የተቀነሰውን ደምረን ያለውን ማቆየት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ከተመረጡና በፓርላማ ከተሰየሙ ጊዜ ጀምሮ፣ አገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረው የሥጋት ደመና ተገፏል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት ከሕዝብ ጋር እያደረጉ ባሉት ውይይትም ይህ እውነታ በሚገባ ተንፀባርቋል፡፡ እሳቸው እያስጀመሩ ያሉትን የለውጥ ሒደት በመደገፍ ሕዝብ በግልጽ እየተናገረም ነው፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ የሚታሰበው ሕዝብ የለውጡ አካል ለመሆን ቁርጠኝነት ሲያሳይ፣ የለውጡን ሒደት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ መኖራቸውም በስፋት ተስተውሏል፡፡

 

አሁን ኢትዮጵያን ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልጋት ልጆቿ በእኩልነት ሊያኖራቸው የሚችል ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንደሆነ መላው ህዝብ የተስማማ መሆኑን በድጋፍ ሰልፎቹ አረጋግጧል። ይህ ጠንካራ አንድነት ልዩነቶችን እያስተናገደ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት መሆን ያለበት መሆኑን የዘነጋ አካሄድ ፤ ይልቁንም የማህበራዊ ሚዲያው ሰጣ ገባ ለውጡን ለሚያደናቅፉ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑም እየተስተዋለ ነው፡፡ ልዩነትን የማያከብር እንዲህ ያለው አካሄድ አንዱን ወዳጅ ሌላውን ጠላት እያለ የሚፈርጅ አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ለለውጥም የማይበጅ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ነው፡፡

 

የለውጡ  ጅምር ስለጥላቻ ሳይሆን ስለፍቅር፣ ስለመለያየት ሳይሆን ስለአንድነት ወይም መደመር፣ ስለበቀል ሳይሆን ስለይቅርታ  የሚያስተምር  ነው። መላው ህዝብ ድጋፉን አደባባይ ወጥቶ የሰጣቸው  ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን አስተምህሮአቸውን እየተገበሩም ነው፡፡ የታሰሩትን ፈተዋል፡፡ የታመሙትን ጠይቀዋል፡፡ የተሰደዱትን መልሰዋል፡፡ ይቅርባይነት ይኼ ነው፡፡ ለፍቅር ሲሉ ከሃያ ዓመታት በላይ የተለያዩትን የኤርትራንና የኢትዮጵያን የከረረ የጠላትነት መንፈስ አስወግደው ዕርቀ ሰላም ለማውረድ፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዘዋል፡፡   

 

ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም ማውረድና ተከባብሮ ለመኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገባቸውን አድርገዋል፡፡ ይኼን ጅምር ማስቀጠል የሚቻለው ደግሞ በዚሁ መርህ የተቃኘ ህዝብና ደጋፊ ሲኖር እንጂ የይቅርታን ልክ በዘነጋ ጥላቻና መሃል ሰፋሪነት አይደለም።

 

ባሳለፍናቸው ሶስት ወራት እንኳ ይህን የመሰለ የይቅርታ ዘመን በአግባቡ መጠቀምና ማስቀጠል አቅቶን ብዙ ጊዜ ከመንገድ እየወጣን፣ ብዙ ኪሳራ አስከትሎብን አገሪቱን ወደ ኋላ የሚያንሸራትቱ ተግባራት ፈጽመናል፡፡አሁን ባለንበት ደረጃ ሕዝቡ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት ቃል እየገባ ነው፡፡ ይቅርታን፣ ሰላምንና መደመርን በአባባል ደረጃ የጋራው አድርጎታል፡፡ በርካቶች ግን በማህበራዊ ሚዲያ መቀነስን እና ጥላቻን በተግባር እየሰበኩ ነው። ካልገባን ማቆምን የመሰለ ነገር እያለ የአደናቃፊው ሰለባ መሆን እንዴት ያለ ኋላ ቀርነት ነው ያስብላል።

 

