ኢትዮጵያ ለውጥ ወይስ ነውጥ ላይ?

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት፣ የብዙ ባህሎችና ታሪክ ባለቤት፣ህዝቦቿ በታሪክና በባህል የተሳሰሩባት፣ አንዱ ብሄር ከሌላው የተዛመደባት፣የኔ ይበልጣል ያንተ ያንሳል ሳይባል አንዱ ያንዱን ባህልና ወግ አክብሮና ተከባብሮ በፍቅርና በመተሳሳብ  የሚኖሩባት ሀገር ነበረች።ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ነገሮችን ካስተዋልን ሀገሪቱ ወዴት እያመራች ነው የሚያስብል አንድምታ አለው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ሥልጣናቸው ከመጡበት ዕለት አንስቶ ለውጥ፣መደመር፣ይቅርታና የመሳሰሉትን ቃላቶችን መስማት ችለናል። በየሚዲያዎቹ እንዲሁም ለአንዳዶች የወሬአቸው ማጣፈጫ ሆኖ በየ ንግግሮች መሀል ላይ ጣል በማድረግ ለንግግራቸው መድመቂያም ሆነዋል።ነገር ግን እውነት የእነዚህን ቃላቶች ሚስጥር ያወቀ ያለ አይመስላኝም ምክንያቱም እውነት ብናውቀው አሁን በሀገራችን ላይ እያስተዋልናቸው ያሉ  ችግሮች ባላየን  ባልሰማን ነበር።መቼም የሚለውጥ ተገኝቶ መለወጥ የማይወድ፣ይቅርታ የሚል ኖሮ ይቅርታን የማይቀበል እንዲሁም የመደመር ሚስጥር ተገልፆለት መደመር አልሻም የሚል ትውልድን ባላየን ነበር።ሌላኛው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበትና ከሚዲያዎቻችን ላይ ሁሌም እየሰማናቸው ካሉት ቃላቶች መካከል አንዱ ለውጥ የሚላው ቃል ነው።እውነት ለውጥ ማለት ምን ማለት ነው? ማንስ ነው ማንን የሚለውጠው? ለውጡስ እንዴት ነው? ለውጡስ ከየት እስከየት ነው? እኚህና ሌሎችም ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልገናል።ምክንያቱም አሁን ላይ በሀገራችን እየተከናወኑ ያሉ ነገሮችን ስናይ ሳንወድ በግዳችን ይህ ጥያቄ በሁላችንም ልብ እንደሚፈጠር አያጠራጥርም።

አንዲት ሀገር ተለውጣለች ማለት የምንችለው መንግስትም ሆነ ህዝብ ለውጥ ለውጥ ስላለ ሳይሆን እርሱ እራሱ የለውጡ አካል መሆን ሲችል ነው።በአንድ ወቅት ማህተ መጋንዲ የተናገሩት ንግግር ታወሰኝ“እንዲለወጥ የምትፈልገው ነገር ካለ አንተ እራስህ የለውጡ አካል ሁን”እውነት ነው አንድ እንዲለወጥ የምንፈልገው ነገር ዳር ላይ ቆመን ለውጥ ለውጥ ስንል ብንውል መቼም ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ከንቱ ነገር ነው የሚሆነው።ስለዚህ አሁን ላይ መንግስትም ሆነ ህዝባችን በየሚዲያው ለውጥ እያሉ ያለው ነገር ማነው የሚለወጠው፣የሚለውጠውስ ማነው? ይህ ካልታወቀ ለውጡ ለውጥ ሳይሆን ነውጥ ይሆንብናል።ስለዚህ ሀገራችን ተለውጣና አድጋ እንድትታይ ከቃላት ያለፈ በስራ የሚታይ ተግባር  ከህዝብም ሆነ ከመንግስት በፍጥነት ሊመጣ ይገባል።ይህ ካሎነ ግን እውነት ይቺ  ሀገር መንግስት አላት ወይ ሊያስብሉ የሚችሉ ጥቄን ያስነሳል።

