…ትኩረት ይሰጠው!

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግለሰባዊና አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው።

በአገልግሎቱ አገራዊ ንቅናቄ መቀጣጠል ይኖርበታል። በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ሌሎች አካባቢዎችም በአርአያነት ሊከተሉት የሚገባ ይመስለኛል።

ሁሉም ክልሎች አገልግሎቱ ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሰሩ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህዝባዊ ባህል እንዲሆንና ከአገልግሎቱ የሚገኙት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን እንደ ህዝብ ልናጣጥማቸው እንድንችል የሚያደርጉን ናቸው። እናም ሁሉም አካል ለአገልግሎቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ክልሎች ለአገልግሎቱ ትኩረት መስጠት ያለባቸው የሚያስገኘውን ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅምች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መካሄድ አገራዊ ስሜትንና የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጎለብት ነው። አገልግሎቱ ዜጐች በተለይም ወጣቶች ያለ ማንም አስገዳጅነት ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ያስችላል።

ወጣቶች የዚህች አገር ገንቢዎች በመሆናቸው አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል አካል ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው አገር በየጊዜው የወጣቶችን አቅም ቢጠቀም ልማታዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

ስለሆነም ወጣቶች በአገራቸው ያመጡትን ለውጥ በበጎ አገልግሎት ስራዎች እየደገፉ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲሄድ ለማድረግ የአገልግሎቱ ትኩረት ማግኘት ወሳኝ ይሆናል። ክልች ይህን አቅም መጠቀም ከቻሉ፣ የአገርን ኢኮኖሚ በራስ አቅም ለማሳደግ የሚቻልበትን አንድ መንገድ ተከትለዋል ማለት ይቻላል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ራሳቸውን፣ ህዝባቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ያደርጋል። አገልግሎቱ ወጣቶች ስራን ሳይንቁ መስራት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እንዲያውቁና የስራን ክቡርነትም እንዲገነዘቡ በማድረግ አገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ከስራ ባህላችን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ያርቃል፣ ያስተካክላል።

ጉዳዩን ከወጣቶች አኳያ ስንመለከተው ወጣቶች አገር መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር እንዲያዩ ያደርጋቸዋል። ህዝቡ ለእነርሱ ያለውን ከበሬታና ከእነርሱ እየተማረ ሊያስተምራቸው ጭምር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ የህዝብ ፍቅር እስከየት ድረስ እንደሆነም እንዲገነዘቡ የሚያደርጋቸው ነው።

ለአገልግሎቱ የሚሰማሩ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ የሰላም አሰፈላጊነት ላይ በማተኮር ህብረተሰቡን ያስተምራሉ። ከግጭት ምንም እንደማይገኝና የሰላም ጠቀሜታ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን ፋይዳ ከህይወት ልምዳቸው እየተነሱ ሊያስገነዝቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በለውጥ ሂደት ላይ ላለችው አገራችን እጅግ ጠቃሚ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በቅርበት በህዝብ መካከል ተገኝቶ ስለ ሰላም ጠቀሜታ ማስተማር ያስፈልጋል። ስለ ሰላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ፋና ወጊ መሆኑንም ማስረዳት ይገባል። የአገራችንንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ ለውጥ ቀልባሽ ሃይሎች መኖራቸውን በአካል ህዝቡ ውስጥ ገብቶ መንገር ይገባል።

ሁሌም ህዝብ ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የመስጠት ባህል ያለው በመሆኑ ይህንኑ በቅርበት ተገኝቶ እንዲያጠናክረው ማድረግ ያስፈልጋል። ክልሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እንዲህ ዓይነቱን ሰናይ ተግባር እንዲከናወንበት ለማድረግም ይጠቀሙበታል።

ስለሆነም የህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው አገራችን በምታካሂደው የለውጥ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር እንዲቆም ለማስተማር አገልግሎቱ ወሳኝ ነው። ዛሬ ህዝቡ ከምንግዜውም በላይ በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበት በቅርበት ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህን እውነታ በማንሳት ዛሬም እምነቱን በማጠናከር ለውጡን የሚጻረሩ አካላትን መታገል እንዳለበት አብረውት እየኖሩ፣ እየበሉና እየጠጡ ማስተማር ትክከለኛው የመልዕክት ማስረጫ መንገድ ይመስለኛል።

ህዝቡ የሰላሙ መሰረት መሆኑን ለማስተማር አገልግሎቱ ወሳኝ ድርሻ አለው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው ለውጥን የመቃወም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው ህብረተሰቡን መሆኑን ለመንገር ከመገናኛ ብዙሃን ይልቅ ፊት ለፊት የሚደረግ ውይይት ጠቃሚ ይመስለኛል። ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ አብሮ በመኖር መንገር ትክክለኛው መንገድ ነው።

ያለ ሰላም የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እንደማይቻል ለማስረዳት፣ በማወቅ ይሁን ባለማወቅ በተሳሳተ አቅጣጫ የሚጓዝ ዜጋ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ እንዳይሆን ለመንገርና አንዱ ህዝብ የሌላውን ህዝብ ሰላም ጭምር እንዲጠብቅ ለማስተማር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ጉልህ ሚና ሊጫዉ ይችላሉ። ስለሆነም ክልሎች ይህን ሁኔታ በመጠቀም ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልሎች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያወጡትን ገንዘብ እንዲቀንሱም ያደርጋቸዋል። ይህን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ አገልግሎቱን መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይሀም በአገር ደረጃ ቁጠባውን በመደገፍ ክልሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ያደርጋቸዋል።

ስለሆነም የለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት “ወጣቶች በክረምት ወቅት ነፃ አገልግሎትን በመስጠት ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” በማለት እንደተናገሩት፣ ክልሎችም ከዚህ ትክክለኛ ምልከታ በመነሳት ለአገልግሎቱ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የአገልግሎቱ ተሳታፊዎች ለሚያከናውኑት ስራ መንግስት የሚያወጣውን ገንዘብ ስለሚያድን ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዩች ላይም ማዋል ይቻላል። ለአብነት ያህል ወጣቶች በህብረተሰቡ የጤና ችግር፣ አካባቢን በመጠበቅና የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ። ስልሳ ቀናትን እንኳን እየተዋወሩ ማህበረሰቡን በማገልገል ከሰሩ፣ በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ። ይህን እውነታ በመገንዘብም በሁሉም ክልሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።