“አንድ ሆነን አንድ እንበል”

መጪው ሳምንት ማለትም ከነሐሴ 13 ቀን 2010 ቀን ጀምሮ እስከ አዲሱ ዓመት መባቻና መስከረም ሦስተኛ ሳምንት ድረስ በሀገራችን ዐበይት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው በዓላት ይከበራሉ ። በነዚህ ጊዜያት በሙስሊሞች በድምቀት የሚከበረው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዐል አንዱ ነው ። በዐሉ ሲከበር ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚኖሩ  ቤተሰቦች ዘመድ ወዳጆች ወደ ቤተሰባቸው ሄደው የሚጠያየቁበት በዐላቸውን አያከበሩ ናፍቆታቸውን እየተወጡ የተወሰነ ጊዜ ቆይተው ወደሥራ ቦታቸው የሚመለሱበት ነው ።

እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች የሚኖሩ ጉራጌና ስልጤ ያሉ ብጤረሰቦች በዐሉን በጉጉት እና ናፍቆት የሚጠብቁበት ከቤተሰቦቻቸው የሚመራረቁበት የጋብቻ ሥርዐት የሚፈፅሙበት በዐል ነው ።በዐሉ በየመስጊዱ ሄደው የሶላት (ስግደት) ሥርዐት የሚያከናዉኑበት በመሆኑም በቤትም በአደባባይም የሚከበር ነው ።  እንደ ቡሄ፣ አሸንዳ፣ ሻደይ ወይም ሶለል ያሉት የወጣቶችና የልጃገረዶች በዐላትም ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ናቸው ።በትግራይ ክልል አሸንዳ በመባል በሴቶችና ልጃገረዶች የሚከበረው በዐል በተመሳሳይ መልኩ በላስታ ላልይበላ ሻደይ በመባል በተመሳሳይ ወቅት ይከበራል ።ከሃያ ቀን በኋላም የዘመን መለወጫ ወይም አዲስ ዓመት፣ ደመራና የመስቀል በዐል ቀጥሎም የኦሮሞ ብሔር የኢሬቻ በዐል ተጠቃሽ ናቸው። ለነዚህ በዐላት ሲባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እስከ 25 ከመቶ የአውሮፕላን ትኬት ቅናሽ ለማድረግ ቃል በመግባት መግለጫ ሰጥቷል። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲሁም  የትራንስፖርትና አስጎብኚ ድርጅቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ቅናሽ ለማድረግ መዘጋጀታቸዉ መልካም አጋጣሚ ነው።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ለመገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ መጪው አዲስ ዓመት በዐል “አንድ ሆነን አንድ እንበል” በሚል መርህ ኢትዮጵያውያንን በሚገልፁ ዕሴቶች ከነሃሴ አጋማሽ እስከ መስከረም መጨረሻ ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል። በነዚህ በዐላት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የዚህ ሥነ ሥርዓት ተሳታፊ  ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን ወደ ኤርትራ የሚያመራ ሲሆን የኤርትራ የባህል ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ እየተሠራ መሆኑን ከሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን መግለጫ መረዳት ተችሏል።

ሕዝቡና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ በተለየ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንግዶችን እንዲያስተናግዱ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው ስምምነት ለበዐሉ የተለየ ድምቀት እንደሚሰጠው ጠቁመው የአገልግሎት ጥራትና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ከማሳሰባቸው በተጨማሪ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚታየው አለመረጋጋት መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ኅብረተሰቡ በመሆኑ በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አፅንጾት ሰጥተው ተናግረዋል።

ከላይ እንደተጠቀሰው ከነሐሴ አጋማሽ እሰከ አዲሱ ዓመት መባቻና መስከረም ወር መጨረሻ የሚከበሩት በዐላት በብዛት ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት የሚከበበሩ  የአደባባይ በዐላት በመሆናቸው ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ጋዜጠኞችና የፀጥታ አካላት በዐላቱ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ድምቀት እንዲከበሩ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው። ይህም ሰሞኑን በየቦታው ስንሰማው የነበረው ሁከትና ግጭት ተወግዶ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለን በመተሳሰብ ለማክበር የሚረዳን ነው ። በተለይ የፀጥታ አካላት ከፊታችን ያሉት በዐላት አሸብርቀው ደምቀው እንዲከበሩ ትልቁን ሰላምና ፀጥታ በማስከበር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ ። ስለዚህ የፀጥታ አካላት በየበዐሉ ሲሄዱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ግርግር ቢፈጠር ለመታዘብ ሳይሆን ለሰላምና ፀጥታ ዘብ ለመቆም ከመንግሥት የተላኩ መሆኑን በመረዳት ቀደም ሲል በአንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ሁከቶች እንዳይደገሙ መጣር አለባቸው።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በዐላቱ ብዙ ስለሆኑ ለፀጥታ አካላቱ በአንዱ በዓል የሚታይ ድክመት በቀጣዩ በዐል ለማረምና ተሞክሮ ለመውሰድ ይጠቅማቸዋል። ብሔር ተኮርም ሆነ ሃይማኖት ተኮር ግርግሮች እንዳይፈጠሩ ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶችም ሕዝቡን ማስተማር ከስሜታዊነት ተቆጥቦ ምክንያታዊነትን አንግቦ በዐላቱን እንዲያከብር ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ክልሎች ተፈጥረው በነበሩ ሁከትና ግርግሮች በገንዘብ ልንተካው የማንችል የሰው ሕይወት አልፏል፣ ንብረት ተዘርፏል፣ የእምነት ተቋማት በእሳት ተቃጥለዋል። ‘የሁከት’ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደተባለው ሕይወት በማጥፋት አካል በማጉደል ንብረት በመዝረፍ የሚገኝ ትርፍ ውጤቱ ፈረንጆች “የዜሮ ድምር ጨዋታ” እንደሚሉት ወይም እንድ ሀገራችን ብሂል “ዘጠኝ ገዝቶ ዘጠኝ መሸጥ ውጤቱ ዘጥዘጥ” ነው። ሕይወት በማጥፋት ንብረት በመዝረፍ አተርፋለሁ ብለው የሚያስቡ ካሉ“ አተርፍ ባይ አጉዳይ” ናቸው። ግርግርና ግራመጋባትን አስወግደን ብሔራዊ መግባባትን ፈጥረን የሀገራችንን ገፅታ የመገንባት ኃላፊነት  የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የዜጎችም ድርሻ ነው።