የመደመር ጉዟችን ደወል ለመኸር ሥራዎቻችንም ይሁን !

በኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍሎች በመጪው ነሐሴ ወር  ነጎድጓድና በረዶ አዘል ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከሰሞኑ ማስታወቁን ሰምተናል። ኤጀንሲው በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ በመጪው ወር ዝናብ ሰጪና አልፎ አልፎም ለወንዞች ሙላትና ለቅፅበታዊ ጎርፍ መከሰት ምክንያት የሚሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች እየተጠናከሩ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቅፅበታዊ ጎርፍ ምክንያት የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መንሸራተት፣ የሰብል ማሳዎች በውሃና በደለል መሸፈን፣ የአረም መስፋፋት፣ የሰብል በሽታዎችና ተባዮች መከሰት ሊኖር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ለዚህ ዓይነቱ ጉዳት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አደጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ሊደረጉ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል።

በአንዳንድ ቦታዎች በሚጥለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ከፍተኛ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል የአየር ትንበያው አመላክቷል። በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢልባቡር፣ በሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ እንደዚሁም  በአዲስ አበባ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራል። ከዚህም ሌላ የአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ባህርዳር ዙርያ፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ እንደዚሁም ሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች  የሚጥለው የክረምት ዝናም ይቀጥላል። የትግራይ፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ዞኖች፣ ከደቡብ ክልል የከፋ፣ የቤንች ማጂ፣ የጉራጌ፣ የሀድያ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋና የሲዳማ ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

 

አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎች ስርጭቱ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለቅፅበታዊ ጎርፍ መከሰት መንስኤ ሊሆን የሚቸል ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ ኤጀንሲው አመልክቷል። ድሬዳዋና ሐረር፣ የአፋር፣ የአርሲና የባሌ ዞኖች፣ የጅግጅጋና የሽነሌ ዞኖች እንደዚሁም በአንዳንድ የደቡብ ኦሞ፣ የሰገን ህዝቦችና የቦረናና የጉጂ ዞኖች ከሚኖራቸው እርጥበት አዘል አየር በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ተበሎ ይጠበቃል። በመጪው ወር የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ አየር ይኖራቸዋል። ስለሆነም ይህን ትንተና መሰረት ያደረገ የመኸር እንቅስቃሴ ከመላው አርሶ አደርና የግብርና ልማት ሙያተኞች ይጠበቃል። በተጨማሪም አዋጩ መንገድ ይህንኑ ተለዋዋጭና የአለምን የበርካታ አመታት የተፈጥሮ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገውን የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት ያደረገ ትጋት ከመላው ባለድርሻዎች ይጠበቃል።

 

በኢትየጵያ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የአገሪቱን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከተነደፉት ስትራቴጂዎች መካከል የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ በሀገሪቱ ከሚተገበሩት ፕሮግራሞች መካከል “የተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም” አንዱ ነው። ፕሮግራሙ የተቀረጸው በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አነስተኛ ይዞታ ያለቸውን አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት በመድረስ በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ነው። ቀጥለውም ትርፍ አምርተውና የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው የተሻለ ገቢ በማግኘት ኑሯቸው እንዲለወጥ ለማስቻል ጭምር ነው።

 

የኘሮግራሙ ዋና ዓላማዎችም  የአየር  ንብረት ለውጥን በመዋጋት፣ ያለችውን አነስተኛ ማሳ ቴክኖሎጅን በመጠቀም መስኖን ተጠቅሞ በማረስ በአመት ሁለት ሶስቴ  በማምረት የምግብ ዋስትናን ማሻሻል እና  የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎችን በመተግበር የመስኖ ተጠቃሚዎችን የኑሮ ደረጀ በዘላቂነት ማሻሻል እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ። የገበያ ትስስርን፣ የሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊነትን ማጠናከር፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የተጋረጡትን ችግሮች መግታትና ለብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ አየር ንብረት ለውጥ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የፕሮግራሙ ትኩረት ነው።

ፕሮግራሙ በትግራይ ፣ በአማራ ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ  ክልሎች ውስጥ ባሉ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው እና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ 110 ወረዳዎች ውስጥ  የሚተገበር መሆኑም ተመልክቷል። ፕሮግራሙ በሶስት ዋና ዋና የክፍሎች የሚመራ ሲሆን እነሱም የአነስተኛ መስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ዘላቂ የግብርና ልማት እና የማናጅመንት፣ የክትትልና ግምገማ ስራዎች ናቸው። በዚህም 18 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን 108 ሺህ 750 አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። እስካሁን በፕሮግራሙ ጥናትና ዲዛይን ተሰርቶላቸው ግንባታቸው ከተጀመሩ ከ50 በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 20ዎቹ ተጠናቀዋል። በእነዚህ የመስኖ እውታሮችም 3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ 18 ሺህ አባወራዎች የተመረጡና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል። በሌላ በኩል የግብርና ሥራ በዘመቻ የሚመራ ሳይሆን በተቀመጠና በነጠረ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚመራ መሆኑን ያመላከተ ነውና የዘርፉ መጠናከር የሀገራዊ ለውጡ አንዱ እይታ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም  የዘንድሮው መኸር እንዳያመልጠን ወሳኝ በሆኑ አንዳንድ  ጉዳዮች ላይ ብንመክር ተገቢ ይሆናል።

ሀገራችን እጅግ ሠፊና የተለያዩ  ስነ-ምህዳሮች በተፈጥሮ የተቸረች ናት፡፡  በመሆኑም በኢትዮጵያውያን የተላመዱና የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑትን ጤፍ፣ ገብስ፣ እንሰት እና ሌሎችም ሀገር በቀል ሰብሎች መኖራቸው ሲታይ መልማት የሚችል እምቅ ሀብት እንዳለን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ የግብርና ሥራው ኋላ-ቀር በመሆኑ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥም ሆነ በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ መልኩ ለመቋቋም አላስቻለንም፡፡

ህዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ በሂደትም የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ መንግስትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ከመሆኑም በላይ አመርቂ ውጤት መገኘቱ ባለፉት አመታት ሲከሰት የነበረውን  ድርቅ በራስ አቅም የተቋቋምንበት ደረጃ በራሱ አብይ አስረጅ ነው፡፡  የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂው  ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬትና ውሃ እና ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑም ፤በሂደት ግብርናው የኢንዱስትሪ ግብዓት፣ የካፒታል ክምችት፣ የገበያ ዕድልና የጉልበት አቅርቦትን በማረጋገጥ ለከተማውና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉም አያጠያይቅም፡፡

የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ቢሆንም ዋናው አጀንዳግን  ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገትም ሆነ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ብሎም የመላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሻጋገር ነው፡፡ በዚህም በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ በግብርናው ዘርፍ የ6.6 በመቶ አማካይ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ለተመዘገበው የ10.1 በመቶ ዕድገት ግብርና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ይህ እድገት እንዳይዋዥቅ የተጠናከረ ስራና አጠቃላይ  የተቀናጀ ትኩረትን  የሚጠይቅ  ተግባር ነው፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተቀመጡ ግቦች አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ  ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ አርሶአደሩ ማሳ ላይ መሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመተግበር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚቻል የሚያረጋግጥ እና መላው አርሶ አደር በዚህ የመኸር ዝግጅት ሊከተለው የሚገባ የመጀመሪያው አቅጣጫ ነው፡፡  

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድም በዕቅድ ዘመኑ መነሻ የነበረውን 3.7 ሚሊዮን ሄክታር በተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሸፈነውን ማሳ ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር ለዚህ መኸር ጠቃሚ ተሞክሮ ይሆናል ። ይኸውም የህብረተሰቡ ሰፊና የተደረጃ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራው በእንስሳት ማድለብ፣ በግና ፍየል በማሞከት፣ንብ በማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚሊዮን ለሚቀጠሩ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ሥራ በስፋቱም ሆነ ህብረተሰቡን በማሳተፍና ተጠቃሚነተቻውን በማረጋገጥ ረገድ በአህጉሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በምርጥ ተሞክሮነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን መኸሩን ውጤታማ ያደርገናል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦትና ተጠቃሚነት  እየተሻሻለ መምጣቱ እና የእንስሳትና የሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ  የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡

ግብርናው በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየጎለበተ ቢመጣም  ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም በመኖሩ አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች አሉን፡፡ በመሆኑም ይህን ታሳቢ ያደረገ እና ይልቁንም ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችንን የሚጨምር ዝግጅትም ከወዲሁ ያስፈልጋል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ስለሆነም አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው ለመኸር ሰብል እንክብካቤ ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡ይኸውም በማሳ ላይ ያለውን  ሰብል የማረምና የመኮትኮት ስራን የሚያጠቃልል ነው፡፡የአረምና የኩትኳቶ ስራውን  ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ ጭምር ማከናወን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግና በዚህ መኸር ሁሉም ሊከተለው የሚገባ አቅጣጫ ነው፡፡የልማት ቡድኖችን በማጠናከር ከዘር ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ በጋራ መስራትም  ተገቢና ሊዘነጋ የማይገባው ነው፡፡ በልማት ቡድኖች አደረጃጀት የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በተናጠል ከሚከናውኑት በበለጠ ጊዜና ጉልበት ይቆጥባልና፡፡የጋራ ስራው ከሰብል ልማት በተጨማሪም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሚያካትት መሆንም አለበት፡፡ በቡድን ስራው ላይ ግንባር ቀደም አርሶአደሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትን አሰራር መዘርጋት ለመኸሩ ውጤታማነት ጠቃሚ ነው፡፡

የክረምቱ ዝናብ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በመጠንና በስርጭት እየተጠናከረ እንደሚሔድ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሰጠውን መረጃም ማስታወስ ተገቢ ነው። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አሁን እየታየ ያለው ዝናብ በአብዛኛው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በስርጭት እየተጠናከረ ይሔዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአገሪቱ ሰሜናዊ አጋማሽ ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል ይጠበቃል። አልፎ አልፎ በፀሐይ ታግዘው ከሚፈጠሩ ጠንካራ ደመናዎች ቅፅበታዊ ጎርፍና የወንዞችን ሙላት ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሊኖር ይችላል ብሏል።

በተጨማሪም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የዝናቡ አወጣጥ በመጠኑ ሊዘገይ እንደሚችል መተበዩን ነው የገለፀው ኤጀንሲው። ስለሆነም ይህ የአየር ሁኔታ በመኸር ወቅት ለሚመረቱ ለመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሰብሎች ዕድገት፣ ለቋሚ ሰብሎች የውሃ ፍላጎት፣ ለአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመጠጥ ውሃና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አዎንታዊ ገጽታ እንዳለው ማጤንና በጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ።

ከዚም ባሻገር እንደትንበያው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ምክንያት ውሃ ማሳ ላይ እንዳይተኛ ቦይ በማውጣትና በማንጠፍጠፍ የመከላከል ስራ ማከናወን ከመኸር ዝግጅቶቻችን ዋናው ሊሆን ይገባል። ከግብርና ባለሙያዎች በሚገኙ ምክረ ሐሳቦች በመደገፍ አረምን በወቅቱ በማረም፣ ፀረ-አረምና ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ በመጠቀም ጥንቃቄ ማድረግም በተመሳሳይ። በትንበያው መሰረት በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩና የሚመለከታቸው አካላት በሰብሎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ሊቦዝኑ አይገባም ። በአንፃሩ በቆላማ የሀገሪቱ ቦታዎች የተገኘውን እርጥበት በአግባቡ በመጠቀምና የውሃ እቀባ፣ የኩሬ ማጎልበትና የዝናብ ውሃ መሰብሰብ ስራዎችን ማከናወን የመኸር ዝግጅቱ ቁልፍ ተግባራቶች ሊሆኑ ይገባል።