የአቢይ ዐቢይ መንገድ ክፍል ሁለትና የመጨረሻ

በቅርብ ዘመን ታሪኳ፤ ኢትዮጵያ ሦስት መንግስታትን አይታለች፡፡ አፄአዊ ፊውዳላዊ አገዛዝን፣ ኮምኒስት ነኝ ባዩን ወታደራዊ ጁንታ እና በብዙ እንከኖች የታወከውን እና ባለፉት ሦስት ዓመታት በህዝብ አመጽ ሲናጥ የከረመውን ‹‹የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ›› ስርዓት አስተናግዳለች፡፡

ከአፄ ኃይለስላሴ ወደ ደርግ የተደረገውን እና ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የተደረገውን የስርዓት ለውጥ ስንመለከት ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ደርግ የስርዓት ሽግግሩን ያወጀው፤ 60 የንጉሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት በመረሸን ነበር፡፡ ከአፄው ወደ ደርግ የተደረገው የሽግግር ሂደት ፖለቲካዊ አመፅ የታየበት ነበር፡፡ የደርግ ባለስልጣናት በትረ መንግስት በጨበጡ ማግስት፤ በአፄው ሹማምንት ላይ በወሰዱት ደመ-ቀዝቃዛ እርምጃ የታሪካቸውን መጋረጃ ገለጡ፡፡ ገና ከመነሻው በደም ቡኬት የፀናው የደርግ የፖለቲካ መድረክ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የማይታወቅ የጭካኔ አውሬ የተቀሰቀሰበት መድረክ ነበር፡፡ ተቀናቃኞቹን በማጥፋት ዘመቻ እና ምንጠራ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ በጎዳና ተገድለዋል፡፡ በቀይ ሽብር ዘመቻ ደም አበላ ወርዷል፡፡

ኢትዮጵያም እንደዚያ ዓይነት ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባት ሀገር ሆነች፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቁስሉ ከጠገገ በኋላ እንኳን ህመሙ ጨርሶ ያልጠፋ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በዚህ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውዶቻቸውን ባጡ ሰዎች ላይ የደረሰው የልብ ስብራት አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ትዝታው ሊዳፈን ያልቻለ ትውስታ አስታቅፎን ሄዷል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባውን ውጦ ሰቀቀኑን ተሸክሞ ዓመታትን ዘልቋል፡፡

ቻርልስ ሻፈር፤ ‹‹ኢህአዴግ የኢትዮጵያን የእርቅ ትውፊት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ሆኖም በRestorative Justice ሰላም የማስፈን ስልትን፤ በመተው የደርግ ባለስልጣናት ጉዳይ በፍርድ አደባባይ እንዲታይ ለማድረግ ወሰነ›› ይላል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በጉዳዩ ላይ ጥናት ካደረጉ ምሁራን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ‹‹ጦርነቱ በኢህአዴግ አሸናፊነት እንደሚደመደም በግልፅ መታየት ሲጀምር የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አድርገው ነገሩ ባማረ ሁኔታ ፍፃሜ ሊያገኝ የሚችለው በፍርድ አደባባይ እንደሆነ ሰፊ ክርክር ካደረግን በኋላ ውሳኔ አሳልፈን ነበር›› ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ ጉዳዩ በፍርድ እንዲታይ ውሳኔ ያደረገው፤ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች መሆኑንም ጸሐፊው ይናገራል፡፡ የመጀመሪያው፤ የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከዘር ማጥፋት ጋር የተቆራኘ ፍጅት እጅግ አረመኒያዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነገሩ ከፖለቲካዊ አድማስ ውጭ እንዲሆን ስላደረገው፤ ሁለተኛ፤ ለከት ያጣና ጨርሶ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ያልጎበኘው፣ እንደ እብድ ሥራ ሊቆጠር የሚችል የኃይል አጠቃቀም የታየበት በመሆኑ፤ ትናንትን ከዛሬ የሚለየው መስመር በግልፅ እንዲሰመር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ሦስተኛ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርን በፍርድ ሂደት እልባት የመስጠት የቆየ ታሪክ እና ልምድ ያለው ህዝብ በመሆኑ የፍርድ ቤት ውሳኔ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖረው በማመን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገራቸውን ሻፈር ይጠቅሳል፡፡

