አማራጭ የሌለው አማራጭ

በአገራችን ሰላምን፣ ልማትን እና ዴሞክራሲ ለማጠናከር ሲባል የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የህግ የበላይነትን በማስፈን ብቻ ነው። ለውጡን ለማስቀጠል እና ከዳር ለማድረስ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው አማራጭ መሆኑ አይካድም።

ዜጎች ድጋፋቸውንም ይሁን ተቃውሟቸውን ሲገልጹ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ መሆን ይገባዋል። ከዚህ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ መሆኑና ይህም ፍጹም አፍራሽና የተጀመረውንም ሊያደናቅፍ የሚችል ተግባር ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች በድጋፍ ሥም የሚካሄዱ ሰልፎችን ተገን በማድረግ በአመራሮችና ህጋዊ ተቋማት ላይ ጥቃት የመፈፀም፣ መንገዶችን የመዝጋት፣ የግለሰቦችንና የመንግሥት ንብረቶችን እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማውደም ተግባራት ሲፈጸሙ እየተስተዋሉ ነው። እነዚህ ተግባሮች ለውጡን የሚያደናቅፉ እንጂ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ለመመለስም ይሁን እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ለውጥ ሊያግዙ አይደሉም። ስለሆነም ህብረተሰቡ ለህግ የበላይነት መከበር የነቃ ተሳትፎውን አጠናክሮ በመቀጠል ይኖርበታል። በተለይም ወጣቶች ከእንዲህ መሰል ለውጥ አደናቃፊ ተግባሮች ራሳቸውን ማራቅ ይኖርባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የህግ የበላይነት በአገራችን ውስጥ እውን መሆን እንዳለበት ደጋግመው አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያት አላቸው። ይኸውም ይህግ የበላይነት በሌለበት አገር ውስጥ ልማትን ብቻ ሳይሆን የዜጎች ውሎና አዳር አደጋ ውስጥ ስለሚገባ ነው። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ለግና ለስርዓት መከበር ዘብ ሆኖ መቆም ይኖርበታል።

የህግ ልዕልና አለመከበር በአገር ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ አሉታዊ ጫናን ይፈጥራል። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር አገራዊ ሃላፊነቱን መከወን የእለት ተእለት ተግባሩ ማድረግ አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ሊሸራረፍና ህገ ወጦች እንዳሻቸው የሚሆኑበት አውድ የለም። ይህ የህግን የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በመከባበበርና በመቻቻል እንዲሁም በኢትዮጵያዊ የአንድነት ስሜት ላይ የተመሰረተውን የለውጥ ሂደት የሚያስተጓጉል ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ አይቀርም።

በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር አለበት። በአሁኑ ሰዓት በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አንዳንድ ወጣቶችን ወደ አላስፈላጊ መንገድ የሚመሩ የግጭት አካላት እየተስተዋሉ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች አመራሮችን ከህግ አግባብ ውጭ እስከ ማደን፣ ከሰልፉ ተቃራኒ በሆኑ መንገድ የግለሰቦችን ንብረት እስከማውደምና የህዝብ መገልገያዎችን ከጥቅም ውጭ እስከማድረግ የመሳሰሉ ተግባሮች እየተስተዋሉ ነው። ይህ ለውጡን ከመደገፍ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። እንዲያውም ለውጡ ይዞት የተነሳውን የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር መንፈስን የሚጻረር ነው። መቀነስም ነው። እናም ተግባሮቹ በአፋጣኝ ሊወገዱ ይገባል።  

እርግጥ መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር መስራቱ አይቀርም። መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት መስጠት ይኖርበታል።

ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ ጽኑ ትግል የተገኘውን ለውጥ በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም። ስለሆነም ህግና ስርዓትን በማስከበር የአብዛኛውን ህዝብ ፍላጎት ማራጋገጥ ይኖርበታል። ጥቂት ግጭትን ለመቀስቀስ የሚፈልጉ ሃይሎችም ከህግ በላይ አለመሆናቸውን ማስተማር አለበት።

በህዝቦች ደም የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚሹ ሃይሎች ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት የእኔነት አስተሳሰብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ህዝቦች በትግላቸው ያመጡት ለውጥ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን የሚያደርግ እንጂ የህግ የበላይነትን የሚጻረር አለመሆኑን ማስገንዘብ የሁሉም አካላት ድርሻ መሆን ይኖርበታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህገ ወጦችንና የደባ ተንኮለኞችን አታስተናግድም። እናም የተገኘው ለውጥ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጠ እንዲሁም ለሚፈፀሙ ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ ሂደቱን ማጋጋል ይኖርበታል።

እርግጥ በየትኛውም አገር ውስጥ ቢሆን፣ ማንኛውም የለውጥ ሂደት ችግሮች የሚደቀኑበት መሆኑ ነባራዊ እውነታ ነው። የሚጠበቅም ነው። ሆኖም ችግሮቹን በመቀነስ ብሎም እስከወዲያኛው በማጥፋት ለውጡ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መረባረብ አለበት። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ እየታየ ያለውንና ለውጡን ሊቀለብስ የሚችለውን የህግ የበላይነትን ያለማክበር ሁኔታ መፍታት ይገባል።

ይህ ተግባር ለመንግስት ብቻ የተተወ አይደለም። ህብረተሰቡ በአጠቃላይ፣ ወጣቶች በተለይ ስለ ህግ የበላይነት በመገንዘብ የሚያከናውኗቸው ማናቸውም ድርጊቶች የህግ የበላይነትን የማይጻረሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። 

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ ለውጡን በተያዘለት መንገድ እንዲሄድ ድጋፍ እናደርጋለን። ከሁሉም በላይ ህጎች ለሁሉም ዜጋ እኩል ሆነው እነደሚሰሩ ማወቅ ይገባል። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ሊሆኑ አይችሉም።

የህግ የበላይነት ለድርድር ሳይቀርብ ሲቀር፣ ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንዳኛለን። የሚያንስም ይሁን የሚበልጥ አይኖርም። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው አገራዊ ጥቅም እኩል ተካፋዩች እንሆናለን። በመሆኑም የህግ የበላይነትን ማክበር ከራስ ጥቅም ጋር የተያያዘ ጭምር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በመሆኑም ከላይ በጠቀስኳቸው እውነታዎች ምክንያት ሁሉም ዜጋ የህግ የበላይነትን ማክበር አማራጭ የሌለው አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል።