ተቋማዊ ዝግጁነት፤ለለውጡ ስኬት

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ አገራዊ አቅምና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ፈርጀ-ብዙ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በአገሪቱ እየተተገበሩ የሚገኙት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም በአንድ በኩል አገሪቷን ከፍጹም ድህነት ወደ ተሻለ ብልፅግና በሚያሸጋግሩ የረጅም ጊዜ ጥረቶች ላይ ሲያተኩሩ፣ በሌላ በኩል ጊዜ በማይሰጡ በምግብ ራስን የመቻልና በየደረጃው ፍትሃዊ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ግቦች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸው በተለያዩ መንግስታዊ ሰነዶች ተመልክቷል፡፡

የዘርፉ ጠበብቶችም ሆኑ መንግስታዊ ሰነዶቹ እንደሚያረጋግጡት አጠቃላይ አገራዊ አቅምና ለተጽዕኖዎች የማይበገር የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ስኬት ጫፍ በሚያመሩ የመዋቅራዊ ለውጥ ሂደቶች እየተፈተነ ማለፍ አለበት፡፡ ይህ የመዋቅራዊ ለውጥ ሽግግርም በግብዓት፣ በሂደትና፣ በውጤት የሚገለጽ ሲሆን በየደረጃው የሚደረጉ ጥረቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች የመዋቅራዊ ሽግግሩን ፍጥነት በእጅጉ ይወስናሉ፡፡

ኢትዮጵያ የእድገቷን አቅጣጫ በቅጡ የሚያመላክት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመንደፍ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅር ለውጥ መትጋት ከጀመረች ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ወቅት የሂደቱን አቅጣጫ ርትዑነት አመላካች ከሆኑት ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ክስተቶች መካከል የተመዘገቡት ከፍተኛ የቁሳዊና ሰብዓዊ ካፒታል ክምችት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት በስኬትነት የሚፈረጁ ናቸው፡፡  

የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ስኬት ከሚለካባቸው ክስተቶች አንዱና ዋናው፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ግብአቶችን በተለይም የሰው ኃይልንና ቁሳዊ ካፒታልን ከመጠቀምና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካላቸው አስተዋጽዖ አንጻር በባህሪያቸው ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ ምርታማነት ወዳላቸው ዘርፎች መሸጋገር መቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ክንዋኔ ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ እንደ መደላድል ተቆጥሮ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ መወሰዱ በሰነዶቹ ላይ ተመልክቷል፡፡ በተለይም ከአገሮች የረጅም ዘመን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ልምድ በመነሳት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅሯን ከግብርና ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ለማሸጋገርና፣ እንዲሁም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጥ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል እቅድ ነድፋለች፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትና የወጪ ንግድ መስፋፋት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ወቅት ከፍተኛ ክትትል ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ መሆናቸው ተመልክቷልና ያለፉትን ሶስት አመታት መቃኘት ተገቢ ነው፡፡ የሁለተኛው ዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የሁለት ዓመት ተኩል አፈፃፀም በተመለከተ በቅርቡ የተካሄደው ግምገማ እንደሚያመለክተው የወጭ ንግድ ተቀዛቅዟል፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣም፣ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች አሁንም ስር እንደሰደዱ ነው። 

የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም መንግስትና ገዥው ፖርቲ በየወቅቱ የተለያዩ ዕቅዶች በማዘጋጀትና ስልቶችን በመንደፍ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ጥረቶች የመጡ ከአካባቢ አካባቢ የሚለያዩ የተሻሻሉ ጉዳዩች እንደተጠበቁ ሆኖ አሁንም በፌዴራልም ሆነ በክልል ተቋማት የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር እየገነገነ መሆኑን ግምገማው አመላክቷል።

 

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ዕቅድ ላይ በተካሄዱ ውይይቶች ወቅት ከሞላ ጐደል በአብዛኛዎቹ መድረኮች የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በጣም ያወያየ፣ ለዕቅዱ መሳካት እንቅፋት ይሆናል ተብሎ በስጋት መልክም የቀረበ፣ እውነት ትፈታላችሁ ወይ? የተባለ እና በብዙ መልኩ በሚገለጽ አግባብ ጐልቶ የወጣ ጥያቄ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም በችግሩ መኖር ላይ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም፡፡ አመራሩ የችግሩን መኖር ያውቀዋል ወይ? ከተባለም ይህ የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም፡፡ ግን ደግሞ  አመራሩ የዛሬ 3 አመት ያወቃቸውን የገመገማቸውን እና ህዝብ የነገረውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በብቃት እየፈታ ነው ወይ ከተባለ በርካታ ችግሮች አሁንም እንደተከመሩ ስለመሆኑ ግምገማው ባያመላክትም እንኳ የህዝቡ የለት ተለት ወሬ በቂ ምስክር ነው፡፡ የእቅዱ ቁልፍ ትኩረት ወደሆነው ሌላኛው ዘርፍ ስናመራ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ እናገኘዋልን።  

 

የኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንቨስትመንት ወጪ ስለሚያስፈልገው አገራዊ የፋይናንስ አቅምን መፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማጎልበት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል ወደ አምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ሽግግር ወደ አዲስ ኢኮኖሚያዊ ባህል የመግባት ያህል በመሆኑ ተቋማዊ ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ቁልፍ ጉዳዮች ፈር ለማስያዝ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተለያዩ የማስቻያ ስልቶችን የነደፈ ስለመሆኑ በሰነዱ ቢመለከትም ይህም ባለፉት ሶስት አመታት መራመድ ያልቻለ እንደሆነ ግምገማው አመላክቷል፡፡

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው ፈታኝ የሽግግር ሂደት ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው መስኮች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የግብርና ልማት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት፣ የግብርናና የአምራች ኢንዱስትሪ ትስስር፣ የተመጣጠነ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት፣ የኤክስፖርት ልማት፣ የከተማ ልማት፣ የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የአረንጓዴ ልማት ግንባታ፣ እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ልዩ የትኩረት መስኮች ሆነውም ተመልክተዋል፡፡  

የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋና ግብ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2017 አገሪቱን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ማድረስና ለዚህ የሚመጥን አጠቃላይ አገራዊ አቅም መገንባት ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ዋና የፖሊሲ ግቦችም ይህንኑ ራዕይ ከማሳካት አንፃር የተቃኙ መሆናቸው የተሰመረበት ቢሆንም ይህም ውጤታማ መንገድ ላይ አይገኝም፡፡  ስለዚህ ምን ይሻላል የሚለው ሊያነጋግረን ቢገባ ሊገርም የማይገባና ይልቁንም የመደመርን ወቅታዊ ሁኔታ ከግቡ ለማድረስ የሚጠቅም ይሆናል። ይህን በተመለከተ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማዞሩ አዲስ ውጥን ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ይጠበቃል። የመልካም አስተዳደሩን የተመለከተው ግን ሰፊ ስራ ይጠይቃል።

ከፍተኛ መጠን ባለው ሃብት ላይ እየወሰነ ያለው አመራር፣ ውሳኔው ንፁህ ሕዝባዊነትና ሃገራዊ ዕድገት ላይ ካልተመሠረተ፣ የሌብነት አረንቋ ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል እየተባለ ሲወተወት የነበረው ስጋት እንዲህ በተጨባጭ ሲከሰት ማየቱ የሚቀጥልና ፈጣን መላ ካልመጣለት በገዛ ሃገር ላይ ባይተዋርነትን ስለሚፈጥር  እርስ በእርስ የሚያናጭ እና ብሶተኛው ሁሉ ህገወጥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እና በተነሱ ግርግሮች ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

 

እንዲህ አይነቱ ከድርጅቱ ውጪ ካለ የሌቦች ሃይል ጋር አብሮ በመጠቃቀም ሲወሰን የሚውለው አመራር ቁጥር ከፍ ባለ መጠን ሃገር የመፍረስ አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህ ይህንን አዝማሚያ በአስቸኳይ ማቆም የግድና የሕልውናም ጉዳይ ነው፡፡

 

መንግስት ይህንን ተገንዝቦ በአዲስ የለውጥ እንቅስቃሴና ትንቅንቅ ላይ ቢገኝም እና በዚህም የለውጥ ብልጭታዎች በውስን ዘርፎች እና አካባቢዎች ላይ እየታየ ቢሆንም ትንቅንቁ ቀላል የሆነለት አይመስልም፡፡ ጥቅመኛው ሃይል በፈጠረው የጥቅም ሰንሰለት የፀረ-ሌብነት ዘመቻውን ለማኮላሸት የሚችለውን ሁሉ ያደረጋል፣ እያደረገም ነው። በተቻለው ሁሉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የዘመቻውን የመከላከያ አጥር ሲያጠብቅና ማኮላሻ መንገድ ሲጠርግ  ውሎ እያደረ  መሆኑን የሚያመላክቱ ፍንጮችም በስፋት እየተስተዋለ ነው። ይህ ደግሞ የድርጅትን መዋቅር ጭምር ተጠቅሞ የፀረ- ሌብነት ሀይሉን እና ዘመቻውን ለማደናቀፍ እየተረባረበ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ሃብት ያካበተ ሃይል እንደመሆኑ፣ በገንዘቡ በመደለል እየመጣበት ያለውን ዘመቻ ለማምከን በሚተጋው ልክ ጤናማው ዜጋ እስካልተጋ ድረስ ይልቁንም ጥቅመኛው በቀደደው ቦይ መፍሰሱን እስካላቆመ ድረስ ችግሩ ወደ በለጠ መወሳሰብና ሃገር ወደ ማፍረስ ማቅናቱ አይቀሬ ይሆናል።

 

ይህ ሃይል የሌብነት መረቡን ከውስጥ እስከ ውጭ በመዘርጋት የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻውን የሚያደናቅፉ፣ ትኩረትን የሚሻሙ ፣ ሃይልን የሚቀንሱ ተግባራትን በዚህም በዚያም በመፈጸም የተካነ መሆኑን የመደመር ፊሽካው ከተነፋ ማግስት ጀምሮ በሚገባ እያሳየን መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡የተዘጋ አጀንዳ እየከፈተ፣ የሌለ አጀንዳ እየፈጠረ ሕዝብን ለትርምስና ለሁከት ለመጋበዝ የሚጣጣረውም እሱ ነው። በመሆኑም የዚህን ሀይል እንቅስቃሴ በሁሉም አቅጣጫ መገደብና በሁሉም አማራጭ መዝጋት የጊዜው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ የመጀመሪያውና ቀዳሚው ተግባር መንግስትና ሕዝብ ተባብረው የሌብነት ሃይሉን ራስን የመከላከል ስልቶችና ማምታታቶች አውቀው መገደብ ነው። ራሱን ለመከላከል ሲል ሊፈጥረው የሚሞክረውን ትርምስ  ምክንያት ተገንዝበው ዓላማውን ማክሸፍ ነው የወቅቱ ጥያቄ፡፡ ቀጥሎም በተመሳሳይ ትብብር ይህን ሃይልና መረቡን የማጋለጥ ተከታታይና የማያባራ ዘመቻ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ከሕዝብ የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ሕዝብ ሁሉንም ገልጦና ገላልጦ ማሳየት አለበት፡፡ በየስርቻው ሀብት ያካበተውን በዘመድ አዝማድ ስም ሀብት ያከማቸውን በመጠቃቀምና በጎሰኝነት የተከለለውን ከየጎሬው እያወጣ ማጋለጥ ከህዝቡ የሚጠበቅ ሃላፊነትና ግዴታ ነው ፡፡ ይህንን ንቅናቄ መንግስት ያለአንዳች መዘናጋት መምራት አለበት፡፡ ከህዝብ በሚያገኘው መረጃ እና በራሱም የተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮች የሚያገኛቸው መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ውስጠ ድርጅት ትግሉን ማቀጣጠልና ለሕዝብ ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ እርምጃ ውስጥ መግባት ይጠበቅበታል፡፡ ንቅናቄው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ማንም አያቆመውም፡፡ ራሱን እያጠናከረ መሄድ ይችላል፡፡ በሂደትም በሌብነት እና  በትርምስ ሃይሉ ላይ ወሳኝ ድል መጎናፀፍ ያስችለናል፡፡