ይቅርታ ማድረግ ማለት የሚወዱትን ሰው የበለጠ መውሰድ አይደለም፡፡ ይቅርታ የሚደረገው ላስቀየሙንና ላስቀየምናቸው ነው፡፡ለወዳጅ የሚያስፈልገው ፍቅር እንጂ ይቅርታ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ ለተየቀምናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይቅርታ ካላደረግን በጥላቻና በፀባችን ለመፍረስ እየተንደረደርን መሆኑን ልንገነዘብ እና ልናጤን ይገባል፡፡ እንዲህ ያለው ቀልድ መሰል ሰጣ ገባ ወዳልተጠበቀ ቀውስ፣ ገፋ ሲልም ወደ እርስ በርስ ግጭት እያመራ እስከ ዛሬ ድረስ በድቅድቅ ጨለማ እንድንኖር ያደረገን ስለመሆኑ ከኛ በላይ መስካሪስ ከየት ሊመጣ ነው፡፡ ቃል የተገባለትን የፍቅር ድልድይ ለመገንባትና የለያዩንን አጥሮች ለማፍረስ በመጀመርያ ይቅርታ ይቀድማል፡፡ ይኼን ካደረግን እንደ ሕዝብ የሚገባንን ሠርተን የመሪያችንና የአጋሮቻቸውን ራዕይ ተገበርን ማለት ነው፡፡አልያ ግን መደመርን እየዘመርን መቀነስን የምናሸበሽብ ከሆነ እዳው የትየለሌና ከባድ ነው።

 

አንዳንዶቻችን በአንድ ወቅት በሆነ አጋጣሚ የተቀየምናቸውን ወገኖች የማግለል ባስ ሲልም የጥላቻ ስሜት እናሳያለን፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር አመክንዮ አዲስ ጨምረን ነባሩን መቀነስ አይደለም፡፡ መደመር የተቀነሰውን ደምረን ያለውን ማቆየት ነው፡፡

                    

አሁን ተስማምተን ድጋፋችንን በሆታና በጭብጨባ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የገለጽን ሁሉ ራሳችንን ልንመረምር የሚገባን ሰዓት ላይ ስለመሆናችን የሚያጠይቁ የጥላቻ ሰጣገባዎችን እያየን ነው፡፡ ይቅርታ እንዴት ፍቅርንና ሰላምን እንደሚያመጣ ከሰሞኑ በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትን ተመልክተን ስናበቃ እዚህ በቤታችን ደግሞ ለመቀነስ እየተሯሯጥን መሆኑን መመልከት የተለከፍንበት በሽታ ምን ያህል ስር እንደሰደደ የሚያረጋግጥ ነውና በቶሎ እንታከም፡፡  

 

መንግሥትን ምልዓተ ሕዝቡ ደግፎታል ማለት የሚቃወመውና የሚጠላው የለም ማለት አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ በየትም አገር ያለ ነው፡፡ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስተት የሚያሳየንም ይህንኑ ነው፡፡ ጋንዲና ኬኔዲን የመሳሰሉ ንፁኃን ተወዳጅ መሪዎችም የዚህ ዓይነቱ የጥላቻ ሰለባዎች ናቸው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን ለመምራት በቂ ዕውቀት፣ ፍላጎትና ተነሳሽነት አላቸው፡፡ አሁን ያሉበትን የርዕሰ መስተዳድር ኃላፊነት ለመከወን እንዲያስችላቸው እሳቸው በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ከፍተኛ የሕዝብና የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አገርን መምራት የሚቻለው በፍቅርና በምሕረት ቢሆን ተመራጭና ጥሩው መንገድ ነው፡፡

 

ለመጀመርያ ጊዜ ፍቅር ሁሉን ነገር እንደሚያሸንፍ ምሕረት ማድረግ የዕለት ተግባራችን እንዲሆን ዓለምን ያስተማረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን እሱ ያስተማራቸው ሰዎች በመሆናቸው ከሰው ባህሪ በሚመነጭ ተንኮል እሱኑ ገድለውታል፡፡ ግን ገዳዮቹን ይቅር ብሏል። ይኼ የሆነው የፍቅርና የይቅርታን ልክ እኛ እንድማርበት የተፈጸመ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለሆነም የጠቅላያችንን የመደመር አመክንዮ በዚህም ደረጃ ማሰብ ተገቢ ይሆናል። 

 

የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ያልተረጋጋና የተወሳሰበ በመሆኑ፣ የመንግሥታችን አካሄድ ሁልጊዜ ያለፉትን ሁኔታዎች በጥልቀት በመመርመር ዳግም ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ በመጀመርያ መጤን አለበት፡፡ ምንም እንኳን በሕዝብና በመንግሥት መናበብ አገሪቱ ከአደጋ እየራቀች ነው ብንልም፣ አሁንም ተግዳሮቶች ስላሉ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ሁከትና ያለመረጋጋት በሁለቱ ክልሎች መሀል በሚደረግ ውይይት መግባባት ይፈጠራል ተብሎ የተኬደበት ቢሆንም፣ ሁኔታው የመሻሻል ምልክት እንኳ ባለማሳየቱ የግድ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነትን ሽቷል። በጉጂና ጌዲዮም በተመሳሳይ። አሁን እየተደረገ ያለው የጥላቻ ሰበካ ደግሞ ወደሌላም አቅጣጫ ማስፋትን ያለመ ነው። ከመደገፍና ከመቃወም አስቀድሞ ዳር አገር ከሌለ መሀል አገር ዳር እንደሚሆን ማስተዋል ይገባል ፡፡