ሌላኛው  ማስተዋል  ያለብን  ነገር  ደግሞ  አሁን ላይ በሀገራችን እየተከናወነ ያለው ለውጥ ነው ካልን እውነት ለውጥ ትውልድን  እየጨረሰ ነው እንዴ? ህዝብ እርስ በእርስ መግባባት አቅቶት ይህ የኔ ስፍራ ነው አንተ መጤ ነክ ውጣልኝ እያለ፣ በፍቅርና በመተሳሰብ አብሮ የኖረ ህዝብ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ በልጦበት ውጣልኝ  እያለ ወገን በወገኑ ላይ ጦር መዞ እየተነሳ፣ ከመደመር ይልቅ መቀነስን መርጦ፣ ከይቅርታ ይልቅ  ቂም  እየቋጠርን፣ የኔ ወገን እኮ እዛ ክልል ተጎድቷል ተሰዶዋል  እኔም  የእርሱን ልጉዳ እያለ በወግ በባህልና በዝምድና የተሳሰሩ ህዝቦች አሁን ላይ ሁሉን ትተው በጥላቻ ማዕበል እየዋኙ ይገኛሉ።እና በዚህ ጊዜ ሀገሪቱን የሚመራ ማነው የሚያስብልም ጥቄን ማንሳቱ አይቀርም ስለዚህ ሁላችንም  የቱ ብሄር ከየት ተፈናቀለ?  ቀጥሎስ የቱ ነው የሚፈናቀለው? እያልን በስጋት ከመኖር ይልቅ በፍቅርና በመተሳሰብ ይዘን የቆየነውን አብሮነታችንን አጥብቀን መያዝ ይገባናል።

ውድ አንባቢያን ሀገራችን እስከዛሬ በአለም ሀገራት የምትታወቀው ሉአላዊት ሀገር በመሆኗና ህዝቦቿ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ሀገር ነበረች ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሁሉ ቀርቶ አሁን በተፈናቃይ ህዝብ ብዛት አቻ ያለተገኘላት ሀገር ሆናለች።“ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለው ብሂል ከመንግስትም ሆነ ከህዝብ ልብ የተሰወረ ነገር  ይመስላኛል ምክንያቱም  አሁን  ላይ  እያስተዋልነው ያለነው ነገር  ነገሮች ከተፈጠሩ ብኋላ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር እያልን ያለነው እንጂ ቅድመ ዝግጅትም ሆነ ቅድመ ጥንቃቄን መውሰድ አልተለመደም ለዛም ነው አሁን ላይ በሀገራችን ሰምተው አይተነውም የማነውቀውን ነገር እያስተዋልን ያለነው። ስላዚህ ህዝብም ሆነ መንግስት መንቃት ያስፈልጋል እላለሁኝ ምክንያቱም ይህ በፍቅርና  በመተሳሰብ  አብሮ  የኖረን ህዝብ እርስበርስ እንዲተላለቅ እያደረገ ያለው አካል ማነው? ህዝቡስ ውስጡ ተቀምጦ የትላቻን መርዝ የሚረጨውን የትላቻ አባት የሆነውን አካል  ለይቶ ማወቅ ተስኖት ነው?ወይስ ተመችቶት ነው መጠቀሚያው እየሆነ ያለው? እነዚህን ጥቄዎች መመለስ ይገባናል።

አሁን አሁንማ የሀገራችን የሰላም ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ከመግባቱ የተነሳ በሀገራችን የሚከበሩ ሐይማኖታዊ በዓላቶቻችን እንኳን ሲከበሩ ስለ በዓሉ ሳይሆን የምንጨነቀው በሰላም መጠናቀቁን ሆኖዋል።ስለዚህ ሁላችንም ስለ ሀገራችን የሰላም ጉዳይ ላይ የበኩላችንን መወጣት ይገባናል።

ሌላኛው በጣም የሚገርመኝ ነገር ደግሞ የዚህ ሕገ ወጥ ገንዘብና የጦር መሳሪያዎች በየ እለቱ ከሀገር ሊወጡና ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ተያዙ የሚባለው ነገር ነው።ቆይ የእነዚህ ገንዘቦችና የጦር መሳሪያዎች ባለቤት ማነው? ምንጩስ ከየት ነው?ለሚለው ጥያቄ ማንም አጥጋቢ ምላሽ  ሲሰጥ አናስተውልም  ሃላፊነቱንም  የሚወስድ አካል አልተገኘለትም ሁሌም ብቻ ተገኘና በቁጥጥር ስር ዋለን ብቻ ነው የምንሰማው ሚዲያዎቻችንም ይህን ጉዳይ በጥልቀት ሲዘግቡት አናስተውልም መንግስትስ ምን እየሰራ ነው ያስብላል።መቼም በጣም ብዙ ጥያቄዎች በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ እንዳለ እሙን ነው ስለዚህ ከ11ኛው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ጉባኤ ብዙ ምላሾችን እንጠብቃለን።