡ በሀገራችን ሁለንተናዊ የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክሉት ሁለቱ ወገኖቻችን ከሚያራርቋቸው ነገሮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸው የጋራ ግቦች በመመልከት አብሮነታቸውን እስካላፀኑ ድረስ የሙስሊሙ ወገናችንም ሆነ የሀገራችን ሰላም በፍጹም ሙሉ ሊሆን አይችልም፤ ብለዋል፡፡ ሙስሊሙን ማህበረሰብ አገለግላለሁ የሚል መሪም አርአያ መሆን እንዳለበት እና ይቅር መባባል የኃይማኖቱም መሰረት እንደሆነ በመጥቀስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ቢጠነክር አንድ ቢሆን ለሀገርም ጥቅም እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ትልቅ አደራን የተቀበለው ኮሚቴው አደራውን እንደማይበላ አምናለው ብለዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር እና ይቅርታን በሚሰብክ እና የሰላም ቤት ነው በሚባል የእምነት ተቋም ውስጥ ደግሞ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ሰላም የግድ መኖር ያለበት ብቻ ሳይሆን ከኃይማኖታዊ ባህርይም በላይ የእምነት ተቋማት ተፈጥሮም ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት የሁለቱ ወገኖች ለመነጋገርና ችግሮቻቸውንም በሰላም ለመፍታት መስማማት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በተራዛሚውም የመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም ብስራት ነው፡፡