ምርምሮች ያስገኙት ውጤቶች

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የእንስሳት ሀብት ብዛት ያላት አገር ስትሆን ከነዚህ መካከል ወደ ስድሳ ሚሊዮን የሚጠጋ የቀንድ ከብት ሲኖራት ይሄ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ በሌላ በኩል ወደ ሦስት መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ የበግ ሐብት ሲኖራት ይሄ በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ የፍየል ሐብቷም ከበግ ሀብቷ ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን በዚህም በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም ስምንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው አገሪቱ በርካታ የእንሰሳት ሀብት ቢኖራትም ከቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ የእንሰሳት ሀብት ያነሰ ቁጥር ያላቸው አገሮች እንኳን ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ የሚያገኙት ገቢ በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በእውቀት ላይ የተመሰረተ የምርምርና ምርት ልማት አቅም በማሳደግ ጥራትና ብዛት ያለው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት አምርተው ለዓለም ገበያ በማቅረባቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ልዩ ባህርይ ከተጎናጸፋት የእንስሳት የቆዳ ሀብቶቿ ተጠቃሚ እንድትሆን የምርምርና የምርት ልማት አቅም መገንባት እንዳለበት ስለሚታመን በዘርፉ እውቀት ያላቸውን ቴክኖሎጂስቶችና ሳይንቲስቶችን ማብዛት አንዱ የትኩረት መስክ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሙያዎች በፒኤች ዲ እና በማስተርስ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ምርምርና ምክር አገልግሎት ገብተው ይገኛሉ፡፡ ከሃያ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዚህ የትምህርት ዘመን በማስተርስ ዲግሪ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ዘርፉ ይሰማራሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች የአቅም ግንባታ ሥራዎች የባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ የሀገራችን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው የሚያስገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አሁን ከሚገኘው በብዙ አጥፍ የበለጠ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየው የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የጥራትና ብክነት ችግር እንዲቀረፍ ከተደረገ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት የሚበረታቱ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ ፋብሪካዎችም ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ስለሚያነሳሳቸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡

ከዘርፉ የሚገኘው የኤክስፖርት ገቢም በከፍተኛ ሁኔታ ሊያድግ እንደሚችል ይታመናል፡፡ የሚገነባው የሰው እውቀት ካፒታል ኢትዮጲያን በቆዳ ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን ስለሚያደርግም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሰልጣኞችና ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሊመጡ ስለሚችሉ ለአገር የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቀላል አይሆንም፡፡ ከአገሮቹ ጋር ሊኖር የሚችለው ግንኙነትም የበለጠ ሊጠናከር ስለሚችል የኢትዮጵያን የቆዳና የቆዳ ምርቶች ለነዚህ አገሮች በብዛት በመላክ የአገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል፡፡ 

መንግሥት የእንስሳት ቆዳ ዘርፍን ለማሳደግ የህግ ማእቀፍንና የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ እንዲኖር በማድረግ የኢንቨስትመንት ህጎችን እንዳአስፈላጊነቱ በመለወጥ፣ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ማሻሻል፣ ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስፈልገውን የገበያ ተኮር የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቀየስ እና በቁርኝት የዘርፉን አቅም በማጎልበት ረገድ ቁርጠኛ አቋም አለው፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የሀገራችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ገና ብዙ ይቀረዋል ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች ውስጥ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችም የቆዳውን ዘርፍ ከማሳደግ አንጻር በየጊዜው የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ያካሂዳሉ ከእነዚህም ውስጥ በ2007 ዓ.ም ምክትል ዋናዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሁሴን በሞዴል ፈጻሚነት የተሸለሙበትን ቀደም ካሉት ሥራዎች ማንሳት እንችላለን፡፡

