ከንቱ ጥረቶች

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ብቅ ጥልቅ የሚሉ ግጭቶችን እየተመለከትን ነው። እነዚህ ግጭቶች በህዝቡና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ግጭት አለ’ ለማስባል እንዲሁም ህዝቦችን ወደ ሃይማኖት ግጭት ውስጥ ለመክተት ያለሙ ከንቱ ጥረቶች ናቸው።

ሆኖም አንድነትና ኢትጵያዊነት እየተዘመረ ባለባት ሀገር ውስጥ የብሔርም ይሁን የሃይማኖት ግጭት ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። የእነዚህ ድብቅ ሴራዎችና ከንቱ ጥረቶች ተዋንያን ጥቅማቸው የተነካባቸው አንዳንድ አካላት መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል። እነዚህ ‘በልተው ሊያባሉን’ የሚፈልጉ አካላት ግጭቶችን ከፈጠሩ በኋላ፣ መልሰው በየማህበራዊ ሚዲያው የግጭቶቹን መነሻዎች ብሔርና ሃይማኖት በማስመሰል እየጣሩ ነው። ይህ ፈፅሞ ነጭ ውሸት ነው።

እዚህ ሀገር ውስጥ የብሔርም ይሁን የሃይማኖት እኩልነት ተከብሯል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ብሔሮች ኢትዮጵያዊነትን በጋራ ለማጠናከር እጅ ለእጅ ተያይዘው በመጓዝ ላይ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “አንድነት አንድ አይነትነት ማለት አይደለም” ባሉት መሰረት ሁሉም ብሔሮች ለአስተዳደር እንዲያመች የተበጀላቸውን ወሰን ጠብቀው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በጠነከረ ሁኔታ መሰባሰብ ጀምረዋል።

የሀገራችን ህዝቦች በኢትዮጵያዊ አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ችግሮች ካሉም በውይይትና በመግባባት የሚፈጥሩበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ይህም ባለፉት አራት ወራት እውን ሆኗል። የኢትዮጵያ እድገትና ስልጣኔ ላይ እንዲረባረቡ የሚያስችላቸው ምህዳርም ተፈጥሮላቸዋል። ይህ ዓይነቱ አዲስ ግንኙነት ኢትዮጵያን በተጠናከረ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ጠንካራ ጉልበት እየሆነ ነው።

የጋራ አስተዳደር የተፈጠረበት አንዱ መነሻ ምክንያት ሁሉም ማንነቶች የሚወዷት ኢትዮጵያ ባለቤቶች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ይህ ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቶ ሁሉም ብሔሮች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ባለሉበት በዚህ ወቅት ግጭት ቀስቃሶች የሚፈጥሯቸውን ችግሮች ወደ ብሔር ግጭት ማዞር የሚችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

ለምሳሌ ያህል ባሌ ጎባ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ጊዜያዊ ግጭት ብንመለከት፤ ‘በልተው ሊያባሉን’ የሚከጅሉ የቀን ጅቦች ጉዳዩን የብሔር ግጭት አስመስለው ለማራገብ ቢሞክሩም ሰሚ አልነበራቸውም። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብሔሮች የሚያስቡት በተናጠል ሳይሆን በጋራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ስኜት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ሁሉም ብሔሮች ተደምረዋል። ድምር ውጤታቸው አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአንድነት ማገር ማቆም ነው። ይህ አንድነት መከበሪያቸው መሆኑን በሚገባ ይገነዘባሉ። አንድ ሲሆኑ በጋራ እንደሚያድጉ፣ የሌላ ሀገር ዜጋ ሳይቀር ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚያከብራቸው ከተረዱ ቆይተዋል። እናም ይህ ሁኔታ ባለበት ሀገር ውስጥ የብሔር ግጭትን አነሳለሁ ብሎ ማሰብ ዘላቂነት የሌለው ከንቱ ጥረት ነው። 

በአሁኑ ወቅት ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊና ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት በሀገሪቱ በነጻነት ተንቀሳቅሰው በመስራት ህይወታቸውን የሚለውጥ ሃብት የማፍራት እንዲሁም ከሀገሪቱ ሃብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታቸውን እንዲጠቀሙ አዲሱ አመራር ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው።

አገሪቱ የምትመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሚመነጩት የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎቶች ለማሟላት በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግስት እንቅስቃሴ ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው። የመንግሥት ሥልጣን፣ መንግሥት የሚያራምዳቸው እምነቶች፣ የሚከተላቸው መርሆዎችና ፖሊሲዎች ምንጭ የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው።

