በፍቅር ሁሉም ይቻላል…!

ለአንዲት አገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት በሌሎች አገራት የሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎች ሚና በቀላል የሚገመት አይደለም፡፡ በርካታ አገሮችም በሌሎች አገራት ከሚኖሩ ዝጎቻቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን እንደ ዕድል ሆኖ የዲያስፖራ ኮሙኒቲው በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገሩ ሪቆና በአገሪቱ የነበረውን ፖለቲካ በመቃወም ከብዙ ጉዳዮች ተቆጠቦ እንደነበርና ከዚያም በላይ በሰው አገር እየኖረ እርስ በርሱ ተጠማምዶና በጠላትነት እየተያየ አመታትን ገፍቷል፡፡ 

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ አዲስ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ቀደም ሲል ነበረውን ችግር ለመፍታት ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበአለ ሲመታቸው ወቅት አጽንኦት ሰጥተው ከተናገሯቸው ቁምነገሮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፍቅርን፣ እርቅን እና መደመርን አስመልክቶ ያደረጓቸው ንግግሮች በሀገር ቤት ያሉትን ዜጎች ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀልብም የሳበ ነበር፡፡

የመንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞም በሀገሪቱ እየተካሄዱ ያሉት ለውጦች ተስፋ ሰጭ በመሆናቸው ዲያስፖራው መደመርን መረጧል፡፡ ሁሉም በጥላቻ ሲተያይ የነበረው የኢትዮጵያ ዲያሲፖራ በአሁኑ ወቅት አንድ ልብ ሆኖ አገሩን ለማገልገል ዝግጁነቱን በተለያየ መልክ እየገለጸ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኗቸውን ተግባሮች በማድነቅ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ባካሄዱበት ወቅትም ለተለያዩ ጉዳዮች በሀገሪቱ የተገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለይ በአዲስ አበባ የተካሄደውን ሰልፍ ተቀላቅለዋል፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ በያሉበት ሀገር ሆነው ሁነቱን ተከታትለውታል፡፡

ይህ ሁሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባልተለመደ መልኩ አንድ ያደረገ ተግባር በተለያዩ ምክንያቶች ሸፍቶ የነበረን ልብ የመለሰ ነውና ታላቅ ክንውን ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ እርምጃዎችንም እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡

በሀገሪቱ የጠበበ የፓለቲካ ምህዳር ሳቢያ በውጭ ሀገር ሆነው የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የፓለቲካ አቋማቸውን ሲያራምዱ የቆዩ ወገኖች ወደ ሀገራቸው ገብተው አመለካከታቸውን እና የፓለቲካ አቋማቸውን የሚያራምዱበት መደላድል ተፈጥሯል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ከማቅረብ በተጨማሪ በወንጀል የሚጠየቁም ካሉ በይቅርታ እንዲገቡ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች ሳይቀሩ ፍረጃው ተነስቶላቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በርካታ የፓለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ፓለቲከኞች ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡ መንግስት እነዚህ ወገኖች ሲመጡም ደማቅ አቀባበል ጭምር አድርጎላቸዋል፡፡

በዚህም ሳይወሰን ከፓርቲዎቹ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓለቲካ አቋማቸው ሳቢያ ሀገራቸውን ጥለው ለበርካታ አመታት ኑሯቸውን በውጭ ሀገሮች ያደረጉ ፓለቲከኞችን ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች አነጋግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት ሀገሮች እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝቶችን ያደረጉ ሲሆን፣ እስረኞችን ከማስፈታት ባለፈ እርሳቸው በሚጓዙበት አውሮፕላን በማሳፈር ወደ ሀገር ቤት መልሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ መንግስት ብዙ ርቀት በመጓዝ የወሰደው እርምጃ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሀገራቸው ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ የጀመሩት ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ደግሞ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በመገኘት የወንዝ ልጆቻቸውን እያነጋገሩ ይገኛሉ፡፡

ጉብኝቱ እግረ መንገድ የተካሄደም አይደለም፡፡ ይህ መንግስታዊ ግንኙነትን መሰረት ያላደረገ ዜጎችን እና ዜጎችን ብቻ የተመለከተ ጉብኝት በአይነቱም ልዩ ሊባል የሚችል እንደመሆኑ፤ የመንግስትን ለዜጎች ትኩረት መስጠት በሚገባ ያመለክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ከሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ከፓርቲዎቹ አመራሮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅትም ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አጥብቀው እንደሚሰሩ በማረጋገጥ ፓርቲዎቹ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል፡፡

ጉብኝቱ በሚገባ የተቀናጀ፣ ደማቅና በርካታ ቁም ነገር የተገኘበትም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ከ25 ሺ በላይ ዜጎችን በዋሽንግተን ዲሲ ማገናኘት ያስቻለና ጠንካራ መልእክትም የተላለፈበት ነው፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ ሀምሌ 21 በተካሄደው ታላቅ መድረክ የከተማው ከንቲባ ጭምር የተገኙ ሲሆን፤ እለቱ በየአመቱ የኢትዮጵያውያን ቀን በሚል እንዲከበር በከንቲባዋ ተሰይሟል፡፡ ጉብኝቱ በሌሎች ሁለት የአሜሪካ ግዛቶችም ተካሂዷል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንደመኖራቸው ፣በመድረኩ ከአሜሪካ ውጭ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገሮች የመጡ ዜጎች የተሳተፉበት እንደመሆኑ ውጤታማ ሊባል የሚችልም ነው፡፡ የመደመር ጉዞ የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝት ብዙ ተደክሞበት በኢትዮጵያ ኤምባሲና

በኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተሰናዳ ሲሆን፤ ስኬታማ ተብሎ ሊወሰድ የሚችልም ነው፡፡ በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ቆይታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ በሚገኝበት አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች ለቀናት የተደረገ መሆኑም ዜጎች ሀገራቸውን አስመልክቶ በቂ መረጃ እንዲይዙ የሚያስችል ሀገሪቱ በሬሚታንስ፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎችም ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ውጤታማነት የሚያግዝ ይሆናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙትን ትረስት ፈንድ ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ከመድረኩ ተሳታፊዎች ማረጋገጫ ተገኝቶበታል፡፡ እስካሁን ድረስ ዲያስፖራው ለአገሩ ያደርገው የነበረው ድጋፍ በከፊል ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ልዩነት ተወግዶ ሁሉም በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው አገራቸውን የሚረዱበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአሜሪካ ያሉት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል እየገቡ የገኛሉ፡፡

ለአብነት ያህል በቅርቡ በዱባይ የተካህደውን ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ሰልፍና አገራቸውን ለመደገፍ የገቡትን ቃል መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ በመንግስት በተለይም ደግሞ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጥረት የተገኘ ውጤት ነው፡፡

እርቅን፣ ፍቅርን ኢትዮጵያዊነትን አጥበቀው ለሚያቀነቅኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ ሁሉም በላይ ይሆናል፡፡

በተለያየ የፓለቲካ ቡድን ፣ በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለው የሚኖሩትን እነዚህን ዜጎችም ወደ አንድ ያመጣ እንደመሆኑ መቼም ያልተደረገ የሚስተካከለው የሌለ አብይ ጉብኝት ነው፡፡ ፍቅርና ትህትና የማይገዛውና የማያንበረክከው ነገር እንደሌለ እስካሁ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረጓቸው ጥረቶችን የተገኙ ስክቶች መማር የቻላል፡፡