መገናኛ ብዙሃንና ሚዛናዊነት…

መገናኛ ብዙሃን ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን ቢኖራቸውም በተመልካቾች ዘንድ ግን በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች በተቀባዩ የእድሜ ወሰን እንዲሁም የትምህርት ደረጃ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም መገናኛ ብዙሃኑ ግን ስለሚያቀርቡት ነገር ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄና ክትትል ሊያደረጉ ይገባል፡፡

በዚህ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ መገናኛ ብዙሃን  ህዝብን ከህዝብ ባህልን ከባህል እንዲሁም ቡድንን ከቡድን እንደ ሰንሰለት ለማስተሳሰርም ሆነ ህዝብን ከህዝብ እንደ በሶ ለማበጣበጥ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ እናም ለሚያቀርቡት ለእያንዳንዱ መረጃ ትልቅ ትኩረት ጥንቃቄ ሊሰጡ ይገባል፡፡ ከምንም በፊት ሊሠሩበት የሚገባው ነገር በህዝቡ ዘንድ ታማኝነትና ተቀባይነት ማግኘት መሆን አለበት፡፡ የህዝቡን ስስ ብልት በመንካት መገናኛ ብዙሃን ማኅበረሰቡ ምን እንደሚያስፈልገውና እንደሚያሻው የህዝቡን የልብ ትርታ በማጥናትና በመዘገብ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡የሕዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥና መዘገብ ካልቻሉ ተደማጭነት ወይም ተነባቢነት በማጣት “በዋል ፈሰስ” ሆነው ይቀራሉ፡፡መገናኛ ብዙሃን ከመንግሥት ወደ ሕዝብ የሚተላለፈውን መልዕክት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡንም አስተያየትና ድምፅ ወደ መንግሥት በማስደመጥ ሚዛናዊ ዘገባዎችን የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት ሚዲያው በአብዛኛው የመንግሥትን ድምፅ የማስተጋባት የግል ሚዲያውም በተመሳሳይ መልኩ የግለሰቦችንና የተወሰኑ ቡድኖችን አስተያየት ብቻ በማስተናገድ ሚዛናዊ ዘገባን ለማቅረብ  ሲጥሩ እምብዛም አይታይም፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ  ሰው ለሚያምነው ነገር ተገዥ ነው እናም ዋጋም ይከፍላልና በፈጣን አቀራረብ ታማኝነት ላይ መሥራት ግዴታቸው ነው:: እነዚህ ተፅዕኖዎች ለተቀባዩ የእድሜ ደረጃ እንዲሁም የትምህርት ደረጃ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም መገናኛ ብዙሃኑ ግን ስለሚያቀርቡት ነገር ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄና ክትትል ሊያደረጉ ይገባል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ለማራመድ ምን ያህል ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዳላቸው ከምንም በፊት ማወቅ ይገባቸል፡፡የሚያመጧቸው መረጃዎች ከታማኝና ትክክለኛ ምንጮች ሊሆን እንደሚገባ ሙያው ያስገድዳል፡፡ ያ ካልሆነ ግን በዚህ ዘመን እንደ ድሮው የሚወዳደሩት ከጋዜጣ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ ጋር ሳይሆን ዘመናዊ ከሆነው (ከመረጃ መረብ) ኢንተርኔት ጋር ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ በፍጥነት መረጃ ማድረስ ካልቻሉ የመረጃ ድር በሰከንዶች ብቻ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ጋር ተደራሽ ስለሚሆኑ እነሱ የሚያቀረቡት ዜናም ሆነ ሌሎች ፕሮግራሞች ከዘመኑ ጋር ዕኩል መራመድ የሚችሉ አይደሉም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሕዝቡ መሃል ለሚፈጠረው ውዥንብር ከሁሉም አባላት በፊት ተጠያቂ የሚሆኑት መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ ሃሳብን በሃሳብ የመግለጽ ነጻነት በሚገለጽበት ሃገር ላይ እየሆነ ያለው ነገር ከዚህ በታቃራኒው ነው፡፡

በመንግሥት ፍላጎትም ይሁን በግለሰቦች አድርባይነት አንዳንድ ቦታዎች ለሚፈጠሩ ነገሮች የመገናኛ ብዙሃኑ ከሁሉም በፊት ትክክለኛ የሆነን መረጃ ለማኅበረሰቡ ማድረስ አለባቸው፡፡ ጊዜውን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ  ካልተቻለ ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች  የሚፈጠረውን ውዥንብር ለማስቀረት ምናልባትም ይረፍድብን ይሆናል ለተዘበራረቁት ነገሮች ፈጣን የሆነ የሆነ ማስተካከያ መንገድን መዘርጋትም ሊያቅተን የሚችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሳችን በፊት መገናኛ ብዙሃኑ በመረጃ መፍጠንም ሆነ መዘግየት ምክንያት ላለ መሆን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመዱ ግብኣትና ዕውቀት ከሚዲያ ባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ምንም እንኳን ሰው ሁሉ የየራሱ ዓይነት የሚመራበት ሕግ ቢኖረውም ሁሉንም ሰው በዕኩል ደረጃ ማስደሰት ባይቻልም ነገር ግን ብዙሃኑን ሰው ያማከለ የሆነ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ዘገባ እንዲሁም ፕሮግራሞች ሊያቀረቡ ይገባል፡፡

ባለፋት ጊዜያት በብዙ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲታይ የነበረው ትልቁ ችግር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለመንግሥት የሚያደሉ ነበሩ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ለሕዝቡም ይሁን ለመንግሥት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝን ነበር፡፡ በዋናነትም መንግሥት ያጠፋቸውን ጥፋቶች የሰራቸውን ስህተቶች ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ የማሻሻል እድሉን አሳጥተውታል፡፡ እነዚሀ ነገሮች በተደጋገሙ ቁጥር ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ መሃል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ይፈጠራል መንግሥት የሚያወራው ለሕዝቡ የማይገባ ይሆናል፡፡

ሌላው ደግሞ ሚዲያው ከሁሉም ነገር የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ፡- ከሐይማኖት፣ ከዘር፣ ከብሔር ከመሳሰሉት ነገሮች መቃቃርና ሽኩቻ ቡከትና ብጥብጥ የራቀ  ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለማድረስ ጥረት ካላደረጉ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለሚኖረው እያንዳንዱ አሉታዊ ግንኙነት ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በስህተት እንኳን ስለ አንድ ሕዝብ ወይም ሃይማኖት ማለት የሌለባቸውን ነገር ካሉ ብዙ የሚበላሽ ነገር አለ፡፡ ሚዲያ ማለት፡- በአንድ ሀገር ውስጥ (ከሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ ) ቀጥሎ እንደ አራተኛ መንግሥት የሚቆጠር  ማለት ነው፡፡  ስለዚህ ይህንን በማወቅ ለሚያቀርቡት ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት ሊሰጡበትና ጥንቃቄ ሊያደረጉ ይገባል፡፡