የቀይ ሽብር ወንጀል በኢትዮጵያ ህግ፣ በኢትዮጵያዊ ዳኞች እና በኢትዮጵያዊ ዓቃቢያነ ህግ እንዲታይ መደረጉ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ ሆኖም የሂደቱ መራዘም እንደ ችግር መጠቀሱ አልቀረም፡፡ መጓተቱም የተፈጠረው፤ ከአቅም፣ ከገንዘብ ከልምድ ጋር በተያያዙ እና መንግስት ‹‹ለመዋጥ ከሚችለው በላይ በመጉረሱ የተነሳ የተፈጠረ ችግር›› መሆኑ ይገለጻል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ደርግ ከነባሩ የፖለቲካ እና የግጭት አፈታት ባህል በወጣ አካሄድ፤ በእስር ላይ የነበሩ 60 ሚኒስትሮችን ያለ ፍርድ ረሸኗል፡፡ በዚህም፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ያለመተማመን አስተሳሰብን አንግሷል፡፡ ደርግ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ኢህአፓ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በውስጠ ድርጅት አሰራራቸው የደርግን ፍርደ- ገምድል ባህርይ አንፀባርቀዋል፡፡ ድርጅታዊ ባህርያቸው ከደርግ ብዙ የተለየ አልነበረም፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ‹‹የነፃነት ጎህ ሲቀድ›› ሲል በፃፉት መፅሐፍ የጠቀሱት ጉዳይ ለዚህ ምስክር ይሆናል፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ‹‹የነጣነት ጎህ ሲቀድ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው በመፅሐፉ፤ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ሠራዊቱ ነፃ መሬት እንደ ደረስኩ የተቀበለኝ ጌራ የሚባል የአመራር አባል፤ ስለ ሠራዊቱ መግለጫ ከሰጠኝ በኋላ፤ አዲስ አበባ ስላለው ሁኔታ ይጠይቀኛል፡፡ እኔም የወጣሁበት ጊዜ ወጣቶች  እየተያዙ የሚታሰሩበት እና ብዙዎችም የተገደሉበት ጊዜ ስለነበር፤ ይህንኑ በመግለፅ ‹የከተማው የትጥቅ ትግል› የሚያዋጣ እንደማይመስለኝ እና በተቻለ መጠን መውጣት የሚችሉትን አባሎች እና ወጣቶች በቶሎ ማስወጣት እንደሚገባ እገልፅለታለሁ፡፡ በዚህን ጊዜ ቁጣ በተሞላበት ሁኔታና ድምፅ ይህንን ነገር እዚህ ሠራዊቱ ውስጥ ለማንም መናገር እንደማልችል፤ ድርጅቱን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም ሊጥል የሚችል መሆኑን ይነግረኛል፡፡

‹‹…በሠራዊቱ የደህንነት አባላት (ጋንታ 44 ይባል ነበር) የሚታዘዝ እስር ቤት እንደ ነበረ ሰማሁ፡፡ በዚህ እስር ቤት በተለያየ ምክንያት የታሰሩ የሠራዊቱ አባች እንደነበሩና በእነኚህ እስረኞች ላይ ሰቆቃ ይደርስ እንደ ነበር ስንሰማ ብዙዎቻችን በተለይ ከከተማ በወጣነው አባላት ላይ ከፍተኛ ግራ መጋባት (Disillussionment) ተፈጠረ፡፡ በምንም ዓይነት የኢህአፓ ሠራዊት አመራር፤ አባላት ላይ ሰቆቃ ይፈፅማል ብለን ለማመን አቃተን›› ይላል፡፡

አያይዘውም፤ ‹‹ከእነኚህ ከታሰሩ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ከእነኚህ ውስጥ ግማሽ ያህል የምንሆነው በመጀመሪያው ቀን የታሰርን ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ይህንን (የአንጃ) እንቅስቃሴ ከሥሩ ለመመንጠር በሚል በተካሄዱ ተከታታይ ስብሰባዎች፣ ገሚሱ በሌሎች (ሐቀኛ) ታጋዮች ስለአንጃነታቸው የተጋለጡ፣ ገሚሱ ደግሞ የታሰርነው ሰዎች ሐጢያት በአደባባይ ሲገለፅ ተደናግጠው ‹‹ራሳቸውን አጋልጠው›› የታሰሩ ነበሩ፡፡ ከኛ በኋላ ታስረው በመጡ ልጆች ስለእነኝህ  ስብሰባዎች የተነገረን ነገር በእውነቱ በጣም የሚያስደነግጡና የሚያሳፍሩ ነበሩ፡፡

