ጥላቻ በፍቅር እንጂ በበቀል መች ተሸንፎ!

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና ታዋቂው አክቲቪስት ስዩም ተሾመ በፌስ ቡክ አካውንት ላይ አንድ ድንቅ  አስተሳሰብ አገኘሁና እጅግ ወደድኳት። አባባሏ  የአዲሱን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት  የሙስጠፋ መሀመድ ኡመርን ንግግር ናት። አቶ ስዩም   የምክትል ፕሬዚዳንቱን  ንግግር ቃል በቃል እንዳሳፈሯት፤ 

 

"በክልላችን በነበረው ብልሹ አስተዳደር ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል። ሁላችንም ተበድለናል። የተፈጸሙትን በደሎችና ችግሮች እንቁጠራቸው ብንል አንችልም። ይቅርታ አድርጉልኝና ማን ማንን እንደሚያጽናና አላውቅም። በደሎቹን ማስታወስና ቁስላችንን መቆስቆስ አያስፈልግም። አልሃምዱሊላህ አሁን ሁሉም አልፏል። ወገኖቼ እምባ ይብቃን፥ ማቃችንን እንጣል፥ በአዲስ መንፈስ እንነሳ። የጥላቻን እና ብቀላን ጦስ እስኪበቃን አይተናል። ወንድሙ የተገደለበት ሁሉ የገዳዮቹን ወንድሞች ልግደል ካለ ሁላችንም ያለ ወንድም እንቀራለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን። ጥላቻ በፍቅር እንጂ በበቀል አይሸነፍም። ስለዚህ ካለፈው ተምረን በፍቅር እና በይቅርታ፥ በአዲስ ሞራል እጅ ለእጅ ተያይዘን ለጋራ ሰላም፥ ዲሞክራሲና ልማት እንረባረብ"።

 

እውነት ነው ወንድሙ የተገደለበት ሁሉ የገዳዮቹን ወንድሞች ልግደል ካለ ሁላችንም ያለ ወንድም እንቀራለን!።  በቀል በቀልን ይወልዳል፤ ኪሳራን ያመጣል እንጂ አብሮነትን አያጠናክርም።  ባለፉት ሶስት ዓመታት አገራችን ክፉኛ ታማ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በእርግጥም  ህመሙ የጠናባቸው በርካታ የኦሮሚያና አማራ  አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ለለውጥ ሲሉ ህይወታቸውን  ሰጥተዋል፣ አካላቸውን ገብረዋል። ህውሃት  ደርግን ሲታገል  በርካታ  ወጣቶች  ህይወታቸውንና አካላቸውን እንደገበረ ሁሉ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታትም ለዛሬዋ ነጻነት በርከታ  የኦሮሞና  የአማራ ወጣቶች  መስዋዕት ሆነዋል። በእነዚህ ሃይሎች የለውጥ ሃይል የሆነው  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ  ቡድን  ወደ ስልጣን መምጣት ችሏል።  አሁን ላይ  እየተቀነቀነ ያለው “የፍቅር፣ አንድነትና መደመር” ፖለቲካ  የወጣቶች ደም  ውጤት ነው።  ይህ በወጣቶች ትግል እውን የሆነው  ለውጥ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ ወጣቶች  ያለአገባብ   እየተተገበረ  መሆኑን እየተመለከትን  ነው። በአገራችን ባህል ለአስክሬን ክብር ይሰጣል፤ ሰው በድንጋይ ተወግሮ አየገደልም፤ ቤተ ዕምነት አይቃጠልም።   

 

አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት የማይካዱ ስኬቶች ማስመዝገብ ብትችልም በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ረገድ ደግሞ በዚህ ዘመን  ሊፈጸሙ  ይቅርና ሊታሰቡ  የማይችሉ ወንጀሎች  በተለይ በህግ ታራሚዎች ላይ  ተፈጽመዋል።  ይሁንና ይህን በማራገብ ለአገራችን ዘላቂ  መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። በተመሳሳይ  ስለኢኮኖሚ ስኬት ብቻ በማውራትም  በደልን  መደባበስ  ተገቢ  አካሄድ  አይደለም።  ይሁንና  ሁሉንም  በልክ  በልክ ማየት  ተገቢ ይመስለኛል። ሁሉም ጽንፍ ቆሞ  በለው ማለት ለማንም አይበጅም።

ዘንድሮ ኢህአዴግን በህዝብ ከመበላት ያዳነው ባለፉት 27  ዓመታት  በኢኮኖሚው ዘርፍ    ማስመዝገብ በቻለው  ስኬት  ይመስለኛል። ይህ ባይሆን ኖሮ ኢህአዴግ ታህድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ በማለት ጊዜ ከመግደል ባለፈ ለውጥ ማምጣት አልቻለም።  ባለፉት ሁለትና ሶስት  ዓመታት  አገራችን በሁከት፣ ግጭትና ቀውስ ውስጥ  እንድትዘፈቅ ዋንኛ ምክንያት የሆነው ስግብግብነትና እኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ  በመስፋፋቱ  ይመስለኛል።  ፍቅር ሲቀዘቅዝ  ግለኝነትና ስግብግብነት  የነግሳል፤ አብሮነት ይላላል፤ አንድነት ይናጋል፤ አገር ወደ ቀውስ ታመራለች። ይህን በተግባር በአገራችን ተመልክተናል።

 

ዛሬ ጠቅላያችን በቀደዱት መንገድ አገራችን ወደ ፍቅር ጉዞ ጀምራለች። ፍቅርና ይቅር ባይነት በአገራችን እንዲሰፍን መንግስት የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። ያለፈን መውቀስና መክሰስ ለፍቅር ስንቅ አይሆንም።  እንደእኔ የትላንትን ወይም የደርግን ወይም የአጼዎቹን  በደል እያነሳን መነታረኩ፤ የበደሉንን እያሰብን ለበቀል የምንነሳሳ ከሆነ  ለነገ ፍቅራችን  ስንቅ አይሆንም።  መጪውን አዲስ ዓመት “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል እናከብራለን። አዲሱ ዓመት   የይቅርታና የፍቅር እንዲሆን  መንግስት ብቻ ሳይሆን  ዜጎችም  ሆደ ሰፊ  በመሆን  ቂም በቀልን  በመተው አብሮነትን ልናጎለብት  ይገባናል። አገር በበቀል አይገነባም፤  ክፉ ክፉውን  በማስታወስም አብሮነት አያጠናክርም።

 

አገራችን  በርካታ ልዩነቶች የሚስተዋልባት በመሆኗ፤ ቀጣይና የሁላችንም እንድትሆን ከፈለግን የሁላችንንም ፍላጎት  ታሳቢ ማድረግ  የግድ ይላታል። የሰጥቶ መቀበል መርህን ልንተገብር ይገባናል። በየትኛውም  ስርዓት  የሁሉም ቡድኖች ሁሉም ፍላጎቶች ሊሟሉ አይችሉም። ይልቁንም  ሰተን የምንቀበለውን ነገር እናስብ።  መቀበል ወይም መጠቀምን ብቻ በማሰብ አብሮነት አይጠናከርም።  በፌዴራሊዝም የምናገኛቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የምናጣቸውም ነገሮች መኖራቸውን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው።  በአገራችን  የሚስተዋሉ ልዩነቶች ማስተሳሰሪያው “ፍቅርና ይቅር ባይነት” ብቻ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ  የፍቅር፣ የመቻቻልና አብሮነት  መንገድን  እንዴትና በምን አኳኋን  እንደምንጓዝበት  በተግባር አሳይተውናል። ይህ መንገድም የይቅር ባይነትና የፍቅር መንገድ  ነው።

 

ከአምስት ወራት  በፊት   በአገራችን ተከስቶ የነበረው ሁኔታ እጅግ አስፈርቶን በርካቶቻችን  ተስፋ  አስቆርጦን የቁልቁለቱን ጉዞ  ልንጀምር  ነው ብለን  ሰግተን ነበር።  አዎ ያ ወቅት ከስጋት ያለጣለው አገር ወዳድ ይኖራል ብዬ አላስብም።  በአጼዎቹም፣ በደርግ፣ በኢህአዴግ  በርካታ በደሎች በአገራችን  ተፈጽመዋል፤ ይሁንና  አገራችን  ይህን ሁሉ ውጣ ውረዶች ተሻግራ ዛሬ ላይ መድረስ የቻለችው በይቅር ባይነትና በፍቅር  ነው። ሰው በደሉን እያሰበ  ወደ እርቅ  አይሄድም።   ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ  ጀምሮ በአገራችን  ፍቅር እንዲጎለብት  ይቅር ባይነት እንዲንግስ  በርካታ ስራዎችን  በማከናወን  ላይ ናቸው።  እርሳቸው እንዳሉት  ማሰር ቀላል ነው፤ ማሳደድ ቀላል ነው፤ መግደል ቀላል ነው፤ የታሰረን መፍታት፤ የተሰደደን መመለስ፤ የተበላሸን ማቅናት፣ ይቅር ባይነትን ማንገስ  እጅግ ከባድና ውስብስብ  ነው። እልህና በቀል አገር አየገነቡም፤ የህዝቦች አብሮነትን  አያጠናክሩም። የፍቅር እንጂ የእልህና የበቀል መንገድ ሩቅና ውስብስብ ናቸው።  ዛሬ አገራችንን ልንገነባት የምንችለው በ“ፍቅር ስንደመር” እና  የገጠሙንን ውጣ ውረዶች   ደግሞ “በይቅርታ ስንሻገር” ብቻ ነው።