በሠላምና መረጋጋት፤ ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት

ኢትዮጵያ ንጉሳዊና አምባገነናዊ የአገዛዝ ስርዓትን አስተናግዳ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ  ስርዓት አቀንቃኝ ከሆነች 27 ዓመታትን አስቆጠረች፡፡ በተቆጠሩት 27 ዓመታት ውስጥ ዲሞክራሲን ትካነው ዘንድ  በዜማ፣ በግጥምና በውዝዋዜ ሞክራዋለች፡፡ ዲምክራሲ በሀገሪቷ ውስጥ ተዘርቶ፣ አብቅሎና አብቦ ፍሬ እንዲያፈራ የተደረጉት ልምምዶችና ትግበራዎች የማይካድና በብዙ መልኩ ሊመነዘር የሚችል አዳጊ ለውጥና  ውጤት አምጥተዋል፡፡  ለውጡ ለውጥ እየፈለገ፣ እድገቱ  ሌላ እድገት  እየሻ፣ ዘመኑ ፍላጎትን እየጨመረ በመምጣቱ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የሀገሪቷ ሰላምና ፖለቲካ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡

ሀገሪቷን ከወደቀችበት አደጋ ለማውጣት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የመጨረሻ አማራጭ በመውሰድ በሰላማዊ መንገድ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ የመፍትሄ እርምጃው የአመራር አካላትን በመቀየር ተጀመሮ  የአመራር ጥበብ እና የፖሊሲ ለውጥ ስለታከለበት ለሦስት ዓመታት በቀውስ፣ በአለመረጋጋት፣ በመጠራጠር፣ በስጋትና በመፈራራት ስትናወጥ የነበረችው ሀገር በሦስት ወራት ውስጥ በፍቅር፣ በሳላም፣ በመረጋጋት፣ በአንድነት፣ በይቅር ባይነትና በመደመር  ማዕበል ተናወጠች፡፡  ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ  መንግስት ባካሄዳቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተገኘው ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት ያልገባበት ቤት፣ ያልሰረፀበት የሰው አእምሮ ስለሌለ በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ነገር በመጻፍ የአንባቢዎቼንም የእኔንም ጊዜ ማባከን አልፈልግም፡፡

በአሁኑ ሰዓት ተቋማት ከተቋማት ጋር፣ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የህግ ማስከበር ሥራ እየተሰራ ስለሆነ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የአትክለትና ፍራፍሬ እንዲሁም የምግብ ምርቶች ዋጋ መቀነስ እያሳየ በመሆኑ ሀገራዊ የግብይት ስርዓቱ እየተረጋጋ ይመስላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጪ ሆኖ የቆየው የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦትም የነበሩበት የአቅርቦትና የስርጭት ችግሮች ተፈተው በተቀመጠው አሰራር መሰረት እየቀረቡ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው የዳቦ ስንዴ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረትና በቅንጅት በመሰራቱ  በአቅርቦቱ ላይ መሻሻል እየታየ ነው፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የውጪ ምንዛሪ ገንዘቦች ወደባንክ መመለስ መጀመራቸው ሰላማችን ለኢኮኖሚያችን የሰጠው ሌላው ዋስትና መሆኑን የምንረዳበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአማካኝ አራት ሚሊዮን ዶላር ወደ ባንክ እየገባ ይገኛል፡፡ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አዎንታዊ ጫና እንዲያሳርፉ የዲያስፖራ አካውን ተከፍቶ መቆጠብ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጋር የፈጠረችው አዲስ ግንኙነት ተሰሚነቷንና ተቀባይነቷን እየጠነከረላት መጥቷል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የፈጠረችው ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነት አማራጪ ወደቦችን እንድትጠቀም ያስቻላት ሲሆን የወደብ አማራጮች መስፋት ደግሞ በሀገራችን ገበያና ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥረውን የሎጂስቲክስ እና የትራንስፖርት ወጭ ይቀንሳል፡፡

ከሰላማችን በተጨማሪ ለግብርናችን ዘርፍ በቂና ተስማሚ የሆነው የክረምት ዝናብ ለኢኮኖሚያችን መነቃቃትና እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ የኢኮኖሚያችን ነጭ የደም ህዋስ እንደመሆኑ መጠን ተፈጥሮ የለገሰችን የክረምት ዝናብ በቀጣይ የግብርናው  ምርት እንዲጨምር ያደርጋል፤ ተያይዞም ተጨማሪ የሥራ ዕድልና የገበያ መረጋጋት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡

ሀሳቤን ሳጠቃልለው በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጣራል እንዲሉ አሁን እጃችን የገባው ሰላምና መረጋጋት እንዳያመልጠን መጠበቅ፣ መንከባከንና ማስቀጠል ይገባናል፡፡ ይህንን ወደተግባር መለወጥ የሚችለው ደግሞ በእኔ፣ በአንተ፣ በአንች፣ በእናንተ፣ በድምሩ በእኛ ነው፡፡ የእኛ ሠላም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትም ሲተርፍና ሲጠቅም ስላየነው እነሱም እንዲጠብቁትና እንዲያከብሩት አስቀድመን እኛ ለእኛ ሠላም ዘብ ቆመን የብጥብጥና የሁከት መነሻ በሮችን መዝጋት አለብን፡፡

በሀገራችን የተፈጠረው ሠላምና መረጋጋት አስከትሎት የመጣው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ላይቀለበስ ወደፊት የሚቀጥለውም በእኛው ተዋናይነት ነው፡፡ መንግስት ባደረገው ሀገራዊ ጥሪ በህገ-ወጥ መልክ ሲዘዋወሩ የተያዙ የውጭ ምንዛሪዎች ወደ ባንክ መግባታቸውና ቀጣይም የውጪ ምንዛሪ የማግኘት እድሉ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በባንክ ስርዓት እንዲያንቀሳቅሱት የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሀገሪቷ ወገቧን ይዞት ከነበረው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሊያላቅቅ የሚችል ስለሆነ የተጀመሩትና በጥቂት ጊዜም ቢሆን ለውጥ የታየባቸው ሥራዎች ይበልጥ ተበረታተው መቀጠል አለባቸው፡፡