ትምህርት ለህይወት

 

የሐገራችን የትምህርት ፖሊሲ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር፤ ትልቅ የማሻሻያ ሥራ ያስፈልገዋል በሚል የገለፀው አንድ የማህበራዊ ዘርፍ አጀንዳ ትምህርት ነው፡፡ በመጪው የትምህርት ዘመን የሚተገበር የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቧል፡፡

የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የትምህርት ፖሊሲውን ችግሮች ሲያበራሩ፤ ‹‹በትምህርት ቤት ኢንጅነሪነግ አጥንተው ወጥተው፤ መንገድ እና ድልድይ መስራት የማይችሉ፤ የሚሰሩትም ግንባታ በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ፤ የምንከተለው የትምህርት ፖሊሲ ችግር እንዳለው በግልጽ ያመለክታል›› ብለዋል፡፡ ለልጆች የሚሰጠው ትምህርት ለህይወት የሚያገለግል ካልሆነ፤ ከንቱ ድካም እና የሐብት ብክነት ሆኖ ይቀራል፡፡

ከዚህ ጋር የተያያዘ የአንድ ጃፓናዊ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ የወጣት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን፤ በማህበረሰብ ጥናት ዘርፍ (ሶሻል ሳይንስ) የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ ነው፡፡ ጃፓን በጦርነቱ የሚሳተፉ ወጣቶችን ስትመለምል፤  ለጃፓን የወደፊት ጉዞ በጣም ያስፈልጋሉ ያለቻቸውን የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎችን በመተው፤ በማህበረሰብ ጥናት ዘርፍ (ሶሻል ሳይንስ) ከገቡት ተማሪዎች ምልመላ አደረገች፡፡

ባለታሪካችን፤ በተመረጠ የጠላት ዒላማ ላይ ሃራኬሪ ሰርተው፤ የሐገራቸው ጃፓን ጠላቶችን ለማደባየት ሰለጠኑ፡፡ ስልጠናው አውሮፕላን አስነስቶ በመብረር፤ የጠላትን ኃይል እና ትጥቅ አጥፍቶ ለመጥፋት ግዳጅ ዝግጁ የሚያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ስልጠና ወስደው፤ ግዳጃቸውን ለመፈጸም ሲጠባበቁ ሳለ፤ የጃፓኑ ንጉሥ ሂሮሂቶ አንድ ያልተጠበቀ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ውሳኔው እንደ ኮሶ በሚመረው እና ቢንገሸግሸውም፤ ሽንፈትን ከመቀበል ይልቅ፤ እንደዋዛ ነገር የሞት ጽዋን ጨልጦ፤ ምድርን መሰናበት ከሚቀለው የጃፓን ህዝብ ፊት ቆሞ ‹‹በጦርነቱ ተሸንፈናል›› ብሎ ለመናገር ወሰነ፡፡

ጃፓን በፈጸመችው ጥቃት የተነሳ፤ በበቀል ስሜት የተቃጠለችው አሜሪካ፤ ምድር እና ሰማይን የሚያርድ፤ በአንድ ደቂቃ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን እንደ ቅጠል የሚያረግፍ የአቶሚክ ቦምብ የጫነ አውሮፕላን ወደ ሂሮሽማ ላከች፡፡ ጃፓን በሂሮሽማ የደረሰባት ድንጋጤ ሳይለቃት፤ አስፈሪው የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ናጋሳኪን ለማውደም በጃፓን ሰማይ ሥር ማነዣበብ ጀመረ፡፡ ቦንቡን ጣለ፡፡

በዚህ የአሜሪካ ጥቃት ህልቆ መሳፍርት የሌለው የሂሮሽማ እና የናጋሳኪ ከተማ ህዝብ ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳረገ፡፡ ከዚህ አደጋ ፊት የቆመው እና ከጀርመን እና ከጣሊያን ጋር ተሰልፎ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲዋጋ የቆየው የጃፓኑ ንጉሥ ሂሮሂቶ፤ አሁን አንድ ነገር ማድረግ አለበት፡፡

በጃፓን ህዝብ ዘንድ እንደ አምላክ የሚታየው ንጉሡ ሂሮሂቶ፤ ፍፁም የሚያንገሸግሽ ነገር ቢሆንበትም፤ እንደ አምላክ የመታየት እና የመከበር ዘልማድ፤ በግብዝነት እንዲወስን እና ከእውነት ጋር እንዲጣላ ሳያደርገው፤ ሐገሩን እና ህዝቡን ከጥፋት ለማዳን ሲል ‹‹እጅ መስጠት አለብን›› አለ፡፡ ስለዚህ፤ ኃያሏን አሜሪካ ተለማምጦ ሰላም ለማውረድ ወሰነ፡፡

ሆኖም፤ በንጉሡ ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው ሦስት የጦር መኮንኖች ‹‹እርቅ ማድረግ አይሞከርም›› ብለው አስቸገሩ፡፡ እንዲያውም፤ ‹‹አሜሪካን ድል ለማድረግ የሚያስችለን አንድ ይዘን ያቆየነው ምስጢራዊ የጦር ዕቅድ አለን›› እያሉ ንጉሡ ከአሜሪካ ጋር እርቅ እንዳያደርግ ተማፀኑ – ወተወቱ፡፡ እንደ ህፃን እያለቀሱ እና ከእግሩ ሥር እየተንደባለሉ፤ ንጉሣቸውን አጥብቀው ለመኑት፡፡

ብልሑ ንጉሥ ሂሮሂቶ አቅሙን አውቆታል፡፡ ስለዚህ የወታደሮቹ ልመና አበሳጨው፡፡ ተቆጣ፡፡ ተቆጥቶም፤ ‹‹እኔ የምፈልገው ከጦር አበሮቹ (እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ) የቀረበውን የእርቅ ሐሳብ መቀበል ብቻ ነው›› ብሎ እቅጩን ነገራቸው፡፡ እንዳለውም አደረገ፡፡

ታዲያ ንጉሡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› የሚል ድብዳቤ ለኃያላኑ መንግስታት ለመስደድ መወሰኑን የሰማው የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር አናሚ፤ መሬት ላይ ወድቆ እየተንከባለለ ንጉሡ እርቅ እንዳያደርግ ቢለምነውም፤ የወታደሮቹ ባዶ ጀግንነት ከጥፋት በቀር የሚጠቅም ነገር እንደማያመጣ የተገነዘበው እና በአስተዋይ መንፈስ የተጤነ ታላቅ ውሳኔ ያደረገው ሂሮሂቶ፤ ‹‹የእርቁን ሐሳብ ተቀብያለሁ›› የሚል ደብዳቤ ለጦር አበሮቹ ሐገራት ሰደደ፡፡

 ይህ ውሳኔ፤ መሪ የመሆን ሸክምን እና መሪ መሆን የሚጠይቀው የመንፈስ ፅናት ምን እንደሚመስል፤ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስተምር ታሪካዊ ውሳኔ በመሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡

በአንፃሩ፤ ንጉሱ ቢሞት ‹‹እርሱ ከሞተ ወዲያ በህይወት መቆየት ምን ይረባኛል›› ብለው ሃራኬሪ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩት የጦር ጀነራሎች ሁሉ፤ የሰጡትን ምክር ገፋ አድርጎ፤ ንጉሥ ሂሮሂቶ ‹‹የእርቁን ሐሳብ ተቀብያለሁ›› አለ፡፡ የጦር ጀነራሎቹ በዚህ የንጉሱ ውሳኔ በእጅጉ ቢያዝኑም፤ በውሳኔው ተቆጥተው ክፉ ለማድረግ አልተነሳሱም፡፡

