‘እኔ ለአገሬና ለወገኔ…?’

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው። በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን በተከፈተው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በላይ፤ በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦችና ምርቶች በማስተዋወቅ እንዲሁም በውጭ አገራት ያካበቱትን እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ልምድን ለአገራቸው በማዋልና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ወዘተ የሚወዷትን አገራቸውን መጥቀም ይችላሉ። ይህም ‘እኔ ለአገሬና ለወገኔ ምን ሰራሁ?’ የሚል ቁጭት በውስጣቸው እንዲፈጠር የሚያደርግና አገራቸውንም የሚጠቅም ነው።

በዚህ ፅሁፍ ሁለት ነገሮችን ከዳያስፖራው አኳያ ላነሳ ወዳለሁ፤ የአገርን የቱሪዝም መስህቦችንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን። እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት የባህል ኢንዱስትሪዎች ምርቶች ተስፋፍተውና ደረጃቸው ተሻሽሎ በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው። የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ መገለጫን “Land of origions” (ቀደምት ምድር) ወደሚል ስያሜ በመቀየር ዘርፉ የዓለም መስህብነቱን ጨምሮ ከፍ እንዲል ለማድረግ ተችሏል። በዚህ ላይ ዳያስፖራው ከተጨመረበት ይበልጥ ከፍ ይላል።

ከዘርፉ ልማት አጠቃላይ እመርታ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑና ባህላዊ እሴቶችና የተፈጥሮ መስህቦች ለሀገሪቱ መልካም ገጽታ ግንባታ የበኩላቸውን አሰተዋፅኦ እንዲያደርጉ በመደረግ ላይ ነው። ይህም እስከ ዕቅዱ ፍፃሜ (እስከ 2012 ዓ.ም) የሚቀጥል ይሆናል። ዳያስፖራው ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብዙ ሚና ሊጫወት ይችላል።

የተለያዩ ህዝቦች መገኛ የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህልን፣ ቅርስንና የተፈጥሮ መስህቦችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመጠበቅና በማልማት እንዲሁም የህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት የባህልና ቱሪዝም ዘርፉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበርክትም በመደረግ ላይ ነው።

የሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች፣ ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንንና ቅርሶቻችንን በመመዝገብና በመጠበቅ እንዲሁም እንዲታወቁና እንዲለሙ በማድረግ ለህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ እየተደረገ ነው።

የሀገሪቱ ባህላዊ እሴቶች ጎልብተው በህዝቦች መካከል መተማመንና መከባበርን እንዲጠናከርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያግዙ የማድረግ ግብን ያነገበው ይህ ዘርፍ፤  ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንና ቅርሶቻችንን እንዲለሙ ብሎም ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ የመፍጠርን ብሔራዊ ራዕይ ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱም ግብ ተጥሎ እየተሰራበት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የህዝቦች ባህላዊ መገለጫዎች የሆኑ የተለያዩ ስርዓቶችና መስህቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውቀው እንዲመዘገቡ እየተደረገ ነው። በእነዚህ ተግባሮች ላይ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ የላቀ ውጤት ይመዘገባል።

ከዳያስፖራው አንፃር የበጎ ፈቃድ አገልግሎትንም ማንሳት እንችላለን። ዳያስፖራው ደ አገሩ በሚመጣበት ወቅት ለእረፍት ካሉት ወራቶች ውስጥ ቢያንስ በአንዱ በዕውቀቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢሰጥ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምዕራቡ አገራትም የተለመደ ነው። ወጣቶችና ታላላቅ ባለሙያዎች ይህን አገልግሎት ይሰጣሉ። የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዩች ላይም ማዋል ይቻላል። ለአብነት ያህል ዳያስፖራው በህብረተሰቡ የጤና ችግር፣ አካባቢን በመጠበቅና የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ ሊሳተፍ ይችላል።

በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ አስታማሚ የሌላቸውን ዜጎች በማስታመም፣ ኤች አይቪ/ኤድስን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ በመሳተፍና ሌላው ቢቀር በሆስፒታሎች ውሰጥ የጤና ትምህርት ሲሰጥ አብሮ በማገልገል ማህበረሰቡን መደገፍ ይቻላል። በአካባቢ ፅዳት ላይ መሳተፍ ማህበረሰባዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

በየቀበሌውና በየመንደሩ በመዘዋወር ስለ ቆሻሻ አወጋገድ ህብረተሰቡን ከውጭ በቀሰሙት ሙያ ማስተማር ይችላሉ። የአፍሪካና የአገራችን መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ በዚህች ከተማ ውስጥ ያለውን የቆሻሻና የመጥፎ ጠረን እንዴት ማስወገድና መከላከል እንደሚገባ ህብረተሰቡን በማስተማር ለውጥ ለውጥ ሊያመጡም ይችላሉ።

በዚህ ተግባራቸውም ከየአካባቢው ወጥቶ በየመንገዱ የሚተኛው ፍሳሽ እንዲሁም እንደነገሩ የሚጣለው ቆሻሻ የከተማዋን ገፅታ ከማበላሸት ባለፈ በርካቶችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ በማስተማር የህብረተሰቡን ጤና እንዲጠበቅ በማድረግ ለአገራቸውና ለወገናቸው ሊሰሩ ይችላሉ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዓለማችንና የአገራችን አሳሳቢ የሆነውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም ሊውል ይችላል። ዳያስፖራው ወደ አገሩ ሲመጣ በለው የእረፍት ቀን በፌዴራልና በክልል ደረጃ ፓስፖርት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች እየተገኙ ስለ ህገ ወጥ ስደት አስከፊነት ለተጓዦች በማሰተማር የግንዛቤ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በቤት ለቤት ቅስቀሳም የችግሩን መንስኤና በምን ምክንያት ዜጎች እየተሰደዱ እጅግ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ በማስተማር የዜግነት ግዴታውን በመወጣት የህሊና እርካታ ያገኛል።

የአካባቢን ስነ ምህዳር ለመጠበቅም የተራቆቱ አካባቢዎችን ለመታደግ ችግኝ በመትከል የአካባቢን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥም ጉልህ ሚና ሊያበረክት ይችላል። የስነ ምህዳር ችግር በተለይ እንደ እኛ ላለ በየጊዜው በተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ለሚጠቃና ዜጎቹም የድርቅ ሰለባ ለሚሆኑበት አገር አደጋውን ከኢኮኖሚና ከአገራዊ ክብር አኳያ በመመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በማከናወን አገርን መጥቀም ይቻላል።

ዳያስፖራው እነዚህን ተግባራት በአካል አገሩ ውስጥ በመገኘት ከተማረውና በውጭ ከቀሰመው ዕውቀት አገሩን ማገዝ ይችላል። ይህም ‘እኔ ለአገሬና ለወገኔ ምን ሰራሁ?’ የሚል የሁሌ ቁጭቱን ከመመለስ ባሻገር ወገኑን ለመጥቀም የሚያደርገው ጥረት ተግባራዊ ምላሹ ይሆናል።