‹‹ … አንዳንዶቻችን ሳናውቀው የተፈጠረ አንጃ ነበረ ወይ ብለን እዚያው‹ስንገደ እስር ቤት› መጠያየቅ ጀምረን ነበር፡፡ ከመሀላችን አንዳንዶቹ በዚህ ላይ የነበረው እምነት የፀና በመሆኑ ምክንያት ምንም እንኳን እሱ ራሱ የተፈጠረው ‹አንጃ› መሪዎች አንዱ በመሆኑ እንደ ተከሰሰ እያወቀና እንዲህ ዓይነት ድርጅት (እሱ የሚመራው) እንደሌለ እየተገነዘበም በድርጅቱ ላይ የነበረው እምነት፣ ፅናት እና በተለይ እነኚህ ሁሉ ጓዶች ሊሳሳቱ አይችሉም በሚል ስሌት፤ ሰራ የተባለውን ወንጀል አምኖ ወንጀሉ እንዴት እንደ ተፈፀመ የሚገልፅ የእምነት ቃል በዝርዝር ፅፎ ለከሳሾቻችን የሰጠ ነበር፡፡ በፍፁም ከማልረሳቸው አጋጣሚዎች እና በዚያ በወጣትነት ዕድሜዬ የሰውን ልጅ የውስጥ ጭንቀት እና በዚህም ምክንያት የሚገጥሙትን ፈተናዎች የሚቋቋምባቸው አካሄዶች እስከ ምን ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ያየሁበት አንድ ሁኔታ ነበር፡፡

‹‹ከታሰርነው ሰዎች መሐል አንዱ በዕድሜው ከብዙዎቻችን ከፍ ያለ፤ በዚያን ጊዜ ውጭ አገር ተምሮ የሁለተኛ ዲግሪ ያለው ሰው ነበር፡፡ በተፈጠረው ሁኔታም በጣም ከተደናገጡት እና ከተረበሹት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡‹ከአንጃው› መሪዎች አንዱ ተደርጎም ይወሰድ ነበር፡፡ የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ወንጀሉን በሚመለከት ሁለት ደብተር ሙሉ የእምነት ፅሑፍ እና ወንጀሉ እንዴት እንደተፈፀመ፤ እነማን በወንጀሉ እንደተሳተፉ (ምንም በሌለ ወንጀል) ዘርዝሮ ለከሳሾቻችን ይሰጣል፡፡ እስር ቤቱ ትንሽ ስለነበር ሁላችንም የምናደርገውን እንተያይ ስለነበር ከመሐላችን አንዱ ‹እንዴ ምን ታሪክ ቢኖርህ ነው ይህንን ሁሉ የፃፍከው› ብሎ እንደ ቀልድ ይጠይቀዋል፡፡ ለዚህ ምንም መልስ ሳይሰጥ በማግስቱም ይህንን ሲፅፍ ውሎ በሦስተኛው ቀን ፅሁፉን ለከሳሻችን ይሰጣል፡፡

‹‹….ከሌሊቱ 11 ሰዓት ገደማ አንድ የማጓራት ድምፅ እሰማና በድንጋጤ ባንኜ ስመለከት፤ የእስር ቤቱ ጣሪያ አጭር ስለነበር እግሩ በትንሹ መሬቱን እየነካው በቶሎ መሞት አልቻለም፡፡ እንደምንም ተደጋግፈን አውርደን አዳነው፡፡ ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ የተኛበት አጠገብ ሔጄ ሳጫውተው በፍፁም እውነት ያልሆነና እራሱን ያዳነ መስሎት ከመሬት ተነስቶ ብዙ ሰው እንደ ወነጀለ፤ያ ረጅም ፅሁፍም ይህ እንደ ሆነና ይህንንም ለከሳሾቻችን እንደ ሰጣቸው፤ እነሱም ይህን ተጠቅመው ብዙ ንፁህ ሰው ሊጎዱ እንደሚችሉ፤ ያደረገው ነገር የታወቀበት ስለመሰለው… የሰራው ሥራ ግዝፈት እንደታየውና ሊመልሰው እንደማይችል ሲያውቅ ከሚሸከመው በላይ እንደ ሆነበትና እንደዚህ ከራሱ ጋር ተጣልቶ ከሚኖር ለመሞት መወሰኑን በዝርዝር አጫወተኝ፡፡››