 እርግጥ፤ የንጉሡ ውሳኔ አበሳጭቷቸው በቁጣ እና በቁጭት ስሜት ተገፋፍተው ክፉ ነገር ከማድረግ አይመለሱም የሚል ሥጋት ስለነበር፤ የእርቅ ሐሳቡ በተገለፀበት ቀን፤ ንጉሥ ሂሮሂቶ ሌሊቱን አሳቻ ቦታ ተደብቆ ነበር ያደረው፡፡

እንደ ተገለፀው፤ የጦር ጀነራሎቹ ንጉሠ ነገስታቸውን ለመድፈር ባይሞክሩም፤ ለቁጣቸው ማስታገሻ የሚሆን ነገር የፈለጉ ይመስል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሱዙኪን የመኖሪያ ቤት አቃጠሉት፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱዙኪ አስቀድሞ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ጠርጥሮ፤ እርሱም እንደ ንጉሡ ተደብቆ ስለነበር ከጥቃቱ አመለጠ፡፡

ጀግናው ንጉሥ ሂሮሂቶ በማግስቱ ማልዶ ተነሳ፡፡ እንደ አምላክ በሚያዩት ጃፓናዊያን ፊት ቆሞ፤ እንደ ሞት የሚጠሏትን ቃል ከአንደበቱ እንድትወጣ ፈቀደ፡፡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› አለ፡፡ ይህን ቃል በጃፓን ህዝብ ፊት ቆሞ መናገር፤ የቀለጠ ብረትን ሳይሳሱ ከመጠጣት ሊቆጠር የሚችል ድፍረት መሆኑን የሚረዳው፤ የጃፓናውያንን ባህል የሚያውቅ ሰው ብቻ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በዚያ ጊዜ ከታላቅ ጅግንነት ሊቆጠር የሚችለው፤ የገዛ ሽጉጥን ጠጥቶ መገላገል ወይም ሻምላን ከእንብርት ላይ ቀብቅቦ ራስን ማጥፋት ሳይሆን፤ በጃፓናዊያን ፊት ቆሞ ‹‹የእርቁን ሐሳብ ተቀብያለሁ›› ብሎ መናገሩ ነበር፡፡

ሂሮሂቶ፤ ሳንጃ ከሆዱ ሰክቶ በክብር ቢሞት፤ የክብር አክሊል ደፍቶ ምድርን መሰናበት ይችል ነበር፡፡ በሞቱ፤ ውርደትን ከእርሱ ያርቃት ነበር፡፡ ነገር ግን፤ በአንድ ጊዜ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጃፓናውያንን ህይወት የሚቀጥፈውን የአሜሪካ የአቶሚክ ቦምብ ከሰማይ መዝነቡን ግን ሊገታው አይችልም ነበር፡፡ ከጃፓናውያን ባህል እና አመለካከት አንፃር ለሂሮሂቶ፤ የሞት ሞት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለው፤ ህዝብን ከመከራ ለመጠበቅ፤ ‹‹ተሸንፈናል›› የሚል ቃል ከአንደበት ማውጣት ነበር፡፡ እናም፤ ንጉሡ አደባባይ ወጥቶ፤ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ባለ ጊዜ፤ እርሱ አሥር ጊዜ ቢሞትም፤ ሐገሩን እና ህዝቡን ከሺህ ሞት አትርፏል፡፡

ሂሮሂቶ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ብሎ ሲያውጅ፤ የጦር ሚኒስትሩ ሃራኬሪ አደረገ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉ የጃፓን የጀነራሎችም በተመሳሳይ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ታናካ የሚሉት አንድ ጀነራል፤ አዋጁ ይፋ ከተደረገበት ደቂቃ ጀምሮ፤ ማንም ሰው በንጉሡ ላይ እጁን እንዳያነሳ ቀን እና ሌሊት ንጉሡን ሲጠብቅ ቆየ፡፡ ከዚያም፤ ንጉሡ ደህና መሆኑን በዓይኑ አይቶ ለማረጋጥ በማሰብ ወደ እልፍኝ ሄደ፡፡ እልፍኝ ገብቶ የንጉሡን ደህንነት አረጋገጠ፡፡ ከዚያም እጅ ነስቶ በመውጣት፤ ሃራኬሪ አደርጎ ከሞት ጋር ተቃቅፎ ወደቀ፡፡ ሞተ፡፡ ጀነራል ታናካ ሞተ፡፡

ጀነራል ታናካ በተስፋ መቁረጥ እና አጥንት በሚሰብር ውርደት ጫና ውስጥ ቢወድቅም፤ ማስተዋልን አጥቶ፤ ወታደራዊ መሐላውን አፍርሶ፤ ሐገሩን የሚጎዳ ነገር ከመፈፀም የሚያቅብ የመንፈስ ጽናት እንደ ነበረው በተግባር አረጋግጧል፡፡ ሆኖም፤ ከዚያ አሻግሮ የሚወስድ የመንፈስ ኃይል አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ‹‹ውርደትን›› በሞት ገንዞ እና ከፍኖ ወደ መቃብር መውረድን መረጠ፡፡

የንጉሡ ታሪክ፤ በዋና ባለታሪካችንም ሆነ በርዕሰ ጉዳያችን (ትምህርት) ላይ ግርዶሽ እንደሰራ ተረድቻለሁ፡፡ ሆኖም፤ ቸ የባለታሪካችን ታሪክ ከንጉሡ ታሪክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ የንጉሱ ታሪክ መወሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ባለታሪካችን ከዚያ ጦርነት አጥፍቶ ከመጥፋት ግዳጁ የዳነው በንጉሡ ውሳኔ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መነኮሰ፡፡

እናም ‹‹የዜን መነኩሴ ለመሆን የበቃሁበት አጋጣሚ›› በሚል ርዕስ በጻፈው አጭር ታሪኩን ጻፈ፡፡ ይህን ታሪካቸውን ያጫወቱን መነኩሴ፤ የመንግስትን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጥሪን ተቀብለው፤ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ ቆዩ፡፡ ከዚያም ለአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ሲዘጋጁ ቆይተው፤ ንጉሡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ብሎ ሲያውጅ፤ የእምነት መሠረታቸውን የሚያነዋውጽ ፈተና ወደቀባቸው፡፡

ህይወትን በፈቃዱ ተሰናብቶ፤ ከሞት ጋር ሲተሻሽ ከከረመ በኋላ፤ በግድ ወደ ህይወት የተመለሰው ያ ወጣት፤ መልሶ ከህይወት ጋር መታረቁ ከበደው፡፡ ሳያመነታ ወደ ሞት ለመሄድ ተዘጋጅቶ የነበረው ልቡ፤ ድንገት ቀኝ ኋላ ዙር ተብሎ ወደ ህይወት ሲመለስ፤ ነፍሱ በሥነ ልቦና ቀውስ ታመሰች፡፡ በንጉሡ ውሳኔ ቅስማቸው የተሰበረ በርካታ ጃፓናውያን ከፎቅ ላይ እየተወረወሩ ሲሞቱ በማየት ሐዘን ልቡን አንጎዳጉዶታል፡፡

በዚህ ዓይነት ድባብ እና የስሜት ሁከት እንደጎበጠ፤ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ከገባበት የሥልጠና ካምፕ ወጥቶ፤ ግብዙን ሆኖ በቶኪዮ ጎዳና መንከራተት ጀመረ፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ የሚሄድበት አድራሻ እና ሐዘን ተጋሪ የቅርብ ዘመድ ጭምር ያልነበረው ያ ወጣት፤ አስቸጋሪ ፈታና ላይ ወደቀ፡፡ ከሞት ወዲያ ማዶ ያለው ዓለም ሊቀበለው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

አካሉ የሚዘዋወርበት እና በፈቃዱ ጥሎት ሊሄድ የነበረው ምድራዊው ህይወትም በጣም ፊት ነስቶታል፡፡ አባት እና እናቱን ጨምሮ ብዙ ዘመዶቹ ጥለውት የሄዱት ይህ ምድራዊ ዓለም፤ ዘመድ አልቦ ወና ሆኖበታል፡፡ ህሊና እና መንፈሱ እንዲህ ዓይነት ጨካኝ የህይወት ሐቅ ውስጥ የተቀረቀረበት ያ ወጣት፤ በቶኪዮ ከተማ ለጊዜው እንኳን የሚጠጋበት ታዛ አልነበረውም፡፡ ለሞት የተሰናዳ መንፈሱ፤ ለህይወት ዝግጁ መሆን ተስኖት ተቸግሯል፡፡

በዚህ ጊዜ፤ ያለፈ የህይወት መንገዱን መለስ ብሎ መመርመር ጀመረ፡፡ ምድረ – ህሊናውን የሚያናውጥ፤ ምድረ – መንፈሱን ቁና የሚያደርግ፤ ነፍሱን እንደ ቅማል የሚያፍተለትል፤ ህሊናን እንደ ደረቅ ሎሚ የሚጨምቅ፤ የእውነት ቅጽበት መጣ፡፡ ልብን ማህለቅት የለሽ በሆነ የጥያቄ ወጀብ የሚመታ፤ እንደ ሱናሚ ባለ አስፈሪ ማዕበል የሚንጥ፤ በጥያቄ እሣተ ጎመራ የሚገለባብጥ፤ የእውነት ቅጽበት ወረደ፡፡

ለ12 ዓመታት የተማረው የአስኳላ ትምህርት፤ በመንፈሱ እና ሐሳቡ በዛለበት በዚህች ሰዓት ምርኩዝ በመሆን፤ ለአንድ ቀን ዕድሜም ቢሆን ወደፊት ለመጓዝ የሚያስችል የህሊና ስንቅ እንዳልሰጠው ተረዳ፡፡ ለመከራ ጊዜ መደገፊያ የሚሆን ጥበብ እንዳላስታጠቀው አወቀ፡፡ ትምህርቱ ከህይወትም ሆነ ከሞት ጋር ሊያስታርቀው አልቻለም፡፡ ለዓመታት ሲያደክመው ቆይቶ፤ ዛሬ አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎት ኮበለለ፡፡

ከመሞቱ በፊት የሞተው ወጣት፤ መልሶ ከህይወት ለመታረቅ የሚያስችል ጥበብ ሊሰጠው ያልቻለውን የአስኳላ ትምህርት ረገመ፡፡ በእንዲህ ያለ ስሜት እየተናጠ ማደሪያ ፍለጋ ተነሳ፡፡ ቀኑን ሙሉ በቶኪዮ ጎዳናዎች ሲንከራተት የዋለው ወጣት፤ አመሻሹ ላይ ሌሊቱን የሚያሳልፍበት ጥግ ለማግኘት ሲያስብ፤ በከተማው ዳርቻ ከሚገኝ አንድ ገዳም በቀር ሌላ መጠጊያ አልታየውም፡፡ ስለዚህ ወደዚያ ለመሄድ ወሰነ፡፡

ይህ ሞት እና ህይወት ያደሙበት ወጣት ወደ ገዳሙ ቅጽር ገብቶ፤ የገዳሙን አስተዳዳሪ ወይም መምህር አገኛቸው፡፡ መጀመሪያ እንዳሰበው፤ ማደሪያ እና ቁራሽ እንጀራ መጠየቁን ትቶ፤ ሌላ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹አባቴ ለመማር ፈልጌ መጥቻለሁና እባክዎን ተቀብለው ያስተምሩኝ?›› አላቸው፡፡

በዚህ በእኛ ሐገር፤ አመንኩሱኝ ብሎ ወደ ገዳም የሄደ ሰው፤ አመክሮ ሳይሰጠው ዕለቱን እንደ ማይቀበሉት፤ ትምህርት ፍለጋ ወደ ዜን መምህር የሚሄድ ሰውም፤ በቀላሉ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ የዜን መምህራን ‹‹ዓለምን ንቄ፤ የእውነት መንገድ ናፍቄ መጣሁ›› ያላቸውን ሰው ሁሉ አይቀበሉም፡፡ እንዲያውም፤ ተማሪውን በተግባር እና በመንፈስ በብዙ ይመዝኑታል፡፡ መነኩሴው እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ፤

‹‹ምንልታደርግ መጣህ?›› አሉኝ የገዳሙ አለቃ፡፡

‹‹የገዳሙ አለቃ የሆኑት መምህር በትውልድ ቅብብሎሽ በየጊዜው እየተሳለ፤ ከእርሳቸው በደረሰ ጥበብ፤ የመንፈስ ይዞታዬን ለመረዳት ሲጣጣሩ፤ እኔ በህሊናዬ የማስበው ሌላ ነበር፡፡ ‹‹አንተ በከንቱ ትለፋለህ፡፡ እኔ እንደሁ የመጣሁ ቸግሮኝ እንጂ የአንተን አሮጌ ጠበብ ለማማር ፈልጌ አይደለም፡፡ አስራ ሁለት ዓመት ያባከንኩበት ትምህርት ይኸው ለጅብ ሰጥቶኝ፤ አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎኝ ሲሄድ አይቻለሁ›› እያልኩ አስብ ነበር በልቤ›› ይላሉ፡፡

                           ***

ከብዙ ምርመራ በኋላ፤ በእኔ ችክ ማለትና በቅዱስ የርህራሄ ስሜት የተሸነፉት መምህሬ፤ በጊዜአዊነት ተቀበሉኝ፡፡ የምበላውን ከሰጡኝ በኋላ፤ ነባር ልማድ በመሆኑ፤ ሰፊውን የገዳሙን ግቢ እንዳፀዳ አዘዙኝ፡፡ በምድረ ግቢው ከበቀሉት ትላልቅ ዛፎች ከረገፉ ቅጠሎች በቀር ብዙ ቆሻሻ የማይታይበትን ቅጽረ ግቢ መጥረግ ጀመርኩ፡፡ ከኔ ራቅ ባለ ሥፍራ በዝምታ ተቀምጠው የነበሩት መምህር፤ ጽማዌ የሚንፀባረቅበት ገጽታ እንደተላበሱ የምሰራውን ሥራ ይከታተሉ ነበር፡፡ ግቢውን ጠርጌ እንደ ጨረስኩ፤

‹‹አባቴ፤ ቆሻሻወን የት ላድርገው?›› ስል ጠየቅኩ፡፡

እርሳቸውም፤ ‹‹በዚህ ምድር ቆሻሻ የሚባል ነገር የለም›› በማለት ተግሳጽ በመሰለ አኳኋን ምላሽ ሰጡኝ፡፡

ደነገፅኩ፡፡ ትምህርት አንድ አልኩ፡፡        

የገዳሙ ማህበረሰብ ማለዳ ተነስተው ለተመስጦ ከመቀመጣቸው በፊት፤ ለብ ባለ ውሃ ገላቸውን ይታጠባሉ፡፡ ስለዚህ፤ ‹‹ቅጠሉ የገላ መታጠቢያ ውሃ ለማሞቅ ያገለግለናል፡፡ ስለዚህ በዚያ ጆንያ ጠቅጥቀህ ወደ ጓሮ ወስደህ አስቀምጠው›› አሉኝ፡፡

ቅጠሉን በጆንያ መጠቅጠቅ ጀመርኩ፡፡ አያያዜ ያለስደሰታቸው እኒያ የ80 ዓመት አዛውንት፤ ከእኔ በቀለጠፈ አኳኋን ቅጠሉን በጆንያ ሲጠቀጥቁ አይቼ፤ የእኔ የአካል ብቃት ከዚያ አዛውንት በእጅጉ እንደሚያንስ ተመልክቼ አዘንኩ፡፡ የ12 ዓመታት ትምህርቴ፤ በአካል፣ በአዕምሮም ሆነ በመንፈስ ረገድ የሰጠኝ አንዳች ብቃት አለመኖሩን ተገነዘብኩ›› የሚሉት መነኩሴው፤ ትረካቸውን ይቀጥላሉ፡፡

