የተሳካ የዲፕሎማሲ ድል!

በአሁን ወቅት አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይዘውት በመጡት “የመደመር” ፍልስፍና ሀገሪቷ በለውጥ መስመር ላይ ትገኛለች። በለውጡም አይነኬ የሚመስሉ ጉዳዮች ተነክተዋል። እንደ ሰማይ እርቀው ይታዩን የነበሩ ነገሮችም  ቅርብ ሆነው ታይተዋል። በመሆኑም በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ጀምሯል። ከተመዘገቡ ለውጦች መካከልም በዋነኝነት የሚጠቀሱ የዲፕሎማሲ ስኬቶች  ይገኙበታል።

በአገራዊ መግባባት መርህ ላይ የተመሰረተው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር አገራዊ መግባባት ለምሥራቅ አፍሪካም መረጋጋት መሆኑን በማመን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በሀገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ታሰረው የነበሩ ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈተዋል። በውጭ አገር ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲ ፓርቲዎችና ምሁራን “በመደመር” እሳቤ ይቅርታን በማስቀደም ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ ለመስራት ወደ አገር ቤት ገብተዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በስልጣን ዘመናቸው በዲፕሎማሲው ዘርፍ አሳካቸዋለሁ  ያሏቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህም መካከል በቀዳሚነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የጥላቻ ግንብ ማፍረስ ነው። በመሆኑም በአሁን  ወቅት ሀገራቱ በይቅርታ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር የጋራ ሰላማቸውንና ተጠቃሚነትታቸውን በማስጠበቅ ምጣኔ ሀብታዊ  ትስስራቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድ ሥር ሰዶ የኖረውን የሰላም እጦት እና ያለመረጋጋት ችግር ለዘለቄታው ለመፍታትና በመልካም ጉርብትና እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ቀጠናዊ ውህደትን መፍጠር ተችሏል። ኢትዮጵያና ኤርትራም ካሳለፉት ክፉ ቀን በላይ ዛሬ ያስመዘገቡት የዲፕሎማሲ ስኬት የህዝቡን እንባ አብሶ ትልቅ ድል አቀዳጅቷል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተጀመረው ጠንካራ ግንኙነት ወንድማማች የሆኑት የሁለቱም አገራት ህዝቦች ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከዚህም ባለፈ በቀጠናው ሠላምና መረጋጋት ሰፍኗል። ከቀጠናው ሰላም ባለፈም የኢትዮ ኤርትራ ሠላም በአፍሪካ ቀንድ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ አልፏል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለምስራቅ አፍሪካ እያበረከተች ያለችው የሰላም አስተዋጽኦ በዲፕሎማሲው ዘርፍ እጅግ የተሳካ ነው። በመሆኑም ከጎረቤት አገራት ጋር ጤናማ ግንኙነትና መልካም ጉርብትናን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ቀጠናዊ ውህደት መፍጠር ችላለች።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የሠላም ስምምነትን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሠላም አየር እንዲነፍስ የላቀ ሚና ተጫውታለች። በዋናነት ከኤርትራ ጋር የነበረባትን ውስጣዊ ችግር ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ መፍታት ችላለች። በተጨማሪም በጅቡቲ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ጋር በመስራት ሁለቱ አገራት እንዲግባቡ በማድረግ  የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርታለች።

በቅርቡ በቻይና መንግሥትና በአፍሪካ ሀገራት መካከል በነበረው የትብብር ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መገኘታቸው ሌላው የዲፕሎማሲ ስኬት ነው። የቻይና መንግሥት ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት ከአፍሪካ መንግስታት ጋር መስራት በሚያስችለው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱም የቻይና መንግስት ለአፍሪካ ሀገራት 60 ቢሊዮን ዶላር በብድር ለመስጠት ያቀደ መሆኑ ይታወቃል። ይህ 60 ቢሊዮን ዶላር ለኢንቨስትመንት ሥራና ለአቅም ግንባታ ስራ የሚውል መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና መንግሥት ሰፋ ያለ ብድር በመውሰድ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብድሩን በተሻለ አቅም በመጠቀም ውጤታማ መሆን ያስፈልጋልም ብለዋል። አያይዘውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ሚዛኑን የጠበቀና  ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂና ጠንካራ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በትብብር መድረኩ በ10 ዓመት ይከፈል የነበረው የአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር ብድር ወደ 30 ዓመት እንዲሸጋገርና የእፎይታ ጊዜውን ማስፋት ተችሏል። በተጨማሪም በሰው ሀይል ግንባታና በአንዳንድ ፕሮጀከቶች ላይ የሚደረገው የብድር ሁኔታን ማስተካከልና ዝርጋታውንም የማስፋፋት ሥራ በቀጣይ እንደሚሰራ በውይይቱ ተካቷል።

በውይይቱ የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ግንኙነት አጥብቆ በመቀጠል በሁሉም መስክ ውጤታማ መሆን እስከተቻለ ድረስ አጋርነቱን እንደሚቀጥል ገልጿል። በተለይም ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶችን በስፋት ወደ ቻይና እንዲገቡ ጥረት ይደረጋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ከሚያርፍባቸው ቦታዎች በተጨማሪ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ላይ መብረር እንዲችል በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የጠበቀ ግንኙነት የማጠናከር ሥራዎችን እንደሚሰሩ ተወያይተዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቻይና አፍሪካ ጉባኤን አጠናቀው አሰብና ምፅዋን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም መንገዶቹና ወደቦቹ ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል። ተጠናክሮ የቀጠለው ይህ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከሰላማቸው አልፎ ወደ ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ተሸጋግሯል። በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ ማዕድናትን ከኤርትራ ጭና መዳረሻዋን ቻይና ያደረገችው የኢትዮጵያ መርከብ ምፅዋ ደርሳ ስራ ጀምራለች። ይህም ሀገራቱ የተሰስማሙበትን የሰላም ጥረት ያረጋገጠ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ ቆይታቸው ከአፍሪካውያን መሪዎች ጋር ቀጠናዊ ውህደት ለመፍጠር የተጀመረውን ውይይት በማስቀጠል ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ሰላማዊ ቀጠናን በመፍጠር በአካባቢው ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለማፋጠን የሚያስችሉ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ከስምምነት  ላይ ደርሰዋል።

በአጠቃላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ቡድኖች መካከል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ፣ በኤርትራ እና በሶማልያ መካከል መቀራረብ ታይቷል። በዚህ መቀራረብም ሀገራቱ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የአሰብ ወደብን በመጠቀም ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚ ስትሆን ኤርትራም ከኢትዮጵያ መልማት ጋር ተጠቃሚ መሆን ጀምራለች። በዚህም ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተለይም ከኤርትራ ጋር በፈጠረችው ሠላም ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መቀዳጀት ችላለች።