አያይዞም፤ ‹‹የሚያሳዝነው ሰውየው ይህንንም አድርጎ አልተረፈም፡፡ …ድርጅቱ ከህወሓት ጋር ጦርነት ገጥሞ ወደ ኤርትራ ማፈግፈግ ስለነበረበት የፍርድ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ ‹‹ሞት ሊፈረድባቸው የሚችሉ›› በሚል ከውስጣችን ለይተው ከገደሏቸው ስምንት እስረኞች መሐል አንዱ ነበር›› የሚለው ዶ/ር ብርሃኑ በመጨረሻ እርሱ ከክሱ ነፃ እንደወጣ ያትታል፡፡ እናም፤ ‹‹ከእስር የወጣን ዕለት ጠዋት ከሠራዊቱ ጋር በማፈግፈግ ወደ ኤርትራ እንደምንሄድ ተነገረን፡፡ የሌሎቹ ጓደኞቻችንን ሁኔታ ብንጠይቅ እናንተን አይመለከታችሁም ተባልን፡፡ ወደ ኤርትራ ጉዞ በጀመርን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጠባቂዎቻችን ከነበሩ አንዳንድ ታጋዮች ጥቂቶቹ የጓደኞቻችን ልብስ ለብሰው አየን፡፡ ቀሪዎቹን እስረኞች እንደገደሏቸው ተረዳን›› ይላል፡፡

የአዲስ ጎዳና

ዶ/ር ዐቢይ ባለፉት 50 ዓመታት እንደ ህዝብ የደረሰብን እንዲህ ያለ መከራ ካደረሰብን ጉዳት እንፈወስ ዘንድ በማስተዋል የመረጡት ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› ፍቅር፣ ይቅርታ እና እርቅ ነው፡፡ ከዚህ መሰል የታሪክ ዳራ ወጥተን፤ መሠረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች የተከበሩበት ፖለቲካዊ ስርዓት ለመፍጠር የምንችለው የሐገራችን ፖለቲካ ሰብአዊ መልክ እንዲይዝ በማድረግ ነው፡፡ ‹‹እኔ ዶ/ር ብርሃኑን ገድዬ በስልጣን ለመቆየት፤ ዶ/ር ብርሃኑ እኔን ገድሎ ስልጣን ለመያዝ ማሰብ አይጠቅመንም›› በማለት፤ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ባህል ሊወገድ እንደሚገባ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ያለ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግለሰቦች ጥረት የሚጠግግ ቁስል አይደለም፡፡ በጋራ ጥረት የሚታከም ቁስል ነው፡፡ እናም ‹‹የትም መቼም እንዳይደገም›› ስንል፤ የዚያን ስርዓት ችግሮች በመዘርዘር እና የውግዘት ናዳ በማውረድ ሳይሆን፤ ያ ስርዓት እንደ ትቢያ የረገጠውን የህግ የበላይነት በማንሳት ተቋማዊ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓት በማፅናት የምናረጋግጠው ነው፡፡

ከ1968 እስከ 1970 ድረስ ባለው ጊዜ በአረመኔያዊው የደርግ ወታደራዊ ጁንታ የተፈፀመውና ‹‹ቀይ ሽብር›› በሚል የሚጠቀሰው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየቦታው የታጎሩበት፣ ቶርች የተደረጉበት እና የተገደሉበት ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ፍትህ የተሰደደችበት ወይም የሞተችበት ዘመን ነው፡፡

የህግ ሊቃውንት፤ ‹‹ለሰው ልጆች ታላቅ ሐሴትን የሚያጎናፅፍ፤ ታላቅ ምድራዊ ፀጋ ፍትሕ ነው›› ይላሉ፡፡ ፍትህን የማስፈን ጥረት ብዙ ገፅታ ያለው ክስተት ነው፡፡ ዋና መገለጫው ደግሞ ዳኝነት ነው፡፡ ፍትሕ፤ የህግ ተግባራዊነት ውጤት ነው፡፡ ፍትሕ የሚገኘው፤ ህግ የሚያዘውን በማስፈፀም እና የማይፈቅደውን በመከልከል ነው፡፡ ስለሆነም፤ ህግ መረን የለቀቀ ፍላጎትን እና ጥሬ ጉልበትን ገድቦ፤ መሆን የሚገባውን እና የማይገባውን ለይቶ ያስቀምጣል ወይም ስርዓትን ይዘረጋል፡፡ ህይወት ዋስትና የሚያገኘው፤ ነፃነት የሚከበረው፤ ዕድገት የሚፋጠነው፤ ዳር ድንበር የሌለው የሰው ፍላጎት፤ ያልተመጣጠነው የሰው ጉልበት ተገድቦ በስርዓት ሲገዛ ነው፡፡

