የውይይቶቹ ጠቀሜታዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ከሃይማኖት መሪዎች ጋር፣ የትጥቅ ትግልን በመተው ወደ ሰላማዊ ትግል የተቀላቀሉትን ጨምሮ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮችና የወርቅ ተሸላሚ ከሆኑ የዘንድሮ ከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶች ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው።

ውይይቶቹ፤ በአገራችን እየተካሄደ ካለው ለውጥ አኳያ ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ፣ ዜጎች ያለ ምንም አድልኦ በጋራ ለአገራቸው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ከማስቻልና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።

በተጨማሪም ዜጎች በየሃይማኖታቸው በአንድ እምነት ስር ተሰባስስ እያለ፤ በሆነው ባልሆነው ጉዳይ በመነታረክ እንደ ጠላት ሲበላሉ የነበሩ አማኞች ይቅር ተባብለው ለአንድ አገራዊ ዓላማ በጋራ እንዲሰለፉ ከማድረግ አኳያም ጠቀሜታቸው የላቀ ነው።

ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንዲሁም የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈፀሟቸው እጅግ የሚያኮራ የመፍትሔና የይቅርታ ስራዎች ሃይማኖታዊ ነፃነትን ለአማኞች ያረጋገጠ ነው።

እርግጥም አሁን ያለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ህገ መንግስቱ የሃይማኖት እኩልነትንና የእምነት ነፃነትን በማስፈርና በተግባር በመተርጎምም የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲችሉ አድርጓል። ሆኖም በተግባራዊ አፈጻጸሙ በአንድ እምነት ስር የሚገኙ ምዕመናን እንደ ጠላት ሲተያዩ ኖረዋል።

ይሁ ሁኔታ በለውጡ እየተቀየረ ነው። የተለየ የሃይማኖት ብዝሃነት በሚስተናገድባት ኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የማምለክ ብሎም የመከተልና የማስፋፋት መብቱን እየተከበረለት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት ይህን የሚያጎላ ነው።

አሁን ያለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ህገ መንግስቱ የሃይማኖት እኩልነትንና የእምነት ነፃነትን በማስፈርና በተግባር በመተርጎምም የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲችሉ አድርጓል። ሆኖም በተግባራዊ አፈጻጸሙ በአንድ እምነት ስር የሚገኙ ምዕመናን እንደ ጠላት ሲተያዩ ኖረዋል።

ዶክተር አብይ ባደረጉት ጥረት ቅዱስ ሲኖዶሱ በውጭ በሚገኘው ሲኖዶስ ላይ አሳልፎቸው የነበሩ ውግዘቶችን እንዲያነሳ ጭምር ያደረገ ነው። ይህም ቅዱስ ሲኖዶሱ የተነሱትን ውግዘቶች ያነሳው በ1984፣ 1985 እና በ1999 ዓመተ ምህረቶች ያስተላለፋቸውን ሃይማኖታዊ ውግዘቶችን ነው።

በውጭ አገር የሚገኘው ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ በሚገኘው ሲኖዶስ ላይ አሳልፏቸው የነበሩ ውግዘቶችን ባለፈው ሳምንት አስቀድሞ አንስቷል። ተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ሲኖዶስ አዲስ አበባ ገብቷል።

በዚህም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ድረስ የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና በጠበቀ መልኩ የአቀባበል ስነ ስርዓት ተከናውኖላቸዋል። ይህም በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የሚታየውን የጥላቻ መንፈስ በፍቅር የቀየረ ነው።

በእስልምና ሃይማኖት ውስጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ጉባኤንና የሚስሊሙ ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ችግራቸውን እንዲፈቱ እያደረጉ ነው። ይህ ችግር የመፍቻ መንገድ ቀደም ሲል በጥላቻ መንፈስ ይተያዩ የነበሩ የአንድ እምነት ተከታዮችን ወደ ጋራ አስተሳሰብ የሚያመጣ ነው።

ከፖለቲካ አኳያም ቢሆን በትጥቅ ትግል ላይ ከነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸው ውይይቶች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በለውጡ ምክንያት የተከፈተው አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ውይይቶችን እየፈጠረ ነው። ውይይቶቹ ለሀገራችን ጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም አገራዊ ድምፆች በእኩልነት እንዲሰሙ የሚያደርጉ ናቸው። ውይይቶቹ ጥርጣሬም እንዲወገድ ያደርጋሉ።

እርግጥ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ድርድር መቋጫው ጥርጣሬንና ግጭትን በማስወገድ ሰላምን ማምጣት ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱንም ስር እንዲሰድ ማሰብ ትርጉም አይኖረውም።

ዴሞክራሲ ስር ባልሰደደበት ሀገር ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ሊያስተዋውቁና በህዝቡ ይሁንታ በሚካሄድ ምርጫ አገር ሊመሩ አይችሉም። በመሆኑም አዋጆችን ይሁን ህጎችን ለመቀየር ሲደራደሩ የሰላማችን ሁኔታ ይበልጥ የሚጠናከርበትን መንገድ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም ታስቦ ነው።

በመሆኑም በገዥው ፓርቲም ይሁን በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሚከናወኑ ጉዳዩች ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም። ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ዴሞክራሲን የማስለጥ ተግባር የዴሞክራሲ መለያ ስለሆነ ነው።

ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት እየተካሄደ ያለው ውይይት ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው። እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የሀገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። ምህዳሩም በሚፈለገው መጠን እንዲሰፋ ያደርጋል።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሃይማኖት መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ጠቀሜታቸው አገራዊ ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን የሚያመጡ ናቸው። ታዲያ ውይይቶቹን በመደገፍና ለተግባራዊነታቸውም መትጋት የዜጎች ሃላፊነት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።