መንኩሴው ትምህርት አንድ … ሁለት … እያሉ ብዙ ያስተምሩናል፡፡ እኔ ግን፤ የመንኩሴውን ታሪክ ተከትዬ ለማንሳት የምፈልገው ጥያቄ፤ ‹‹በሐገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ህሊናችንን ለሚጎተጉቱ እና መሠረታዊ ለሆኑ የህይወት ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የሚያግዘን ነውን?›› የሚል ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ እንዳሉት መልሱ፤ ‹‹በፍፁም፤ አይደለም›› የሚል ነው፡፡

አንዳንዶች የምዕራቡን የትምህርት አሰጣጥ ‹‹ለቢሮ እና ለፋብሪካ ሥራዎች ብቻ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚጥር እንጂ ሰውን በተሟላ ሁኔታ በመገንባት ለህይወት ብቁ የሚያደርግ ትምህርት አይደለም›› ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ‹‹እውነተኛ መምህር እና እውነተኛ ተማሪ ከዓለም ጠፍተዋል፡፡ ስለእውነት ሞትን ለመቀበል የሚደፍረው፤ የመጨረሻው እና እውነተኛው መምህር ከዘመናት በፊት ሔምሎክ ጠጥቶ ሞቷል፡፡ እውነተኛው መምህር ከክርስቶስ ልደት በፊት በ399 ዓመተ ዓለም ሞቶ ተቀብሯል፡፡

የመጨረሻው መምህር ሶቅራጥስ (470-399 ቅ.ል.ክ) በአቴና ሲሞት፤ በእግሩ የተተኩት የዘመናችን መምህራን፤ እውነትን ለንግድ ጥቅም ሊሸጡ የሚችሉ፤ እውነት እና ዕውቀት የብሔራዊ (ቡድናዊ) ጥቅም ማዳወሪያ ሲሆኑ ማየት የማይገዳቸው ሆነዋል›› እያሉ ይብከነከናሉ፡፡

እነሱ ‹‹ትምህርታችን የሰውን ስሜት እና መንፈስ ጭምር ሳይሆን እጁን ብቻ የሚያሰለጥን ትምህርት ነው›› ማለታቸው ነው፡፡ የእኛ ችግር ግን ከእነሱ የባሰ ሆኖ እጅንም የሚያሰለጥን ትምህርት መስጠት አልቻልንም፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ እንዳሉት በሥራ ረገድ ብቁ የሚሆን ተማሪ ማፍራት አልቻልንም ነው፡፡ ትምህርታችን በብዙ ረገድ ተመዝኖ ብዙ ጉድለት ተገኝቶበታል፡፡

አንዳንድ ምዕራባውያን የትምህርት ባለሙያዎች፤ ‹‹ዘላለማዊ ከሆነው እና ከማይሞተው የሰው ልጆች መፍለቂያ ይግቡ›› የሚል ኃይለ ቃል ከመግቢያው በር የሚያስነብበው፤ እውነተኛው ት/ቤት (አካዳሚ)፤ ያ የመጨረሻው ት/ቤት፤ ዛሬ የሸፋጮች፣ የሸቃጮች እና የአጭበርባሪዎች ደብር ሆኗል›› ይላሉ፡፡ እኛም የትምህርት ፖሊሲአችንን በማሻሻል፤ የትምህርት ተቋሞቻችን ‹‹እውነተኛ ትምህርት፣ መምህር እና ተማሪ›› የሚገኙባቸው ማድረግ ይገባናል፡፡ አዲሱ ዘመን፤ ለህይወት የሚረባ ትምህርትን ለመቅሰም የምንችልበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ መልካም ዘመን ለውድ አንባቢያን፡፡