ይህ ስርዓት መብት እና ነፃነት ይሰጣል፡፡ አብሮም ግዴታን ያፀናል፡፡ መብትም ግዴታም የሚታሰቡት በህግ ውስጥ ነው፡፡ ህግ፤ መብት የሚያቋቁመው ሰዎች በነፃ ፍላጎታቸው እና በግዙፍ ጉልበታቸው ሊያደርጉ የሚችሉትን ገድቦ፤ መሆን የሚገባውን እና የማይገባውን ለይቶ በማስቀመጥ ነው፡፡ ሁሉን እኩል የሚያይ እና ተፈጻሚነቱም በሰዎች ማንነት የማይደናቀፍ ስርዓተ ህግ በማጽናት ነው፡፡

ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ደርግ የተደረገውን ሽግግር እና ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የተደረገውን ሽግግር መመልከት ችግራችንን በትክክል ሊያስረዳን ይችላል፡፡ የደርግ  ሽግግር የፍትህን ታላላቅ እሴቶች ሁሉ የደፈጠጠ ነበር፡፡ ደርግ የታሪክ ምዕራፉን የከፈተው፤ 60 ሹማምንትን ያለ ፍርድ በመረሸን ነበር፡፡ እንዲሁም ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው፤ ደም አፋሳሽ ከሆነ የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ነበር፡፡ ኢህአዴግ የመንግስት ሥልጣ ሲይዝ ሐገሪቱ ድብልቅልቅ ያለ የተሳከረ ሁኔታ የተጋፈጠችበት ወቅት ነበር፡፡ ብዙዎች ብዙ ነገር ጠብቀዋል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ የሽግርር ሂደት ምዕራፉን የከፈተው፤ በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበባቸው የደርግ ባለስልጣናት፤ ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸው በፍርድ እንዲታይ በማድረግ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁርጠኛ መሆኑን እና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ስርዓት ለመገንባት መነሳቱን የሚያሳይ ትልቅ እርምጃ ወሰደ፡፡ 

የስራዎቹ ሁሉ መጀመሪያ ሆኖ ከኢህአዴግ ፊት የተደቀነው እና በወቅቱ ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ አጀንዳ የነበረው የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳይ ነበር፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ቀይ ሽብር በሚል በተሰየመ ዘመቻ ተማሪዎችን፣ ምሁራንን እና ሌሎች ዜጎችን ያለ ፍርድ በመጨፍጨፍ፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ ናቸው፡፡ የሽግግሩ መንግስት ዋነኛ አጀንዳም ይህ የሰብዓዊ መበት ጥሰት፤ አንድ መልክ ይዞ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ እና በደም ከተጨማለቀው የትናንት ታሪክ በመውጣት የአዲስ የተስፋ ምድር መፍጠር፤ በተለያዩ የህብረተሰብ ቡድኖች መካከል እርቅ እንዲወርድ ማድረግ ነበር፡፡

የደርግ እርምጃ የተወሰኑ ባለሥልጣናትን ወይም ጥቂት ግለሰቦችን ለጉዳት የዳረገ ሳይሆን መላ የሀገሪቱ ህዝብ ላይ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ሰቆቃ የፈጠረ እርምጃ ነው፡፡  የደርግ የጅምላ ጭፍጨፋ ወይም ነፃ እርምጃ፤ የመንግስት ሥልጣንን በጨበጠ ኃይል ተቀነባብሮ የስርዓቱ ተቃዋሚ እና ‹‹ፀረ-አብዮተኞች›› የተባሉ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሰለባ ያደረገ ነው፡፡ ሀገራችን በ1983 ዓ.ም፤ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የኋላ ታሪኳ አድርጋ ይዛ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች የተከበሩበት፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት ለመፍጠር ስትነሳ ፈተናዋ ብዙ ነበር፡፡

ኢህአዴግ የደርግ ባለስልጣናትን ጉዳይ በፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረጉ፤ ከትናንት ታሪክ የተለየ አካሄድ ለመከተል መወሰኑን እና ለሰብአዊ መብት ጉዳዮች ያለውን አቋምም የሚያመለክት ነበር፡፡ እንዲሁም ሐገሪቱ ከኋላ ታሪኳ ጋር ለመታረቅ የምትችልበትን ዕድልም የፈጠረ ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ኢህአዴግ በ960ዎቹ እና 70ዎቹ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመመርመር ወንጀለኞቹ በህግ የሚጠየቁበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ያሳየው ቁርጠኝነት እና የታየው የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ፤ መጪውን ጊዜ ከትናንት የሚለይ ግልጽ እና ጉልህ መስመር ያሰመረ ነበር፡፡

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሰለባ ያደረገው ያ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና ወንጀል በፍርድ ቤት ዳኝነት እንዲታይ ከተደረገ በኋላ፤ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያምን ጨምሮ የወታደራዊ ጁንታው ግንባር ቀደም የፖለቲካ አመራሮች በዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ የግፍ ተግባር ወንጀለኛ ሆነው በመገኘታቸው ዋና ዋናዎቹ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ታህሳስ 8/1998 ዓ.ም የጥፋተኛነት ብይን ተላለፈባቸው፡፡ የሐገራችን መጥፎ የታሪክ ምዕራፍም እንዲዘጋ ተደረገ፡፡

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠ/ሚ፤፡ከኒው አፍሪካ መፅሔት ጋር (ሴፕቴምበር፣ 1994)፤ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹ለኢትዮጵያ ህዝብ ህግን የጣሱ፣ ሰብዓዊ መበትን የረገጡ ሰዎች፣ ራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው የተመለከቱ ሰዎች፤ በእርግጥ ከህግ በላይ እንዳልሆኑ አንድ ቀን ሂሳብ መወራረዱ እንደማይቀር፤ ዕዳ የሚከፈልበት ሁሉም ሰው የእጁን የሚያገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ በተጨባጭ ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡

ሆኖም የኢህአዴግ መንግስት በእስከ ዛሬ ጉዞው ያለው የታሪክ መዝገብ ከችግር የጸዳ እንዲሆን ማድረግ አልቻለም፡፡ በተያዙ ሰዎች የመብት አከባበር ረገድ በርካታ ግድፈቶች መፈጸሙን በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን የቀረቡ ዘገባዎች በግልጽ አሳይተውናል፡፡ ለዚህ ችግር መነሻው፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ግንባር ቀደም ተዋናዮች የሆኑት ኃይሎች ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ባህል እሴቶች ታንፀው ያደጉ አለመሆናቸው ነው፡፡ በአንድ በኩል በተለያየ መልክ እና ደረጃ የአፈናውን ስርዓት የተዋጉ ወይም የታገሉ፤ በሌላ በኩል የስርዓቱ ባለሟሎች የነበሩ ወገኖች፤ በተለያየ ደረጃም ቢሆን የአፈናው ስርዓት ትውፊት፣ እሴት እና ውርስ ተጠቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር በዜጎችና በተቋማት ዘንድ የዴሞክራሲያዊ እሴቶች እና አሠራሮች መጠናከር ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት መጠናከርም የዴሞክራሲያዊ ባህል መጠናከር ነው፡፡ የባህል ግንባታ ሂደት ደግሞ ጊዜን የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ባለፉት 27 ዓመታት የሀገራችን ዴሞክራያዊ ባህል እየተጠናከረ መሄዱን የሚያመለከቱ በርካታ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መወያየት ማይታሰብ ጉዳይ ነበር፡፡ አንዱ ሌላኛውን በጠላትነት የሚያይበት ሁኔታ ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ ባሩድ- ባሩድ በሚሸትና የፖሊሲ አማራጭ የማያሳይ የምርጫ ቅስቀሳ ውድድር የሚደረግበት ሁኔታም ነበር፡፡ አሁን ይህ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ቀደም ሲል፤ ከተቀናቃኝ ጋር ሲጨባበጡ መታየት ሆነ በጋራ ጉዳይ ላይ ለመምከር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ በፖለቲካ ድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን በህብረሰቡም ዘንድ እንደ ክህደት የሚታይበት ጊዜ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ አስተሳሰብ በእጅጉ ተለውጧል፡፡