“የአዲስ ዓመት ስጦታ ለሃገሬ”

ኢትዮጵያውያን የጳጉሜን ወር በተለየ መልኩ በበጎ አድራጎት ስራዎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው።የዿጉሜ ወር የተለየ የዘመን አቆጣጠር ለምትከተለው ኢትዮጵያችን ብዙ ተግባራትን መከወኛ ወር ተደርጋ ትቆጠራለች። የዘንደሮው የዿጉሜ ወርም “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን እየተከበረ ይገኛል።

 

ከእነዚህም መካከል የጽዳት ስራ፤ ኑሯቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ በማሰባሰብና አረጋውያንን በመደገፍ መላው ህብረተሰብ የመንግስትና የግል ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። የዿጉሜ ወር ቂም በቀልና ጥላቻን ለማስወገድና ያለፈውን ይቅር የምንባባልበት እንዲሆንም መርህ ወጥቶ እየተሰራበት ነው።

 

በዚህ መሰረት ጳጉሜ 1 የሰላም ቀን፤ ጳጉሜ 2 የፍቅር ቀን፤ ጳጉሜ 3 የይቅርታ ቀን፤ ጳጉሜ 4 የመደመር ቀን፤ ጳጉሜ 5 የአንድነት ቀን በሚል ስያሜ በመላ አገሪቷ በልዩልዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል። የቡሄ፣ ዘመን መለወጫ፣ ሻደይ፣ መስቀል፣ እሬቻ እና ሌሎችም በዓላት በመርሃ ግብሩ የተካተቱ በዓላት ናቸው።

 

አዲሱን አመት አንድ ሆነን አንድ እንበል በሚል መርህ  ከነሃሴ አጋማሽ እስከ መስከረም መጨረሻ በሚዘልቀው አዲስ አመት በዓል ኢትየያውያን ዲያስፖራው እና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት መርሃ ግብሮች የሚካሄድ መሆኑንም የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል።ከነዚህ መካከል ዋነኛው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው።

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  በሚሊኒየም አዳራሽ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜ 1/2010 ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ክፍት የነበረ ሲሆን፤በዚህም የተለያዩ ልገሳዎች ተከናውነዋል። ለአብነትም የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ ለ30 ሺህ አቅም የሌላቸዉ ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ለ7 ሺ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እንዲሁም የደም ልገሳ የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡በዚህ በጎ ተግባር በመሳተፍ የጠቅላይ ሚንስትራችንን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጥሪ በቀጣይነትም  ማረጋገጥ  ይገባል።

 

ላለፉት አራት ቀናት “የአዲስ ዓመት ስጦታ ለአገሬ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የተከናወነው የአዲስ ዓመት የስጦታ መርሃ-ግብር ብዙ ነገር አስተምሮን አልፏል። በስጦታ መርሃ-ግብሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ፣ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና ሌሎች ስጦታዎች በበጎ አደራጊዎች ተበርክተዋል። ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በህዝብ መካከል መተሳሰብን ከመፍጠር ባሻገር ማህበራዊ ችግርንም የሚያቃልል በመሆኑ ተግባሩ ባህል ሆኖ ሊቀጠል ይገባል። ይህ ተግባር ተጠናክሮና ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።

 

ከዚህ አገልግሎት የሚያስተባበር ወይም ቀስቃሽ አካል ካለ ለተቸገሩ ዜጎች እጅ መዘርጋት ቀላል እንደሆነ ተምረናል። ግን ደግሞ በየዓመቱ በዓላትንና ወቅትን ጠብቆ የሚደረግ ስጦታ ችግርን በዘላቂነት እንደማይፈታም አስተውለንበታል። ስለሆነም ዓመቱን ሙሉ ሰዎች ካላቸው ቀንሰው ለተቸገሩ የሚያካፍሉበት ተቋማዊ አሰራር በመፍጠር የልገሳ ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ ይሆናል፡፡በተቋም ደረጃ ወጥ አሰራር ቢኖረው በጣም ጥሩ ነው፤ሰው የሚችለውን አስር ብር ይሁን መቶ ብር ይሁን በቋሚነት የሚሰጥበትን አንድ የአሰራር ስርአት መዘርጋት አለበት። 

 

በአዲስ አበባ ባሉ ክፍለ ከተማዎችና ወረዳዎች ለኑሮ አመቺ ባልሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን እጅግ የተጎሳቆለ ኑሮን በመግፋት ላይ መሆናቸው በተመሳሳይ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ “በአንድ ወረዳ አንድ ቤት” በሚል መሪ ቃል የአረጋውያንንና የችግረኞችን ቤት የማደስ ሥራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተከናወነ መሆኑም ሌላኛውና በአዲሱ አመት ብዙ ቁምነገር የሸመትንበት አዲስ ተግባር ነው።

 

በአርቲስቶች፣ በአትሌቶች፣ በታዋቂ ስፖርተኞችና በወጣቶች የተጀመረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አገራዊ ግዴታ እና ሀላፊነትን ከመወጣት በዘለለ የህሊና እርካታ የሚሠጥ ሰብአዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በአዲስ ተስፋ ቀመር ጥላቻን መቀነስ፣ ይቅርታን ማባዛት፣ ያለንን ማካፈል፣ ፍቅርን መደመር በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊሳተፍ ይገባል። 

 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዚህም ባሻገር የሆኑ ፋይዳዎች አሉት። በጎ ፈቃደኞች ለህበረተሰቡ ከሚሰጡት ጠቃሚ አገልግሎት ባሻገር ራሳቸውም በሰርቶ መማር ሊበለፅግ የሚችል ልምድ እና ተሞክሮ የሚያገኙ ሲሆን በሂደቱም ህዝባዊ ፍቅርን የሚገበዩበት መልካም አጋጣሚ ይሆናል፡፡ አዲሱ የልማትና የለውጥ ንቅናቄ በሁሉም መስክ የህዝቦችን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ የለውጥ ንቅናቄው አዳዲስ አስተሳሰቦችን መያዝ ብቻ ሳይሆን እነዚህንኑ አዳዲስ አስተሳሰቦች በተግባር ማሳየትና በተግባር ከሚገኘው እውቅት በመነሳትም መልሶ የተሻለ ስራ መስራት ይጠይቃል፡፡ ለዚህም የእውቀት እና የጉልበት ሀይል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው የልማት እድገት ደረጃችን ብዙ ስራዎች በጉልበት ሀይል የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በሌላ አገላለፅ የማሽንና ለሌሎች ቴክኖሎጂዎች ያልተስፋፉበት የእድገት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ወቅት ሰፊ የጉልበት ሀይል ብቻ ሳይሆን የጉልበት ሀይልን በቁጠባና በውጤታማነት መጠቀም ይጠይቃል።

 

በዚሁ መሰረት  እድገትና ተደራሽነት የተስተዋለበት የበጎ ፈቃደኝነት ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ወጣቶች እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን አስተባብረው ወደ ህብረተሰቡ በመሄድ በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በማቀናጀት የተሻለ ስራ መስራታቸውን አሳይተውናል፡፡

 

በመሆኑም ወደፊት የታቀደና በተገቢ ዝግጅት የታገዘ ንቅናቄ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ወገኖች ችግሮቻቸውን አርመው ለመፍትሄው እንዲተጉና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጥራት ያለው የልማት ተደማሪ አቅም እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው። 

 

ሌላው ልምድ ሊወሰድበት የሚገባው ጉዳይ የአዲስ ዓመት መቀበያ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና  የዲያስፖራ አባላት የተሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ ነው። በአራዳ ክፍለ ከተማ   በአትክልት ተራ እና አካባቢው በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የፌዴራል ከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር ዓባይ እንዳስታወቁት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሞችን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውን በጎ ተግባር እና ተሞክሮ ወደ ክልል ከተሞች በማስፋፋት ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ይህ ደግሞ መደመርን እደግፋለሁ ለሚል ሁሉ ቁም ነገር ያለውና እራስን በተግባር ለመፈተሽ የሚያስችል ነው።

 

በአትክልት ተራ እና አካባቢው በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ የአዲስ አበባ ከተማ የካቢቤ አባላት ፣ የዲያስፖራ አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ በተያያዘ ዜናም የዲያስፖራ አባላት በኣራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የቀይ ባህር የጋራ መኖሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ አነስተኛ ቤተ መጽሃፍት በማቋቋም የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጽሃፍት በስጦታ ማበርከታቸውም ተሰምቷል፡፡

 

ሌላም ለአዲስ አመት የሚሆን ሰጦታ በአስተዳደሩ በኩል ተበርክቷል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ መጠለያ የሌላቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 199 የከተማዋ ነዋሪዎች የመንግስት ቤት የመስጠታቸው ጉዳይ ከቤት የዘለቀ ትርጉም አለው።

 

ከአሁን በኋላ በከተማዋ የሚደረጉ የቤቶች ግንባታ ነዋሪዎችን ካሉበት ቦታና ከማህበራዊ ህይወታቸው በማያፈናቅል መልኩ በኖሩበት አካባቢ ቤቶችን በመገንባት እንደሚሆን መጠቆሙ የትርጉሙን ፍንጭ ይሰጣል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ የትናየት ሙሉጌታ በበኩላቸው ክፍለ ከተማው ለነዋሪዎች ከሚያስተላልፋቸው 199 ቤቶች መካከል 129 በእለቱ እንደተላለፉና ቀሪዎቹ 67 ደግሞ ጥገና ተደርጎላቸው እንደሚተላለፉ አስታውቀዋል። ቤቶቹን ከአሁን በፊት ኮንዶሚኒየም ቤት እድለኛ የሆኑ፣ ሃብት አፍርተው እያለ በቀበሌ ቤት መኖር የቀጠሉ እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ ቤቶቹን ይዘው የነበሩ ግለሰቦች ይኖሩባቸው እንደነበር ገልፀዋል። ተጠቃሚዎችን የመለየት ሂደቱ በግልፅ መመዘኛና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በቀጥታ በመምረጥና በመተቸት ተሳትፈውበት የተፈፀመ መሆኑንም ገልፀዋል።የቤት ባለቤት ከሆኑት ውስጥ 147ቱ ሴቶች ናቸው።ትርጉሙም ይህና ከመልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጋር የተያያዘው የአዲስ አመት የለውጥ ስጦታ ነው።