ምርምሩም ትኩረት የሚያደርገው በዋንኬ በግሌጦ ላይ ሲሆን እነዚህም በጎች በምስራቁ የአገራችን ክፍል በተለይም በሱማሌ ከልል ኦጋዴን አካባቢ የሚገኙ ሲሆን አንገታቸው ጥቁር ሌላው አካላቸው ደግሞ በሙሉ ነጭ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ሌጧቸው ስብ የሚበዛበት ከመሆኑ በላይ ስስ ነው፡፡ አካባቢው ቆላ በመሆኑ ሌጦው ላይ ያለው ጸጉር አጭር ሲሆን በዚህም የተነሳ ጭረት ይበዛበታል፡፡ እነዚህ የበግ ዝርያዎች በድርቅ ምክንያት የተጎዱ በመሆናቸው የጎድን አጥንታቸው ምልክት በምርት ሂደት ላይ ጎላ ብሎ ይታያል፡፡ በአጠቃላይ በተፈጥሯዊ ግድፈቶች የተነሳ የዋንኬ በግ ሌጦ በቆዳ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ በተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ዘንድ እምብዛም የማይፈለጉ ሲሆን ጥቅም ላይ ከዋሉም ለጫማ ገበር ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ የጥሬ ሌጦ ዋጋቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በቀድሞው ምህንድስና አቅም ግንባታ ፕሮግራም እንዲሁም የህንድ አቻ ተቋማት የሆኑት ማዕከላዊ የቆዳ ምርምር ኢንስቲትዩት እና የጫማ ዲዛይንና ልማት ኢንስቲትዩት መካከል በ2003 በጀት ዓመት የቁርኝት ፕሮጀክት የውል ስምምነት ፊርማ ተፈርሞ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ አንዱ ትኩረት የተሰጠው በዋንኬ በግ ሌጦ ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል የምርምር ስራ መስራት ነበር፡፡

በቀረበው የምርምር ምክረ ሀሳብ ለጥናቱ ከተመረጡት ባለሙያዎች አንዱ በመሆን ለሦስት ወራት ህንድ በመቆየት ጥናቱን አካሂደዋል፡፡ ከህንድ ከተመለሱም በኋላ አገር ውስጥ ለስድስት ወራት ምርምሩን በማካሄድ የሚያበረታታ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ በተለይም የቆዳውን ይዘት በተመለከተ ኬሚካል፣ ፊዚካልና ህብረ ህዋስ በማጥናት ወደ እሴት መለወጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ እና በጫማና በቆዳ አልባሳት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ምርምር ተካሂዷል፡፡

የምርምር ውጤቱም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ምርምሩ ችግር ፈቺ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ከምርምሩ በመነሳት የራሳቸውን የምርት ማልማት ስራ በመስራት የእጅ ጓንት ኤክስፖርት ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የቆዳ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላትና የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት የተደረገባቸውን ሁለት የምርምር ውጤቶች ማንሳት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በአቶ ወገኔ ደምሴ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ የቆዳ ጓንትን በመጠቀም ስልክን መጠቀም የሚያስችል የምርምር ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተደረገ ድጋፍ የቆዳ ጓንት በመጠቀም ጓንቱን ማንሳት ሳያስፈልግ የኤሌክትሪክ ግፊትን ወደ ሞባይል ስልክ ማስተላለፍ እንደሚቻል በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ለምርምሩ የሚያስፈልጉ የኬሚካል ግብአቶችም በቀላሉ የሚገኙና የአካባቢ ብክለትን የማያስከትሉ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

ከዚህም በላይ ይህ ፈጠራ በቆዳ አመራረት ውስጥ ከአነስተኛ የቆዳ ዘርፍ እስከከ ፍተኛ የቆዳ ምርት በማሸጋገር ለህክምና፣ ለመዝናኛ እና ለውትድርና ተግባራት ማዋል ይቻላል

ሌላኛው በኢንስቲትዩቱ ኢንቫይሮመንታል ዳይሬክቶሬት የቀረበ ሲሆን ይህም በቆዳ ማምረት ሂደት ውስጥ የሚወገዱ ተረፈ ምርቶችን ከቃጫ ጋር በማቀላቀል ጥቅም ላይ የማዋል ስራ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው ምርትም ለቤት ውስጥ ግርግዳ መከፋፈያ፣ ለኮርኒስ እና ለጫማ ገበር እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላል፡፡

በዚህም መሰረት በኢንስቲትዩቱ እስካሁን የተሰሩት የምርመር ሥራዎች አመርቂ ውጤት ያሳዩ ቢሆንም ኢንስቲትዩቱ ዘርፉን ከመደገፍ አንጻር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ የባለሀብቱ፣ የባለሞያው፣ የትምህርትና ምርምር ተቋማት በአጠቃላይ የሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረትና ቅንጅታዊ አሰራርወሳኝ ስለሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት