ወጣቱ እና የለውጡ ጉዞ

የኢትዮጵያ ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የዛሬው ትውልድ ወጣት እንደ ትናንቱ ወጣቶች እየታፈነ ለጦርነት አይወሰድም። ይህ ወጣት ዛሬ ሰርተህ ተቀየር ተብሏል፤ መንግሥትም ምህዳሩን አመቻችልሃለሁ ብሎታል። ችግሩን የሚረዳለት፣ ለችግሩም መፍትሄ  በአፋጣኝ የሚሰጥ መንግሥት አለው። ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ትልሞችም በመንግሥት ተቀርፀዋል።

እርግጥ በየትኛውም አገር ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። እንኳንስ ለልማቱም ይሁን ለዴሞክራሲው ጀማሪ በሆነችው ኢትዮጵያ ቀርቶ ባደጉት አገሮችም ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም። የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም አገር ውስጥ የለም። በመንግሥት የሥራ አስፈፃሚዎች ውስጥም ቢሆን ችግር ይኖራል።

ወጣቱ ጥንካሬውንና አፍላነቱን በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ ሲያውል ይስተዋል።  እርግጥም በወጣትነት ዘመን ጉልበት አለ። ወጣትነት ሁሉንም ነገር ለማድረግ ፍላጎት የሚያይልበት አፍላ ወቅት ነው። በወጣትነት ሁሉንም ነገር ለማድረግ፣ ሁሉንም ነገር ለመከወን ፍላጎት ይበረታል። እናም በዚህ የአፍላ ዘመን ሊፈጽም የማይችለው ነገር ያለ አይመስለውም። ይህ እውነታ ተፈጥሮአዊ ነው። በወጣትነት ዘመኑ እንዲህ ዓይነት ፍላጎትና ስሜት ቢያድርበት አይገርምም።  

በማደግ ላይ ያሉ አገራት ካሏቸው ሃብቶች መካከል ዋነኛው የሰው ሃብት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ይህን የሰው ኃይላቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ ሃብቱ የዕድገታቸው ምንጭ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከአገሪቱ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይታመናል። ይህን አፍላና ሁሉንም ነገር የመፈፀም ባህሪያዊ ተፈጥሮ ያለውን ወጣት በልማት ሥራ ላይ ማሰማራት ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ቀላል ይሆናል።  

ይህን እውነታ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት ቀደም ባሉት ጊዜያት ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን በማደራጀት ራሳቸውን ጠቅመው የአገራቸውን ዕድገት እንዲያስቀጥሉ ማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም ወጣቱ በልማት ሥራው ላይ እንዲሳተፍ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ ወጣቱን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። በዚህም ውጤት እየተገኘበት ነው።

ከፌዴራል መንግሥት ፈንድ በተጨማሪ በጀት መድበው ወጣቱ በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ የቻሉ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮችም አሉ። በተጠናቀቀው የ2010 የበጀት ዓመት በዋነኛነት ለወጣቱ ትኩረት በመስጠት እንደሰሩ ይታወቃል።  ይህም መንግሥት እዚህ አገር ውስጥ ላሉ ወጣቶች ምቹ የልማት ተግባሮችን እያከናወነ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ለወጣቱ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ፣ ወጣቶቿም ለኢትዮጵያ እንዲጠቅሙ ከማሰብ የመነጨ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ፈጣንና ተከታታይ ልማት ተስፋ ሰጪ ነው።  ይህንን ሁኔታ ደግሞ የተግባሩ ተሳታፊዎች ከሆኑት ወጣቶች ውጪ ማንም ሊመሰክር አይችልም። ሆኖም ሁከት ፈጣሪዎች በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች እየፈፀሙት የሚገኘውን  ጥፋት በረጋ መንፈስ ላስተዋለ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።

የሁከት ናፋቂነት መርዝ ለመርጨት በገንዘብ ተደልለው የሚንቀሳቀሱትንም ታዝበናል። አመፅን የማቀጣጠል የጥፋት ተግባራቸውን ዳር ለማድረስ ሲውተረተሩም ተመልክተናል።    

ታዲያ ወጣቱ የእነዚህን ፀረ ሠላም ቡድኖች ዓላማና ግብ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል። ፀረ ሠላም ቡድኖቹ የትኛውንም የአገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ሊወክሉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ከበስተኋላቸው የሚደጉማቸውን ቡድን  ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ ስለሆነ ነው።

የነዚህ ቡድኖች ፍላጎት በሁከት የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት ነው። ለዚህም ሲባል ቡድኖቹ ሁከት ፈጣሪዎችን በጉያቸው ውስጥ ወሽቀው ሠላምን ለማደፍረስና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

ይሁንና ይህ ፍላጎት በኢፌዴሪ መንግሥት በሣል አመራር እንዲሁም በህዝቡና በፀጥታ ኃይሎች ርብርብ እየከሸፈ ይገኛል። እነዚህ ሁከት ፈጣሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩ ናቸው።

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሆን ተብሎ የኢትዮጵያን ሠላም ለማወክ ነውጡ በፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች እንደሚቀነባበር መረዳት ይገባል። እናም ፀረ ሠላም ቡድኖቹ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች እየፈጸሙት ያሉት የማተራመስ ተልዕኮን ወጣቱ ተረጋግቶ መገንዘብ ይኖርበታል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን፤ የእነርሱን ማንነት በመገንዘብ ሊታገላቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፍ ይገባል። ወጣቱ የለውጡ አጋዥ ነውና።