የዲፕሎማሲው ትሩፋቶች ከትናንቱ ዛሬ

አንዲት ሀገር ከሌሎች ሀገሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ግንኙነት በመፍጠር አጋርነቷን አጠናክራ ትቀጥል ዘንድ ሁነኛ የዲፕሎማሲ መርህ ያስፈልጋታል፡፡ ከሀገሮች ጋር ያለን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተሳካ እንዲሆን ደግሞ ጊዜው የሚፈልገውን የተላበሰ መሪ ያስፈልጋል፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን ለማስመዝገብና  ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ጤናማ የሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፍጠር ወደ ዕድገት ጎዳና እንድንሸጋገር የሚረዳ ለገፅታ ግንባታችንም ሁነኛ መሣሪያ ነው፡፡

በቅርቡ ወደ መንበረ ሥልጣናቸው የመጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዲፕሎማሲው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመከወን በተለያዩ ሀገራት መሪዎች ዘንድ በአጭር ወራት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን የተገበሩ እንዲባሉ አስችሏቸዋል፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ሥራቸውን የጀመሩት ደግሞ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት አስደማሚ ንግግር ላይ ያነሱዋቸው ጉዳዮች ናቸው። የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም “ተፎካካሪ” በሚል መጠሪያ በመሰየም በተለያዩ ሀገራት በጥገኝነት ለሚኖሩ ፓርቲዎች ሰላማዊ ጥሪ በማድረግ እንዲሁም ለታሰሩ ፖለቲከኞች የምህረት በመስጠት በሀገራቸው ሆነው ስለ ሀገራቸው በሰላማዊ መንገድ እንዲደራደሩ በር መክፈታቸው በደምና አጥንት ከተሳሰርናት ኤርትራ ጋር ከጦርነት ወደ ሰላም ያደረግነው ሽግግር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የከወኑት የዲፕሎማሲ ሥራቸው በሌሎች የአፍሪካና  የእስያ አህጉራት በእስር የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያንን ከእስር እንዲፈቱ በማደረግ ረገድ አመርቂ  በመሆናቸው እንደ ዲፕሎማሲ ድል የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ተግባርም ለድፍን ሁለት አስርት ዓመታት “ሞት አልባው ጦርነት” ተብሎ የሚጠራውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት እጅግ ለማመን በሚከበድ መንገድ ለኢሳያስ አፈወርቂ ጥያቄ በማቅረብ ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት ለሰላም በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ እንዲወያዩ ያስቻለ ነዋሪዎች በሰላም ተጉዘው ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው  እንዲገናኙ በር የከፈተ ነው፡፡

ይህ አኩሪ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ የዓለምን የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችን ቀልብ በመሳብ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ሲሉ በተለያዩ ድረ ገፆቻቸው አስነብበዋል፡፡ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ሻክሮ የነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ አድርጓል፡፡ ከነዚህ ተግባራት መካከልም ከእንግሊዝ ጋር የነበረው ግንኙነት በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በግንቦት ሰባት ውስጥ በሽብር ተግባር ተከሰው  ዘብጥያ በመውረዳቸው ምክንያት እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ሊሻክር ችሏል፡፡ በዶክተር ዐቢይ የለውጥ መሪነት የተነሳ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌም ከእስር በመለቀቃቸው እንግሊዝ ግንኙነቷን ዳግም በማደስ አጠናክራ እንድትቀጥል በር ከፍቷል፡፡ ስለሆነም ይህን ግንኙነት አጠናክረው በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ መክረው ግንኙነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ የባህር ማዶ የልማት ትብበር ያገኘቸው ድጋፍ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በእጅጉ መሻሻሉን የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡ ይህ የተሻሻለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፈጠር ለሀገራችን የሚሰጠው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ድርሻው የጎላ ነው ተብሏል፡፡

በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ባለሃብቶች ጋር በመሆን የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘታቸው ፓርኩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረትና ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ኢኮኖሚያችን ለማሳደግ የሚኖረውን ጥቅም ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይም የሆነው ሁለቱ ሀገራት በጋራ በሚሰሩበት ሀሳብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ተወካይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በተነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ኢኮኖሚያችን ለማሳደግ የሚኖረው ሚና የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ፊት ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የሚኖረውን አንድምታ ያጎለዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ስለሆነ ቴክኖሎጂውን በማሳደግ ረገድ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የወደፊት ራዕዩዋን ለማሳካት ሁነኛ በር ከፋች ግንኙነት ማድረጓ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ሆኗል፡፡ ስለሆነም ይህ አኩሪ ዲፕሎማሲ በተገቢው ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ ህዝቡ ሰላሙን፣ ልማቱን እንዲሁም የመኖር ህልውናውን ሊፈታተኑ የሚችሉ የቀውስ አክቲቪስቶችን በቻለው መጠን በትክክለኛው መስመር እንዲንቀሳቀሱ ማስተማርና መገሰፅ ይገባል፡፡

ሀገሪቷ ለምታደርገው የለውጥ ጉዞ ራሱን የቻለ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም የሀገር የዕድገት ጉዞ  በማይናወፅ ፅኑ መሠረት ላይ ያረፈ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ሁሉንም ህዝብ ያሳተፈ ሀገር ወዳድነት ስሜትና በእኔ ባይነት ስሜት የሰላም ሐዋሪያ በመሆን በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስቆም እና ዳግም እንዳይከሰቱ በማድረግ ለሀገሩ ጥብቅና የቆመ ዜጋ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ ደገሞ  የአገሪቱ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው ዘርፍ ተመራጭነትና ተቀባይነት  ያስገኛል፡፡

በዲፕሎማሲው ረገድ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው የዕርቀ ሰላም እና የአንድነት ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ስኬቶች እንዲመዘገቡ አድርጋለች፡፡ ከነዚህ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መካከልም የሁለቱ ሀገራት ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የባህል፣ የቋንቋና የእምነት ዕሴቶችን የተጋሩ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በእጅጉ የተሳሰሩ ሀገሮች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሀገራት ላለፉት ሁለት አስር ዓመታትን በሞት አልባ ጦርነት በመቆየታቸው በጋራ ተጠቃሚነታቸው ላይ ራሱን የቻለ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎ ቆይቷል፡፡ ይህን ተፅዕኖ በውል የተገነዘቡት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ለአቶ ኢሳያስ አፈወረቂ የመደመርና የይቅርባይነት መልክታቸውን በመላካቸው እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንትም መልዕክቱን በአዎንታ ተቀብለው የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች በደስታ ተቀብለው ሰላማቸውን በዓለም አደባባይ አሳይተዋል፡፡ ይህ የሁለቱም ሀገራት ዳግም ግንኙነት ከመደመርም በላይ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ሀገሮች አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ እሴቶች ስላሏቸው ነው፡፡ 

የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የልዑካን ቡድኖች ርስ በርስ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ያካሄዱት ውይይት  ግንኙነታቸው በሁሉም ዘርፍ የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ነው ፡፡ በተለይም በሁለቱም ሀገራት ወሰን አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችን የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በአሰብ ወደብ ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን በአረጋገጠ መልኩ ለመገልገል ስምምነት ላይ መድረሷ የአንድ እጅ ጭብጨባ መስሎ የቆየውን የጅቡቲን የወደብ በር ወደ ሁለት አማራጭ ከፍ በማድረጉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ታላቅ ተስፋን ይዞ መጥቷል፡፡ ይህ መሆኑ ሀገራችን ለምታደርገው በዓይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ የለውጥ ሥርዓት ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳርፋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሁለቱን ህዝቦች አንድ ከማድረጉም በላይ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ የፈጠረው አዎንታዊ ጫና የሀገራቱ ግንኙነት ከድንበር በላይ የሆነ በመሆኑ ትልቁ የአንድነታቸው ማሳያ ምልክት ነው፡፡ ስለሆነም በኤርትራ በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩ የግንቦት ሰባትና የኦነግ የተቃዋሚ ኃይሎች የሁለቱን ሀገራት አንድነት ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው ድርድር እንዲያደርጉ መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር ግንኙነት በር የከፈተ ነው፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን የሚያጠናክር የአሰብ-ምፅዋ መንገድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመሆን የማደስና የመጥረግ ሥራ እየተከናወነ ይገናል፡፡ ይህ የጥገና ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት በሚሆንበት ወቅትም የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም ባሻገር ለቀጠናው ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ በኩል የላቀ ሚና አለው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በሁለቱም ሀገራት ውህደት የኢኮኖሚ ትስስርን ከመፍጠሩ በተጨማሪ ሕዝቦቹ የባህል፣ የቋንቋና የእምነት ዕሴቶቻቸው ዳግም በተሃድሶ ወደ ነበሩበት የአንድነትና የፍቅር መስመር እንዲመለሱ አስችሏቸዋል፡፡የተለያዩ ሀገራት የልዑካን ቡድናቸውን ወደ ሀገራችን በመላክ በልዩ ልዩ የጋራ እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሳተፍ የሚያደርጉት መልካም የዲፕሎማሲ ተግባር ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በሀገራችን የፈነጠቀው የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ጮራ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በይቅር ባይነትና በመደመር ዕሳቤ አንድነቷን በመፍጠር ለሌሎች ሀገራት የኢንቨትመንትም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች ትገኛለች፡፡

በሌላ በኩል የአሰብ- ምፅዋን ወደብ ኢትዮጵያ መጠቀሟ ለጅቡቲ ስጋት ሳይሆን ታላቅ አጋርነትን የሚፈጥር ስለሆነ በጅቡቲ በኩል ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማይኖረው በተደጋጋሚ በባለሙያዎች ሲወሳ ቆይቷል፡፡  ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ መጠቀሟ ለጅቡቲ ተስፋ ሰጭ እንጂ ተፅዕኖ አይሆንም፡፡ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር አማራጭ ወደቦችን መጠቀም አለባት። የሀገራችን ህዝብ ቁጥርና እስካሁን በጅቡቲ በኩል የምናስገባው ምርት በቂ እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በቀጣይም የጅቡቲን በር ከምንጊዜውም በበለጠ የወደቡ አገልግሎት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን ወደቦች በአግባቡ በመጠቀም የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ለማሟላት፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ ምርቶቿን ወደ ውጭ በስፋት ለመላክ የጅቡቲ ወደብ ብቻውን  በቂ አይደለም፡፡

በወደብና በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት ምርቶችን በተፈለገው ጊዜ መላክና ማስገባት ስላልተቻለ የኑሮ ውድነትን በሰዓቱ መቀነስ አልተቻለም ፡፡ ስለሆነም ይህን የኑሮ ውድነት ለማሸነፍ ተጨማሪ ወደብ የሚያስፈልግ መሆኑ የጅቡቲ ወደብ መጨናነቅ ህያው ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ሁኔታ ለመቀነስ የአሰብና ምፅዋ ወደቦችን ሀገራችን ለመጠቀም መታሰቡ በጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን መጨናነቅ ከመቀነሱም ባሻገር የሚፈለገውን የወደብ አገልግሎት ያቀላጥፈዋል፡፡