ሁሉም እንደ አንድ…

በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘ ከፍተኛ የውጭ አገር ገንዘብና የተለያዩ የጦር መሳሪዎች አብረው በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው። የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ዓላማ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው። ዓላማቸውም በአገር ላይ የኢኮኖሚ ሸፍጥ መፍጠርና ሰላምና መረጋጋትን ማወክ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ እኩይ ዓላማ አገራችን ከሶስት እና አራት ወር በፊት ወደነበረችበት የኢኮኖሚ ችግርና የሰላም እጦት ውስጥ ተመልሳ እንድትገባ የሚደረግ ተንኮል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይደለም።

ስለሆነም ህብረተሰቡ ወንጀሉንና ፈጻሚዎቹን በመከታተል በለውጡ የተጀመሩት የኢኮኖሚ ማንሰራራትና አንጻራዊ የሰላም ሁኔታችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም እንደ አንድ በመሆን የድርሻውን ሊወጣ የግድ ይላል። ሰሞኑን የታዩት ሁኔታዎች ይህን እውነታ የሚያረጋግጡ ናቸው።

ሰሞኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል እንደገለፁት፤ ጥናትን መሰረት በማድረግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ፖሊስ በጋራ ባካሄዱት ኦፕሬሽን 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ተይዟል። በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ የነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች በዚሁ ኦፕሬሽን ሊያዙ መቻላቸው ተጠቁሟል።

ከነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎቹ መካከልም ሽጉጥና ጥይቶች እንዲሁም ሁለት መትረየሶች የሚገኙበት ሲሆን፣ 80 ሺህ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይቶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል። እነዚህ የጦር መሳሪያዎች በሱዳን እና በጅቡቲ በኩል የገቡ ሲሆን፤ ስሪታቸውም በአብዛኛው ቱርክ መሆኑ ተገልጿል። በዋናነትም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረገበት ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር መሆኑ ግልፅ ነው።

ህብረተሰቡ አለመረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረትን መከላከል ይኖርበታል። ህዝቡ የሰላሙ ሁኔታ መሪ ተዋናይ ነው። በየአካባቢው ለሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ ለውጥን ማምጣት አይቻልም ነበር።

በአገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ግጭት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ እየከፈለ ያለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም። የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው። ካለፉት ተግባሮቹ ስለተማረ ነው።

ይህ ሰላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሰላም እንዲሰሩና የሰላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ የቻለ ነው። ይህ ህዝብ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተራመዳቸው አስከፊ ሁኔታዎች የፈጠሩበትን ችግር ያስታውሳል። እነዚያ አስከፊ ሁኔታዎች እንዲቀየሩና ለውጥ እንዲመጣ መስዋዕትም ሆኗል።

ለውጦቹ በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ነው። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ያውቃል።

በለውጡ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው። በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥ የገንዘብና የመሳሪያ ዝውውሮች የሰላም እጦቶችን በመፍጠር የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የታለመ በመሆኑ ሊከላከላቸው ይገባል። 

በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም።

 እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም።

ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። አዎ! የአንድ ሀገር ሰላም የህዝቧቿ ሰላም ነው።

በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ።

እርግጥ የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም።

የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና። እናም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም— ይጠብቃቸዋል እንጂ። ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።

ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ማስተማር ይኖርባቸዋል።

አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ይሁን እንጂ ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሰላም ጉዳይ መደራደር እንደማያስፈልግ ማሳወቅም ከተጠርጣሪ ወጣቶቹ የሚጠበቅ ተግባር ይመስለኛል። ሰላም ከሌለ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይቻልም። ሰላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሰረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ደግሞ ስለ ሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል። እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሰላምን በጋራ ለማቆም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ የውይይት ባህልን እየገነቡ መሄድም ያስፈልጋል።

እነዚህን ተግባራቱን እያጎለበተም፤ ህዝቡ ኢኮኖሚውን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን እንዲሁም የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማደፍረስ ከአንድ ቦታወደ ሌላው የሚደረጉ የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን መግታት አለበት። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ነገር ባለመኖሩ ህገ ወጥ የገንዘብም ይሁን የመሳሪያ ዝውውሮችን በመግታት ኢኮኖሚውንና ሰላሙን የተረጋጋ የማድረግ የተለመደ ሚናውን ማጠናከር ይኖርበታል።