መንግሥት በተለይ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ ይህን እውነታ ለማሳካት ተንቀሳቅሷል። ህዝብን የሚጠቅሙ ውይይቶች እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን ጋር በጠላትነት የመተያየት አጀንዳን በመስበር በፍቅርና በሰላም በአንድነት እንድንኖር ማድረግ ችሏል። ይህ  ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት ሀገር ውስጥ አንዱን ከአንዱ በመለየት ለማጋጨት የሚደረግ ጥረት የከንቱዎች ሁሉ ከንቱ ነው። ‘በልተው ሊያባሉን’ የሚከጅሉ ጥቂት ሃይሎች ግጭቶች ለማጎን ሃይማኖትንም በአጀንዳነት ሊጠቀሙ ሲፈልጉ ይስተዋላል። ይህም ከንቱ ጥረት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በባላንጣነት የሚተያይ ሃይማኖት የለም። ሁሉም በየእምነቱ ተቻችሎና ተከባብሮ አምልኮውን እያካሄደ ነው።

 ሃይማኖታዊ ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገም ነው። ከመሰንበቻው ዶክተር አብይ አህመድ የእስልምናንና የኦርቶዶክስ እምነት አባቶችን በማነጋገር የፈፀሟቸው ገድሎች የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ነው። ይህ እየሆነበት ባለበት ሀገር ውስጥ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ማሰብ እንደ ‘ላም አለኝ በሰማይ…’ ዓይነት ነገር ከማሰብ የሚተናነስ አይደለም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሃይማኖት እኩል ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የእምነት ነፃነትና የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጧል። መንግስትና ሃይማኖትም ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግለሰቦች የራሳቸውን የእምነት ነፃነት ለማስከበር በማሰብ ‘የእኔ እምነት ትክክል ስለሆነ እኔን ብቻ ተከተለኝ’ በማለት ማስገደድ እይችሉም። ምክንያቱም ሌላውም ዜጋ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ያሻውን እምነት መያዝ ስለሚችል ነው። ይህ ሁኔታ በተረጋገጠበት ሀገር ውስጥ ጊዜያዊ ግጭቶችን በሃይማኖት ሰበብ አድርጎ ለማቅረብ መፈለግ ከንቱ ቅዠት ነው።

እንደሚታወቀው አንድ ግለሰብ የእምነት ነፃነቱ የሚከበርለት፣ የሌላው ግለሰብ አምልኮአዊ ነፃነት በሚከበርበት ማዕቀፍ ውስጥ ነው። የግለሰብ መብቶች ሲከበሩ በተነፃፃሪ የብዙሃን መብቶችም ለሊከበሩ ይችላሉ። ስለሆነም የሁሉም ዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ገቢራዊ የሚሆነው፣ አዲሱ አመራር በሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ካለው ፍላጎት አኳያ ነው።

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ዶክተር አብይ በሃይማኖት ውሰጣዊ ጉዳዩች ሳይገቡ በእምነቱ አባቶች ጥያቄ መሰረት እንደ መሪ ቅራኔዎችን ለመፍታት ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ ነበሩ። ይህን መሰል ውጤት እየተገኘ ባለበት ሀገር ውስጥ ሃይማኖትን አስታክኮ ግጭት ለማስነሳት መሞከር በከንቱ መልፋት ነው።

እንደ እኛ ባሉ በዴሞክራሲያዊ ሀገራት ውስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። አንዱ ከሌላኛው አይበላለጥም። የሚፈፅሟቸው ማናቸውም ጉዳዩች የበላይም የበታችም ሊሆኑ አይችሉም። ማንኛውም ዜጋ የሚከተለው እምነት ሳቢያ ከሌላው ዜጋ ሊበልጥም ሆነ ሊያንስ አይችልም። ይህም እንደ እኛ ባለው ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሀገር ውስጥ ሁሉም እምነቶች እኩል ስለ መሆናቸው አስረጅ ነው።

ርግጥ አንዱ ሃይማኖት ያለው መብት ሌሎችም ሃይማኖቶች አላቸው። የእምኩልነታቸው መሰረት የሚመነጨው ኢትዮጵያ ከምትከተለው የዴሞክራሲ ስርዓት የእኩልነት መርህ በመነሳት ነው። ይህ እኩልነት ባለበት ሀገር ውስጥ በሃይማኖት ሰበብ አስባብ ግጭትን ማጫር አይቻልም። ግጭትን ማጫር በማይቻልበት ሁኔታም የሌለ ነባራዊ ሁኔታን መመኘት “ላም አለኝ በሰማይ…” ከመሆን የሚዘል አይደለም። ያም ሆነ ይህ ግት ናፋቂዎችን ህብረተሰቡ ሊገታቸው ይገባል። ማንነታቸውን በመገንዘብም በውስጡም ይሁን በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያስተላልፏቸውን ከንቱ ጥረቶች ተረድቶ በሳል ውሳኔ መውሰድ አለበት።