 

ነባር የኢሕአዴግ ታጋዮችም ቢሆኑ በተለያየ ምክንያት ከነበሩበት ኃላፊነት ቢነሱ ምንም የሚያስከፋ ነገር የሌለ በመሆኑ ለለውጡ ሲባል መቀበል ግዴታ ነው፡፡ በጡረታ መገለል፣ ከሥልጣን መሻር፣ መታሰርና መሞት ጭምር በራስ ላይ ሲደርስ ይከብዳል እንጂ ከዚህ ባነሰ ወይም ያለምንም ጥፋት የታሰሩ፣ የተሰደዱና የሞቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ማንም ሹም ቢሆን በዕድሜው የመጨረሻ አካባቢ የሚያስደስተው ነገር ቢኖር በክፉ ጊዜ የሰራው መልካም ሥራ ስለሆነ፣ እናንተም በዚህ እየተፅናናችሁ ወደ መደመር ብትመለሱ ለመላው አገሪቱም ሆነ ለእናንተ የተሻለ ነው፡፡ በተረፈ የፌስቡክ አርበኞችን ችላ ማለት ነው፡፡ መንግስትም የተቀነሰውን መደመር ብቻ ሳይሆን ያሉትን በማቆየት የመደመር ስሌት ቢያስተናግዳቸው እየተሳቀቅን ካለንበት ጊዜ ያሻግረናል።

 

ከዚያ ባሻገር ግን አገር ከምንም ነገር በላይ ስለሆነች ለተጀመረው ለውጥ ቢቻል ደጋፊ መሆን፣ ካልተቻለ ደግሞ አደብ መግዛት ይመረጣል፡፡ከለውጡ ጋር መራመድ የተሳነው ካለም ወይ ራሱን ማደስ ይኖርበታል፣ ካልሆነም አደናቃፊ እንዳይሆን መቆጠብ አለበት፡፡ ይኼንን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ተስፋ የሰነቀ የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል መሞከር ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፡፡ ለእናት አገሩ ከፍተኛ ፍቅር ያለው ሕዝብ አገሩ ለሦስት ዓመታት ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እያየች በመሆኑ፣ ከዳር እስከ ዳር ደስታውን እየገለጸ ነው፡፡ 

 

አገር ላይ ያንዣበበው ሥጋት ተገፎ ኢትዮጵያዊያን መጪውን ጊዜ ለማሳመር በቀና መንፈስ በአንድነት ለመነሳት መልካም ፈቃዳቸውን ሲያሳዩ፣ ለሕዝብ በማይገባ አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ ወደኋላ ለመመለስ የሚፍጨረጨሩ ካሉ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እየታደስኩ ነው ብሎ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ወደ ኋላ ለመመለስ ማንገራገር ዕርባና ቢስ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕዝብ ጋርም የመረረ ፀብ ውስጥ ይከታል፡፡

 

ለውጡ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አስተማማኝ አንዲሆን ደግሞ መደጋገፍ ይገባል፡፡ ይኼ መደጋገፍ ጥቅም ያስገኛል፡፡ የአገሪቱን አንፃራዊ ሰላም ይመልሳል፣ የሕዝቡ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል እንዲመለሱ ይረዳል፣ የሕዝቡን በአንድነት የመኖር ፀጋ ያጠናክራል፣ ለአገር ዕድገትና ለጋራ ጉዳዮች መግባባት ይፈጥራል፣ የነገውን ቀና ጎዳና በኅብረት ለመተለም ዕገዛ ያደርጋል፡፡

 

ለዚህ ስኬት አገሪቱ የተረጋጋ አመራር እንዲኖራት ያስፈልጋል፡፡ መምራት ማለት መራመድ ሲሆን፣ አንድ ቦታ ቆሞ ለመምራት መሞከር አይታሰብም፡፡ አመራሩን አላንቀሳቅስ የሚሉ እንከኖች ሲፈጠሩ ለውጥ ይደናቀፋል፡፡ በፓርቲ ውስጥም ሆነ በአገር ደረጃ ለለውጥ የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ ሲገባ፣ እንቅፋት መሆን አገርን ለሌላ ዙር ቀውስ ማመቻቸት ነው፡፡ ቁማር እንደተበላ ቁማርተኛ እየተነጫነጩ የለውጥ ሒደቱን መራገምና ጨለምተኛ መሆን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