በቀነሰ ትኩረት ዉስጥ የቀጠለዉ ድምፅ አልባዉ ገዳይ

ለዓመታት የበርካታ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈው፣ ልጆችን ያለወላጅ ያስቀረው እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከተለው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ አሁንም በጣም በቀነሰ ትኩረት ታግዞ ድምፅ አልባ ገዳይነቱ ቀጥሏል። ባለፈው ዓመት የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በሀገር ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት 1.18 በመቶ ደርሷል።

 

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ከአንድ በመቶ በላይ ከሆነ በአንድ ሃገር ውስጥ ወረርሽኝ ተከስቷል ማለት ይቻላል። በ1978 ዓ.ም በሁለት ሰዎች ደም ውስጥ ብቻ ይገኝ የነበረው ቫይረስ ዛሬ ላይ ከ700ሺ በላይ ