ጥቂት ስለ ፍኖተ ካርታው

በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የትምህርት አፈፃፀም ማህበረሰብ ተኰር ነው። ማህበረሰቡ የማይሳተፍበት የትምህርት አፈፃፀም ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ከዚህ አኳያ ሰሞኑን መንግስት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል። ፍኖተ ካርታው የተደራጀ ሃሳብን የያዘ ነው። ይህን ፍኖተ ካርታ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ ከመንግስት ጎን በመቆም መስራት ከማህበረሰሱ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ አንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የዜጎቿን ህይወት መለወጥ የምትችው በሰው ሃብቷ አቅም መሆኑ ግልፅ ነው። እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና እና ሲንጋፖር የመሳሰሉ አገራት በአገራቸው ልማትን ማምጣት የቻሉት ለትምህርትና ስልጠና በሰጡት ትኩረት ነው። በዚህም የሰው ሃብታቸውን በማልማትና እድገት በማስመዝገብ የህዝቦቻቸውን ኑሮ መለወጥ እንደቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ላለፉት ሃያ ዓመታት በስራ ላይ የነበረው የትምህር ፖሊሲ ያስገኛቸው ውጤቶች ቢኖሩም በብዛት ላይ በማተኮሩ በትምህርት ጥራት ላይ ችግር እንደነበረበት ይታወቃል። ይህም በአብዛኛው ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል።

ይህን ችግር ለመፍታትም መንግስት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል።  በመንግስት የተዘጋጀው ይህ ፍኖተ ካርታ የአገሪቱን የትምህርት ስልጠና ችግሮችና ተግዳሮቶችን የሚያመላክት ነው። ችግሮቹን በጥናት ላይ ተመርኩዞ ለመስራት ፍኖተ ካርታው የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

ፍኖተ ካርታው የዘርፉን ችግሮች አብጠርጥሮ ለማስቀመጥ ልዩ ትኩረት ማድረጉ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። የትምህርት ሥርዓቱ በተደራሽነት፣ በፍትሐዊነት፣ በጥራትና አግባብነት አኳያ ስር የሰደደ ችግር ያለበት መሆኑ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ ነው።

ሰነዱ እንደሚያመለክተው መንግስትም የትምህርት ዘርፉ ከገባበት ዝቅጠት ለማውጣት ቁርጠኝነት መሆኑን ያስረዳል። ይህም ለአገራችን የሰው ሃይል ብቃት ተገቢ ሚና ሊጫወት የሚችል ነው።

በዚህ መሰረትም የትምህርት ስልጠናው የማሻሻያ ሃሳቦች በርካታና ወሳኝ ለውጦችን እንዲይዝ ተደርጓል። የትምህርት ስርዓቱ ፍልስፍና እና መዋቅር ለመከለስ፣ የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከር እንደታሰበ ሰነዱ ያስረዳል።

ሰነዱ 70፡30 የሚለው የመስክ ምጥጥን ፖሊሲ ቀርፆ ጉዳዩ በገበያና ፍላጎት እንዲመራ፣ የወጪ መጋራት ድርሻ በ15 ዓመታት ውስጥ ከ15 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ እንዲል፣ የቋንቋ ትምህርት ፖሊሲው እንዲሻሻል፣ የትምህርት ግብርና የሙያ ምዘና ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ዋና አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል፣ የተግባር ልምምድ በሰፊው ስራ ላይ እንዲውል፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብዝኃነትን በሚያዳብር መንገድ እንዲሰጥ የሚሉና ሌሎችም ሃሳቦች በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

እነዚህ  ጉዳዩች በጥቅል ሲታዩ የትምህርት ስልጠና ጥራት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ የሚታየውን ችግር መፍታት ይገባል። ለዚህም አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መከተል ይገባል። እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንደሚኖሩና በችግሮቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ የትምህርት ሥርዓቱ አጠቃላይ መገለጫዎች ናቸው።

በመሆኑም አገራችን “ዕውቀት ሁሉ ከውጭ የሚገባ ነው” ከሚባልበት ዘመን ወጥታ፣ ዛሬ ላይ በራሷ አቅም የትምህርትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በዚህም በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ መስኮች የቅበላ አቅሟን ብታሳድግም ጥራቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።  

ፍኖተ ካርታው የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ የሚያደርገን ነው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን በበለጠ ሁኔታ እንዲከውኑ የሚያደርግ ነው።

ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራትን የሚያጎለብቱ ሰነዶች፣ ከመስክ ጥናትና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተገኙ ግብዓቶች የተቀመሩበት ነው። ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የላብራቶሪና የሰርቶ ማሳያ ግብዓቶች በተሟላ መልኩ እንዲኖሩና እነዚህ ካልተሟሉ ከፍተኛ ትምህርት መክፈት አያሰፈልግም የሚል ጉዳይንም የያዘ ነው።

በስራ ላይ የለውን የትምህርት ስልጠና ፖሊሲን የሚያሻሽለው ይህ ፍኖተ ካርታ፤ የሀገሪቱን የሰው ሃይል ፍላጎት መሰረት አድርጎ ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት ዓይነት እንዲያጠኑ የሚደረግበት ይሆናል።

ፍኖተ ካርታው በፍላጎትና በአቅርቦት የተሟላ ትምሀርት በማቅረብ ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ብቁ ሃይል ለማፍራት እገዛ ይኖረዋል። እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት መዋቅር የሚያሻሽልና ዩኒቨርስቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው የሚግዝ ነው።

በፍኖተ ካርታው መሰረት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 12ኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ተብሎ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ጎን ለጎን የሚሰጥበት መርሃ ግብር ይኖራል።

ከዚህ በተጨማሪ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ስለጠና ሚኒስቴር፣ አጠቃላይ የትምሀርት ስልጠና ሚኒስቴር የክህሎትና ስራ ፈጠራ ሚኒስቴር ተብሎ ለሶስት ይከፈላል። ይህም ውጤታማነትን መሰረት ያደረገ ነው።

በአጠቃላይ በጥራት ላይ የተመሰረተው ይህ ፍኖተ ካርታ አገራችን የጀመረችውን ለውጥ የሚያጠናክርና አቅም ያለውን የሰው ሃይል በሁሉም መስኮች መፍጠር የሚችል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ባለው አቅም ሁሉ ለተግባራዊነቱ ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።