ለውጥና የህግ የበላይነት!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች  እየተፈጸሙ ያሉ የህግ ጥሰቶች  በአገራችን እየተካሄደ ላለው የለውጥ እንቅፋት እንዳይሆን ስጋት አለኝ። መንግስት እንዲህ ያሉ አካሄዶችን ሊታገሳቸው አይገባም።  አየተፈጸሙ ያሉ ጸያፍ ድርጊቶችን   መንግስት ሳይመለከታቸው ወይም ለማስቆም አቅም አጥቶ ሳይሆን  የህዝቦችን  የለውጥ ፍላጎት ላለመጫን ብሎ ዝምታን የመረጠ ይመስለኛል። ይሁንና አሁን ላይ ህብረተሰቡ  በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ  ስጋት እያደረበት  በመምጣቱ  ጥቃቶቹን  በግልጽ  በማውገዝ  መንግስት እርምጃ እንዲወስድ  እያሳሰበ ይገኛል። 

እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ  አካሄዶች  በአገራችን እየተካሄደ  ያለውን  ለውጥ  ወደኋላ የመመለስ  አቅም ባይኖራቸውም በግለሰቦች ላይ የሚፈጥረው ጫና በቀላሉ  የሚታይ አይደለም።  በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጠረው ሁከት በርካቶችን  መስዋዕት  ያደረገ ነው።  

ይህን ለውጥ ልንከባከበው ይገባናል።  እንደእኔ ይህ ለውጥ አገራችንን  ታድጓታል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ይህ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ  ምን አልባት  ኢትዮጵያ  እንደ አገር   ልትቀጥል  የማትችልበት  ደረጃ  ላይ ደርሳ ነበር።

 በኦሮሚያና አማራ ተከስቶ የነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ አገራችን ወደ ለውጥ ጎዳና እንድታመራ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። ዛሬ ላይ በዚያ ሃይል ስም ወንጀል ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ ቡድን እየተመለከትን ነው።  ዛሬ ላይ አገራችን የጀመረችውን የለውጥ ሂደት አጠናክሮ ከመቀጠል እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ከማድረግ ውጪ  ሌላው አማራጭ ከባድና ውስብስብ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

አንዳንድ ሃይሎች ይህ ለውጥ ጥቅማችንን ያሳጣናል በሚል አስተሳሰብ በሚመስል መልኩ ለውጡን በቀናነት አልተመለከተቱም። በዚህም ምክንያት ይመስላል እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች ለውጡን ለመቀልበስ የተለያዩ እንቅፋቶችን ቀድመው እያስቀመጡልን  ለውጡን ፈታኝና ከባድ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ለህግ የበላይነት መረጋገጥ  መንግስት  የማይተካ ሚና ይኑረው እንጂ  ህብረተሰቡ  ለህግ የበላይነትን ማረጋገጥ  ያለው  አስተዋጽዖም  ከፍተኛ  ነው።  የሕግ የበላይነት ለሰላም መረጋገጥ  የመጀመሪያውና ትልቁ  መስፈርት ነው።  አገር እንደአገር ልትቀጥል የምትችለው በተመሳሳይ መንግስትም እንደመንግስት ሊከበርና አገር ሊያስተዳድር  የሚችለው የህግ የበላይነት ማረጋገገገጥ ሲችል ብቻ ነው።  በየትኛውም አገር መንግስት መንግስት ሊባል የሚችለው በስልጣን ላይም የሚቆየው፣ በህዝቦች ተቀባይነት  የሚኖረውም ወዘተ  የህግ የበላይነትን ማረጋገገጥ ሲችል ብቻ ነው።  

ነውጠኛ  ሃይል  ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ ነውጥ እያስነሳ መዝረፍን አማራጭ እያደረገ እንደሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ተመልክተናል። ህይወት እያጠፋና ንብረት እየዘረፈ በማናለብኝነት  የሚንቀሳቀስ ሃይልን  ሁላችንም ተረባርበን  ማስቆም ካልቻልን  አገራችንን ወደ ማጡ እንደሚወስዳት ምንም ጥርጥር  የለም።

እናቴ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ  እንደሚባለው ዛሬ ላይ ሁላችንም  ለህግ የበላይነት መረባረብ ይጠበቅብናል።  የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው  ህዝብና መንግሥትን  ጨምሮ  ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለህግ የበላይነት  መረጋገጥ ጥረት ሲያደርጉ እንዲሁም  ሁሉም  የህብረተሰብ  ክፍል  በህግ ፊት  እኩል  መሆናቸውን  ማረጋገጥ  ሲቻል  ብቻ  ነው።

   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  መንግስት  ወይም  ገዥው  ፓርቲ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አቅም ያነሰው እስኪመስል ድረስ  ማንም እየተነሳ የሚጨፍርበት ሁኔታ በአገራችን እንዲፈጠር በር የተከፈተ ይመስላል። ቄሮ፣ ፋኖ፣ ወዘተ  በሚል ስያሜ የተቋቋሙ ወጣቶች በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት እንደሆኑ ሁሉ አሁን ላይ ደግሞ በእነርሱ ስም የተቋቋሙ ሃይሎች ቀን በቀን ዘረፋ ላይ እየተሰማሩ ህብረተሰቡን በማስመረር ላይ ናቸው። 

በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች ያለሃጢያታቸው ይገደላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ከሁሉም በላይ  የሚያስገርመው  ደግሞ ይህን የሚፈጽሙ አካላት ድርጊቱን እንደመብታቸው መመልከታቸው ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል።

በተመሳሳይ  ጥቃት የደረሰባቸው አካሎችም  ወደ ህግ ቢሄዱም መፍትሄ እንደማያገኙ፤ የህግ አካሉም ሊከላከልላቸው እንደማይችል  አምነው በመቀበላቸው  የሚደርስባቸውን  በደል ለፈጣሪያቸው ብቻ  ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ። ይህ ነው የሚያሳዝነው። ይህ ነው  የሚያሳፍረውም። በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል  የተፈጸመው ድርጊት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።  

ያለፈው አልፏል  መንግስት  አሁን ላይ  አገራችን ያለችበትን ነበራዊ ሁኔታ  ታሳቢ  በማድረግ  ከዚህ ብኋላ ነገሮችን በለሆሳስ ማለፍ የለበትም። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሰጡት መግለጫ በተግባር ተተርጎሞ ለማየት እንፈልጋለን። አናሳ ናቸው  ተበለው  የሚታሰቡ  አካሎችን   መግደልና አካል ማጉደል፣ የመንግስትና የግለሰቦችን ንብረት ማውደምና መዝረፍ፣  የጸጥታ ሃይሎችን ማጥቃት  የኢትዮጵያዊያን  ባህል አይደለም፤ በሃይማኖትም  ረገድ  አይፈቅድም።

እኛ ኢትዮጵያዊያን  ነን፤ የራሳችን እሴቶች አሉን። እነዚህን መልካም እሴቶቻችን  እንዳይሸረሸሩ  ህብረተሰብ  መከላከል አለበት። የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያዩ ስርዓቶች  ውስጥ  አብረው ኖረዋል፤ ይህ ቀንም ያልፍና   ነገም አብረው  የኖራሉ። በመሆኑም በብሄር ወይም በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አስተሳሰቡ አማካኝነት በዜጎች ላይ ጥቃት  ማድረስ  ኋላቀርነትና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው።    

የህግ የበላይነት ካልተረጋገገጠ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይቅሩና  ሰብዓዊ መብቶች  በጠራራ ጸሃይ ይጣሳሉ፡፡ ይህን ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተግባር ተመልክተናል፤ ሰዎች በዘራቸው ብቻ ከመኖሪያ ቤታቸው እየተጎተቱ  ተገድለዋል፣ መኖሪያቸውና ቤተ ዕምነቶቻቸው ተቃጥለዋል፣  በርካታ ደሃ ዜጎች ያለሃጢያታቸው ተደብድበዋል፣ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን ተዘርፏል።  

አገሩ የእኛ ብቻ  ነው ብለው ያሰቡ ወይም እንደዚያ  የተነገራቸው አካሎች  በዘር ወይም በቋንቋ ወይም በአስተሳሰብ  ተለይተውናል እኛን አይመስሉም ያሏቸውን  አናሳ ወገኖች  እንደፈለጉ  ሲያጠቁ  ሲዘርፉና  ሲያዘርፉ ተመልክተናል።  ለዜጎች ደህንነት  የመጀመሪያው ተጠያቂ መንግስት ይሁን እንጂ ህብረተሰቡም ሃላፊነት ሊሰማው ይገባል። በርካታ ቅን ዜጎች ወገኖቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል ጥረት አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በርካታ ሶማሌዎች በወገኖቻቸውን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ከማውገዝ ጀምረው ለመከላከል ጥረት አድርገዋል።

ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የመኖር ህገመንግስታዊ  መብት አላቸው።  ይሁንና ይህ  ህገመንግስታዊ መብት በጠራራ ጸሃይ ሲጣስ አባት አልነበረውም። ህገመንግስት መጣስ  ሲጀምር  ቀጣዩ ምን እንደሚሆን መገመት የሚከብድ አይሆንም። ዴሞክራሲ ማለት የህግ የበላይነት ማለት ነው። ከእያንዳንዱ መብቶች ጎን ለጎን ግዴታዎችንም  መኖራቸውን  መታሰብ ይኖርበታል። መቼም ቢሆን በሁከትና በአመጽ የተሳተፈ ማንኛውም አካል መጠየቅ መቻል ይኖርበታል። አገራችን በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ናት፤ በዚህ የለውጥ ሆዳና ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን እየተመለከትን ነው።

አንዳንዶች በዚህ የለውጥ ጊዜ የሚፈጽሟቸው ህገወጥ ድርጊቶች ተጠያቂነት እንደሌለ በማሰብ በጠራራ ጸሃይ ወንጀል በመፈጸም ላይ ናቸው።  ማንም ለሰራው ጥፋት ተጠያቂነትን ማስፈን ካልተቻለ የህግ የበላይነት ከጥያቄ ላይ የሚወድቅ ይሆናል። በመሆኑም የህግ የበላይነት መረጋገጥን ለመንግስት ብቻ ሳንተው ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል።