ትኩረት ያልተሰጠው ሀብታችን

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ሀብት የታደለች አገር ናት። የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እድሜም ከዘጠና በላይ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ 58 ሚሊየን የሚደርስ ከብቶች አላት። በዚህ ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ስምንተኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች። ከሚሊየን በላይ በሚደርሱ በጎች ደግሞ በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም አሥረኛ ደረጃ ላይ ነች። በ29 ነጥብ 7 ሚሊየን የፍየል ሀብቷም በተመሳሳይ በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም አሥረኛ ደረጃ ላይ ናት። በየዓመቱ ወደ ቆዳ ማልፊያና ማለስለሻ ፋብሪካዎች ከሚቀርቡት ቆዳ እና ሌጦ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የከብቶች፣ 20 ሚሊየን የፍየሎች፣ 13 ነጥብ 2 ሚሊየን የበጎች ነው፡፡

ካለው ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ነው፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአገሪቱን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪዎች ልማትና ሽግግርን በማፋጠን ኢንዱስትሪዎቹ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ፈጣን ልማት እንዲያስመዘግቡ ማብቃትን ዓላማ አድርጐ የተቋቋመ የምርምር ተቋም ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ የቆዳ ኢንዱስትሪውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋ እና የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ልማት ዘርፍን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ፣ የቴክኒክ፣ የግብይት፣ የሥራ አመራርና ሌሎች እንደ አስፈላጊነቱ የሚያግዙ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ የምርምርና ሥርፀት፣ የምክርና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የቆዳ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም  የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ በዓላት አከባበር ከእርድ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጥብቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ  ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለሥጋው እንጂ ለቆዳው አይደለም፡፡ በ2011 በጀት ዓመት ከ133 ሚሊዮን ካሬ ጫማ ቆዳና ሌጦ በማልፋትና በማለስለስ ያለቀለት ቆዳን ማምረት የሚችሉ ከ32 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች ቢኖሩም ለፋብሪካዎቹ የሚቀርቡት ቆዳና ሌጦዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። ከፍተኛ የጥራት ችግርም አለባቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አገራችን ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከዘርፉ በማግኘት ላይ አይደለችም፡፡ ይህም በተለይ በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ በሚፈጠር ሰው ሠራሽ ችግር የተነሳ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት በእርድ ወቅትና በኋላ እና  በቆዳ ሰብሳቢዎችና ነጋዴዎች መወሰድ የሚገቡ ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ ጉድለት በቶሎ የመበላሸት ባህሪ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የእንስሳት እርድ የሚፈጽሙ አካላት ቆዳ በቢላዋ ሳይበሳ፣ ሳይቀደድ እና ሳይተፈተፍ ያለምንም ሰው ሠራሽ እንከን መግፈፍ፣ በእርድ ወቅት አንገት ከተቆረጠ ወይም ከተባረከ በኋላ እንስሳውን መሬት ላይ አለመጎተት፣ ዘመናዊ ቄራዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በእንስሳት እርድ በቂ ልምድና ሙያ ባላቸው ሰዎች እርድ ማካሄድ፣ ከቆዳው መወገድ ያለባቸውን እንደ ኮቴ፣ ጆሮ እና የመሳሰሉትን ማስወገድ፣ ሥጋን እና አጥንትን በቆዳው ላይ አለመከትከት፣ በተቻለ ፍጥነት በአቅራቢያ ለሚገኙ ቆዳ ሰብሳቢዎች በሽያጭ ማቅረብ፣ በየአካባቢው ቆዳና ሌጦ የሚሰበስቡ ነጋዴዎች የተረከቡትን ቆዳና ሌጦ በጨው በማጀል በጥንቃቄ መያዝ፣ ጨው ማግኘት ካልተቻለ ቆዳ እንዳይበሰብስ ዘረጋግቶ አየር እንዲያገኝ በማድረግ ለቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ወይም ለፋብሪካዎች በሽያጭ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጨው ያልተቀባን ቆዳ የቆዳውን 40 በመቶ ክብደት በሚመዝን ንፁህ ጨው በአግባቡ ሁሉንም የቆዳ ክፍል መቀባት፣ ጨው የተቀባውን ቆዳ መደርደሪያ በርብራብ መልክ ከመሬት ከፍ ያለ ሆኖ እንዲዘጋጅ በማድረግ ከቆዳው የሚወጣውን ደምና ፈሳሽ የሚንጠፈጠፍበት ክፍተት ማዘጋጀት፣ ጨው የተቀባውን ቆዳ የውስጠኛው /የሥጋውን ክፍል በማገናኘት ቀዝቃዛና ነፋሻማ መጋዘን ውስጥ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ጨው የተቀባውን ቆዳ በመደርደሪያው ላይ በደንቡ መሠረት ሲቀመጥ የድርድሩ ከፍታ አንድ ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

ቆዳና ሌጦን በማልፋትና በማለስለስ ከመጫሚያዎች፣ ከቆዳ ዕቃዎችና አልባሣት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ከሚውሉ ጓንቶች በተጨማሪ የመኪና ወንበርና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት ጥቅም ላይ ስለሚውል በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ስለሆነ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የሚከናወን ንግድ ለአገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከጥሬ ቆዳና ሌጦ ንግድ ጀምሮ እስከ ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ሂደት በርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንዲያገኙ ስለሚያስችል ጠቀሜታውን ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል፡፡

በመሆኑም ቆዳና ኢንዱስትሪ ካለው ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ኅብረተሰቡ ለቆዳ የሚያደርገው ጥንቃቄ ከእንስሳት እርባታ እስከ አለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ግብይት ድረስ ባሉት የግብይት ሰንሰለቶች፣ ቆዳና ሌጦ እንዳይባክን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡

ያለንበት ወቅት የአዲስ ዓመት መባቻ እንደመሆኑ በርካታ እርድ ይከናወንበታል፡፡ እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች በዚሁ በዓል ወቅት የታረዱ ከብቶች ቆዳና ሌጦ የሽያጭ ዋጋ ወርዶ እንደ አልባሌ ዕቃ በየቦታውና በቆሻሻ መጣያ ገንዳዎች ሲጣሉ ለመታዘብ ችለናል፡፡ ትኩረት ያልተሰጠው ሐብታችን ያልነውም ለዚሁ ነው ፡፡

የቆዳ ፋብሪካዎችና የሚመለከታቸው አካላት ለዚህ ችግር በጊዜ እልባት የሚሰጡበትን መንገድ ቢያመቻቹ መልካም ነው፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የሚከበረው የመስቀል በዓልና የሠርግና ምላሽ ባህላዊ ዝግጅቶችም ብዙ እርድ የሚፈፀምባቸው ናቸው፡፡ በተለይም በደቡብ ኢትዮዽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቢያንስ ለአንድ ሣምንት የሚያስቆይ የበዓልና የጋብቻ ዝግጅቶች ስላሉ የውጪ ምንዛሪ የሚያመነጨውን ቆዳና ሌጦ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንረባረብበት፡፡