ሠላም!… ሠላም!… ሠላም!…

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እየተከሰተ የሚገኘዉ ግጭት ዘላቂ መፍትሄን የሚሻ ነዉ:: በተለይም ዘርን እና ሀይማኖትን መሰረት አድርገዉ የሚነሱ ግጭቶች መብረጃ የላቸዉም:: አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ሰላም ለማደናቀፍ ተግተዉ የሚሰሩት የሀገር ባላንጣዎችም ቢሆኑ ዘርን እና ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭት የሚያስነሱት ግጭቱ ሀገሪቱን ወደለየለት አዘቅት ዉስጥ ለመክተት ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው::

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚተላለፉት አንዳንድ መልእክቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከእዉነት ያፈነገጡ ናቸው:: ማንነታቸዉ በግልፅ ያልታወቁ ሰዎች አሁን እየፈነጠቀ ያለዉን የሰላም ወጋገን ለማደፍረሰ በተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ምንም የማያዉቀዉን የዋህ ህዝብ መጠቀሚያ በማድረግ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የእኩይ ዓላማቸዉ ማሳኪያ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ::  እነዚህ ማንነታቸዉ በዉል ባለታወቀ ሀይሎች በሚነዙት ወሬ ምክንያት ክብር የሆነዉ የሰዉ ልጅ ህይወት ጠፍቷል:: ብዙዎች የቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ሰለባም መሆናቸዉ ይታወቃል::  በየቦታዉ የሚታዩት እነዚህ ችግሮችን በንግግር መፍታት እየተቻለ ነገሮችን ወደ ሀይል ሆን ተብሎ ይቀየራሉ:: ጥፋትም ሆነ ጥሩነት ግለሰባዊ እንጂ ሀገራዊ መሆን የለበትም::

ግጭቱን የሚቆሰቁሱት የተያያዝነዉ የፍቅር እና የአንድነት የመደመር ጉዞ እንዲደናቀፍ እና ህዝቦች እርስ በእርስ አንዲናቆሩ የሚፈልጉ ጥቂት ሰዎችን በገንዘብ በመግዛት ችግሮች እንዲፈጥሩ እና የሚፈጠረዉ ችግርም ህዝብ ለህዝብ ለማስመሰል እንደሚጥሩ እስካሁን የተፈጠሩት ችግሮች ማሳያ ናቸዉ::

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዳሉት ሁሌም ሟች ደሀዉ ማህበረሰብ ነዉ:: ብዙ መስራት ሚጠበቅበት ነገ ሀገር ይረከባል የተባለ ወጣት ነዉ:: በሚዲያም  በኩል ቢሆን የሚዲያዉ ነፃነት ታፍኖ እንደነበር የሚያሳዩ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ሲነሱ መኖራቸው የአደባባይ ሚሰጥር  ነዉ:: ታፍኖ የኖረ ሜዳዉም ፈረሱም ያዉ በነፃነት ማዉራት ትችላለህ ሲባል ያለፈዉን ስርዓት ከመተቸት በዘለለ ለህዝቡ የሚገባዉን መረጃ በተገቢዉ ሰዓት እንዲያደርስ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ እየተጠቀመበት አይደለም:: ገፍቶ የመሄድ ችግር እየተመለከትን ነዉ፡፡ ለአብነት ያህል የሰኔ 16ቱን ጥቃት ብናነሳ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ እስኪረጋጋ ድረስ ያለዉን ሁኔታ ሚዲያዎች ሲዘግቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የተደረሰበትን የምርመራ ዉጤት ተከታትሎ ለህዝብ ማድረስ በዋነኛነት የሚዲያዉ ተግባር ቢሆንም ይህ ሲደረግ እስከአሁን አላስተዋልንም:: ሚዲያዉ በህብረተሰቡን ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ ብዙ መስራት እየቻለ ይህን ማድረግ አልቻለም:: ይልቁኑ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ህዝቡን ወደ ለየለት ብጥብጥ እና ሁከት ዉስጥ የመክተት ሥራዎች ይታያሉ::

ምንም እንኳን ነገሮችን በንግግር የመፍታት ባህላችን ገና እንጭጭ ቢሆንም እኛ እንደ አውሮፓውያን ወይም አሜሪካ በብዙ ነገሮች የግለኝነት ኑሮን የምናዘወትር ህዝቦች ሳንሆን የየዕለት ተግባራችን አንዳችን ከሌላችን ያለን ግንኙነት እንዳይቋረጥ ሆኖ የተሰናሰለ                                          የክርስቲያኑን የአንገት ክር ከሙስሊም ጓደኛው ጋር አበሮ የገመደ የሙስሊም ኮፍያውን ከክርስቲያን ዘመዱ ጋር  ሆኖ የሚሰፋ ማህበረሰብ ነው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ህይወት ሙሉ አይሆንም፤ እናም በዚህ ፍቅር መካከል ማንም የጥፋት ተልእኮውን አንግቦ መግባት አይችልም::

ፍቅር ፍቅር እያሉ ሲሰብኩን ለነበሩት መሪያችን ለወታደሮች ፀጥታን እንዲያስከብሩ መዉሰድ ያለባቸዉን እርምጃ ወታደሮች እንዲወስዱ መመሪያ መስጠት  ቀላል ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ህዝብ ላይ እየደረሰ ካለዉ የግፍ ግድያ በስተጀርባ ያሉትን ሃሰተኞች በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲባል የግድ መደረግ የነበረበት ትክክለኛ እርምጃ ነዉ፡፡ በዚሁ አቁዋም ከቀጠሉም አሁን ባለንበት ሁኔታ በግፍ እየሞቱ ያሉ ሰዎችን ደም ማስቀረት እንኩዋን ባንችል ከግፈኞች ስም ዝርዝር እራሳችንን  መቀነስ  እንችላለን:፡