የለውጥ ኃይልነትን…

ወጣቱ ኃይል የለውጥ እንቀሳቃሹ ዋነኛ ሞተር ነው። የታገለለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ የሚችለው በምክንያታዊ አስተሳሰብ እየተመራ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት እንጂ በስሜታዊነትና በጠባቂነት መንፈስ ሊሆ አይገባም። በመሆኑም ወጣቱ ምክንያታዊ አስተሳሰብን መሰነቅ ይኖርበታል። ከስሜታዊነት የወጣ፣ በምክንያት ላይ ተመስርቶ የሚቃወምና የሚደገፍ ወጣት፤ በሀገራችን ውስጥ መኖሩ በለውጥ ሂደት ላይ ላለችው ኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት የሚኖረውን ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እናም ወጣቱ የለውጥ ኃይልነቱን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል።

ስሜታዊነት ለማንም አይበጅም። በሁሉም ጉዳዩች ላይ በሰከነ ሁኔታ መመካከር ያስፈልጋል። ስሜታዊነት ራስን፣ አካባቢንና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር ነው። ዜጎቿ ስሜታዊ በመሆናቸው ምክንያት ያደገች ሀገር የለችም። እንዲያውም ከስሜታዊነት የሚገኘው ነገር፤ የሰው ልጅ ህይወት እንደ ዋዛ መጥፋት፣ የንብረትና የሀገር ውድመት ብቻ ነው።

የሰው ልጅ ስሜቱን እስካልተቆጣጠረ ድረስ በራሱ ህይወትም ይሁን በሚኖርባት ሀገር ውስጥ የሚፈጥረው መዘዝ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። በስሜት ውስጥ ሆነን የምንፈፅማቸው ማናቸውም ተግባራት የሚያስከፍሉን ዋጋ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ዜጋ ከስሜታዊነት ራሱን በማራቅ ግራና ቀኙን ማገናዘብ፣ በእርጋታና በሚዛናዊነት ነገርን መፈተሽ አለበት።

በተለይም ወጣቱ ያለበት የዕድሜ ክልል አፍላና “ትኩስ” በመሆኑ ለስሜታዊነት ቅርብ ነው። ሆኖም እንዳልኩት ስሜታዊነትን መግራት ይኖርበታል። ወጣቱ በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ ሚዛናዊና ሁሉንም ነገሮች በልካቸው የሚመዝን መሆን አለበት። ራስን መቆጣጠር የስልጣኔ አንድ ማሳያ ነው።

የሰለጠነ ሰው ራሱን በመቆጣጠር ድርጊቶቹ ወደ አላስፈላጊ ንትርክ እንዳይሄዱ ያደርጋል። የሰለጠነ ሰው ችግሮች ካሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታል። የሰለጠነ ሰው የራሱን መብት ሲያከብርና ሲያስከብር የሌሎችንም መብቶች ያከብራል፤ ያስከብራል። ‘የእኔ አስተሳሰብና ድርጊት ብቻ ትክክል ነው’ የሚል ጊዜ ያለፈበት አሮጌ እሳቤ፤ ሀገራችንና የለውጥ አመራሩ ከሚከተሉት የዴሞክራሲ መርህ ጋር እንደሚጋጭ ይገነዘባል። ለፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ቦታ የለውም። ይፀየፋቸዋል። ለሌሎችን ያከብራል እንጂ አይጠየፍም። በማንም ላይ ያልተገባ ስምን አይለጥፍም። አክብሮቱና መቻቻሉ እዚህ ሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ሀገራዊ መግባባት ምን ያህል ጠቃሚና ወሳኝ እንደሆነ ይገነዘባል። የሰለጠነ ወጣት ዳርቻው እስከዚህ ድረስ ነው። ከፍ ሲልም የስልጣኔ ዳርቻው ለቀጣናው፣ ለአህጉሩና ለዓለም በማሰብም ሊገለፅ ይችላል።

ሀገራችን ውስጥ የመጣው ለውጥ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ወጣቱ የለውጡ አካልና ፊት ለፊት የቆመ ቀዳሚ ተዋናይ መሆኑ አይታበይም። የለውጡ ባለቤትም ነው። እናም የለውጥ ኃይልነቱ በምክንያት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። በምክንያት ላይ ተመርኩዞ ሊቃወምም ይሁን ሊደግፍ ይገባል። በስሜታዊነትና በጭፍን መደገፍም ይሁን መቃወም ያልሰለጠነ ሰው አተሳሰብ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።

ርግጥ አንዳንድ ስራቸው ሁሉ ግራ የሆኑ እኩይ ኃይሎች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ወጣትን ባልተገባ መንገድ ሊቀሰቅሱትና ምክንያታዊነቱን ሊያስቱት ይችላሉ። ወጣቱ ግን ሁሌም በምክንያታዊነት የሚመራ መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል። አስተሳሰቡ የተቆራኘው ከምክንያታዊነቱ ጋር እንጂ ከስሜታዊነት ጋር አለመሆኑን በድርጊቱ ሊያሳያቸው ይገባል።

ወጣቱ የለውጥ ቀልባሾችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን ተከትሎ እንዲሁም እኩይ ሃይሎች ለሚፈፅሙት ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት በጨዋነት መንፈስ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። በዚህ በሳል ተግባሩም ራሱ ያመጣው ለውጥ እንዳይደናቀፍ ያደርጋል።

ርግጥ አሁን የምንገኝበት የለውጥ ወቅት ምክንያታዊነት እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው። ምክንያታዊነት ወሳኝነቱ ካልተረጋገጠ አደጋ ይኖረዋል። ለውጡ መሰረት ይዞ ለቀጣይ ስራዎች እንዳይነሳሳ ያደርገዋል። ስለሆነም አሁን በምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ሚዛናዊነት መኖር አለበት። ለዚህ ደግሞ ወጣቱ አካባቢውን ሁከት እያነፈነፉ ህግን ለመጣስ ከሚሹ አካላት ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል። እንዲሁም በሚያከናውናቸው የህግ የበላይነትን የማይፃረሩ ተግባራት የለውጥ አደናቃፊዎችን አደብ ማስገዛት አለበት።

እንዳልኩት ወጣቱ የለውጡ ባለቤት ነው። የዛሬው ወጣት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ የሚሄድ አይደለም። በትግሉ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው። በዚህም ዛሬ ቀና ብሎ በማንነቱ በመኩራት እንዲሁም በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። አዲሱን ዓመት የተቀበለውም በዚሁ መንፈስ ነው።

ርግጥ አመዛኙ ወጣት ምክንያታዊ አስተሳሰብንም እየተላበሰ ነው። ችግሮች ቢኖሩም በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንደሚፈቱ ያውቃል። ይህ አቋሙ ለውጥ አደናቃፊዎችን ከህግ ፊት በማቅረብ ሲገለፅ ተመልክቻለሁ። ችግሮቹን በግልፅ ውይይት በማሳየትና የሚፈቱበትን አግባብ በማመለላከት ጭምር የመፍትሄ አካል እየሆነ ግልፅ ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚው ቢያድግም መጠነ ሰፊው ድህነት ከፍተኛ ስለነበር ሁሉንም ማዳረስ አልቻለም። ሆኖም በዶክተር አብይ መሪነት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ወጣቱ ያውቃል። ይህ የለውጥና የነፃነት አውድ በሂደት እንደሚጠቅመውም ይገነዘባል።

በምክንያታዊነት የሚያምነው ወጣት ባለፉት ዓመታት የሚገባውን ጥቅም ባያገኝም፣ በአሁኑ ወቅት በራሱ ትግል የፈጠረው ለውጥ እንደሚጠቅመው ይገነዘባል። መንግስትና ህዝቡ በድህነት ላይ በከፈቱት ዘመቻ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህንኑ ወጣት ነው።

ለውጡን እየመራው ያለው የዶክተር አብይ መንግስት የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅምም ይሁን ብቃቱ ያለው ነው። ወጣቶች ያሉባቸውን ጊዜያዊ ችግሮችንም እንደሚፈታ ጥርጥር የለውም። እናም ወጣቱ በሚዛናዊ አስተሳሰቡ መንግስት ያለበትን ችግር እንደሚፈታ በመገንዘብ መጪው ጊዜ የእርሱ መሆኑን በማወቅ አሁንም ሚዛናዊና የሰከነ አስተሳሰቡን እየጠበቀ የለውጥ ሃይልነቱን ማሳየት ይኖርበታል።

ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረው ያለው ለውጥ ለወጣቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ነፃነትንም አብሮ ያጎናፀፈው ነው። ነፃነት ደግሞ ለሁሉም ነው። የአንዱ ነፃነት ለሌላኛው ችግር አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንዱ ያለው ነፃነት ሌላውም አለው። በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሁሉም ሰው እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ የነፃነትም እኩልነት የሚገደብ አይሆንም።

ስለሆነም አንዱ ያገኘውን ነፃነት ሌላኛውም ሊጠቀምበት ሲፈልግ ምንም ዓይነት ገደብ ሊደረግበት አይገባም። ጥቃቅን ምክንያቶችን እያነሱ፤ የአንዱን ነፃነት ለመገደብ መሞከር ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲንም የሚቃረን ምልከታ ነው። ስለሆነም የለውጥ ኃይሉ ይህን እውነታ በምክንያታዊነት ላይ በመመርኮዝ ሰከን ብሎ ማሰብ ይኖርበታል እላለሁ።