የጥንካሬያችን ምንጭ

የአገራችን የለውጥ ድባብ ብዙዎችን እየማረከ ነው። የጥንካሬያችን ምንጭ መሆኑንም እያረጋገጠ ነው። በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ከውጭ ኢንቨስትመንት እየሳብን፣ በአገር ውስጥም ደግሞ የግብር አሰባሰብ ስራችንን ወደ ዘመናዊት እየቀየርን ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የሚያስችለውን አቅምም እየገነባ ነው።

በተጨማሪም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለውጡን ለመደፍ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ድጋፍም እያደረጉ ይገኛሉ። በቅርቡ ከዓለም ባንክ የተገኘው የአንድ ቢሊየን ዶላር ድጋፍንና የጀርመን መንግስት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሊያደርግ ያሰበው ትብብር ተጠቃሾች ናቸው።

የእነዚህ ተግባሮች ድምር ውጤትም ለውጡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቅም ፈጣሪ አቅም እንዲሁም የጥንካሬያችን ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለውጡን በመጠበቅ በመፈጠር ላይ ያለውን አገራዊ የኢኮኖሚ ጥንካሬ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት።

ለውጡ ኢኮኖሚውን እያንቀሳቀሰው ነው። የተቀዛቀዘውን የልማት ስራም እያነቃቃው ነው። ዛሬ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ቢሊዩን ዶላሮች ካዝናችን ውስጥ ይገኛል። ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተስፋፋ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች በባለሃብቶች እየተፈለጉ ነው። በእነዚህ ሁኔታዎች ሳቢያ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአገራችን ኢኮኖሚ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትንበያ እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል።

እርግጥ ዓለም አቀፉ ተቋማት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በዋራቶች ውስጥ የሚያወጧቸው የትንበያ ዘገባዎች ለእኛ ከማሰብ አሊያም ኢትዮጵያን ለመጥቀም ከመፈለግ የመነጩ አይደሉም። በአገራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የምጣኔ ሃብት አቅምን ከመተንበይ የተገኙ ግኝቶችን መሰረት አድርገው እንጂ። በመሆኑም በለውጡ መጪ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀጥል እየነገሩን ነው። አንጻራዊ ሰላምን የፈጠረው ለውጡ ኢንቨስትመንትን በተገቢው ሁኔታ እየሳበ ስለሆነ በኢኮኖሚው ረገድ ውጤት ማምጣቱ ትክክል ነው። ይህም ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አቅም በፈቀደ መጠን ለመተግበር የሚያስችል ነው።

መንግስት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል።

አገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል።

መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ በፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ሳቢያ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ አገራችን እየተመሙ ነው።

በአገራችን ውስጥ እያደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው።

በተጨማሪም አገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ዛሬ የውጭ ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህም አገራችን የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም እና ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም ለባለ ሃብቶች የተዘጋጀው የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ብሎም በታዋቂው አየር መንገዷ የዓለም ገበያን በቀላሉ ለመድረስ መቻሏ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የሚያሰራ ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሃብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግስት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል እየተካሄደ ነው። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ አእድርጓል።

መንግስት መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ እየሰጠ ነው። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን የሚያሳድግ ይሆናል።

እነዚህ ጉዳዩች ተፈላጊነታችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናከር የተለያዩ የውጭ ሃይሎችን እየሳቡ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በለውጡ በመሳባቸው በአገራችን ያለውን ምቹነት ተጠቅመው በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ የጥንካሬያችን ምንጭ ጭምር እየሆነ ስለመጣ ለውጡን መንከባከብና እንዳይገናቀፍ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ከአገራችን ህዝብ የሚጠበቅ ተግባር ነው።