የሠላም ትሩፋቶች…!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ትላልቅ ክስተቶች ተስተናግደዋል፡፡ የመጀመሪያው በቋፍ የነበረው የአገሪቱ ሰላም ወደነበረበት የተረጋጋ ሁኔታ መመለስ ነው፡፡ አገራችን የሚትገኝበት ቀጣና አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት የማይታይበት ለዓመታት የዘለቀ የእርስ በርስና በአጎራባች አገራት መካከል መቋጫ የሌለው ጦርነት የነበረበት አስጊ ቀጣና እንደሆነ ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ሲታይ ለአብነት ያህል ሶማሊያ ለዓመታት የአሸባሪዎች መናኸርያ ከመሆኗም ባሻገር ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሳይኖራት ዘልቃለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በእርስ በርስ ግጭት የምትታመስ እስካሁን ድረስ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ያለች አገር ስትሆን  ኢትዮጵያም  ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ደም አፋሳሽ የድንበር ግጭት ምክንያት ሞት አልባ ጦርነት ላይ የነበረች በመሆኑ አጠቃላይ ቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የራቀው እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

አገሪቱን የመበታተን ጫፍ ላይ አድርሰዋት የቆዩ የተጠራቀሙ ችግሮች እንዲፈቱ እንዲሁም፤ ህዝብን ለምሬት የዳረጉ ብሶቶች እንዲቀንሱ በቁርጠኛ አመራራቸው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ተስፋ ሰጪው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዳይመለስ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል፤ ተግብረዋል፡፡ በመልካም አንደበታቸው ለመላው ህዝብ ተስፋንና ብሩህ ዘመናትን አመላክተዋል፡፡ በይቅር ባይነት መጥፎ ጠባሳ የሚሻር መሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ  የውስጥ ሠላሟን ባረጋገጠች ቁጥር  ከቀጣናዊ መረጋጋት የሚገኘውን ትሩፋት ለማጣጣም ይቻል ዘንድ የድርሻዋን ማበርከት አለባት፡፡ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባለፉት ወራት ሰላምን ለማረጋገጥ ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት  አገራችንን  ለማረጋጋት  ጉልህ ፋይዳ እንዳለው እሙን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰላምን በህዝብ ለማስረጽና ጥላቻን ለማስወገድ ባደረጉት ዘመቻ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ከህዝብ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በጅግጅጋ፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ባሌ፣ ደንቢዶሎ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤና አፋር ከተሞች የሠላም መልእክት አንግበው ኅብረተሰቡን አወያይተዋል፡፡

በተደረገው ጥረት አሁን በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሠላም ቢሰፍንም፤ በተለያዩ ስፍራዎች ብሄርን መሰረት አድርገው የሚታዩ ግጭቶች ሙሉ ለሙሉ አልቆሙም፡፡ የተጀመረው ለውጥ ሙሉ እርካታን ያጎናጽፍ ዘንድ ችግሮችን ከምንጫቸው በመፈተሽ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡  ይህ በሚዛኑ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ለውጥ ያስፈልጋል መልካም አስተዳደርና ፍትህ መስፈን አለበት በሚል መንፈስ በተለያየ መንገድ ሀሳባቸውን ሲገልጹና ሲታገሉ የቆዩት የእነርሱ መብት ተከብሮ የሌሎች እንዲጣስ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡

በአገራችን ብሎም በቀጠናችን ሰላም በተገቢው መልክ ይሰፍን ዘንድ   ይቅርታ ማድረግ ይቀድማል፡፡ ይቅርታ ማድረግ ደግሞ ለፍቅር ትልቅ ድልድይ ነው፡፡ ይቅርታ በማድረግ ፍቅርን እውን ማድረግ ያሻል፡፡

መደመር ያለ ዘር ልዩነት በአንድ ላይ በመቆም የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ማድረግ ነውና በየስፍራው የሚንጸባረቀው የልዩነት ግንብ ሊፈርስ ይገባል፡፡ አንድነታችንን አጠናክረን አገራችን ካለችበት የድህነት ማጥ ሊናላቅቃት ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ ይህንን ማድረግ ስንችል ቀጣናው ላይ የሚኖረን ተጽእኖ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በቅርብም በሩቅም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር ወደ ሆኑ አገሮች አቅንተው በጋራ ጉዳዮች ላይ በተለይም ደግሞ በሰላምና በኢኮኖሚ ትብብር ላይ ከአቻዎቻቸው ጋር በመነጋገር የተለያዩ የትብብር ፓኬጆች እንዲፈረሙና በተግባር ላይ እንዲውሉ የተደረገው፡፡

ከጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳና ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያና ዩናይትድ ዓረብ ኢሜሬቶችን ጎብኝተዋል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የሞት አልባ ጦርነት ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም ለዓመታት ተራርቀው የኖሩትን ህዝቦች ለማቀራረብ፣ መልካም ጉርብትና የሚያስገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነው፡፡

በወደብና በየብስ የሚደረገው ግንኙነት የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች በጋራ ለማደግና ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ከምንም በላይ አገሪቱ ሰላሟ የተረጋገጠ እንዲሆን በጸጥታ ረገድ የሚያበረክተው ሚና ጉልህ በመሆኑ በተጀመረው ልክ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

 

ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ውበት የመሆን ሞገሱን አጥቶ፣ አካባቢያዊ ማንነት ነግሦ፣ ዜጋው  በገዛ አገሩ መድረሻ ቸግሮት እያየን ከንፈር ከመምጠጥ ባሻገር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ጥቂት እንኳ ባልተሞከረበት ሁኔታ መለያየታችንን ወደለየለት ደረጃ ሊያደርሰው ተቃርቦ እንደነበር

ይታወሳል፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያንገበገባቸው የለውጥ ኃይሎች ያነሱት ተቃውሞና የችግሩ ግዝፈት መንግሥትን አሳስቦት እርሱ እራሱ የችግሩ አካል እንደሆነ በመረዳት የእርምት እርምጃ በመውሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ወደ ሥልጣን በማሸጋገር በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ዕርምጃ ወስዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መድረኮችና ክልሎች ስለሰላምና ፍቅር ዋጋ የሚሰጣቸውን ምርጥ ቃላት ቢያዘንቡም፣ ሰላም ለማስፈን ቢተጉም፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን ቢያነጋግሩም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚፈለገው ሰላም እየራቀ ግጭቶች እያገረሹ፣ ነዋሪዎች ከየቀዬአቸው እየተሰደዱና የመኖር ተስፋቸው እየመነመነ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አንድነትና ስለ አብሮ መኖር አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተፈቃቅረው ፣ተሳስበውና ተዛዝነው ሊኖሩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የውጭ አገራት ሳይቀር ኢትዮጵያውያንን አስጠልለው ባሉበት ሁኔታ ዜጎች በአገራቸው ከመኖሪያ ስፍራቸው ሊፈናቀሉ እንደማይገባ አስተዛዝነው አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮች አሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ፣በደቡብ ክልል በጌዴኦ የተከሰተው ግጭት ብዙዎችን ለዕልቂት ዳርጎ ብዙ ሺዎችን አፈናቅሏል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዜጎችን ከማፈናቀል አልፎ የተፈጸመው ግድያ፣ በደቡብ ወሎ በከሚሴና በባቲ የተፈጸሙ አሳዛኝ ድርጊቶች በቀላሉ የሚታዩ እንዳልሆኑ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይም ባለፉት ጊዜያት ዴሞክራሲ ተነፈግን፣ መብታችን ተረገጠ፣ታፈንን ፣ በሚል ከአገር  በመሰደድ ከቃላት ትግል አልፎ የጦር መሳሪያ አንስተናል ሲሉ የነበሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገ የሰላም ጥሪ  በነፃነት ወደ አገር ቤት ገብተው እንዲታገሉ እድሉ ክፍት ሆኗል፡፡ ይህንን ተጠቅመው ወደ አገር ቤት የገቡም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ወገኖቹን የሚጠላበት ምክንያትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሕዝብን ከሕዝብ ለማቆራረጥ በጥፍራቸው የቆሙ የሰላም ጠንቆች፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያተራምሱ፣ ተንኮልና መርዝ የሚረጩትን ሕብረተሰቡ ሊያዳምጣቸው አይገባም፡፡ ሕዝብን አንዴ ማታለል ቢቻልም፣ ደጋግሞ ለማታለል መሞከር ግን ሞኝነት በመሆኑ አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡

 

እስካሁን ድረስ በተደረገው ጥረት ሰላምን ማረጋገጥ የተቻለበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መነሳሻ ነው፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግም ሆነ ድህነትን ታሪክ ማድረግ የሚቻለው ሰላምን ማረጋገጥ ሲቻል ነው፡ የሰላም ቱርፋቶች ፈርጀ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በመሰረታዊነት የሚጠቀሰው ደግሞ የኢኮኖሚ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ካለችበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ግንባር ቀደም ኃላፊነት ቢኖርባቸውም በአስተዋይነት መንፈስ ድጋፍ ሊያደርግላቸው የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ  ነው፡፡  ህዝቡ ይህንን ለውጥ ዳር ለማድረስና ከሰላም የሚገኘውን ውጤት ባግባቡ ለመጠቀም ቱርፋቱንም ለማጣጣም ይችል ዘንድ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል፡፡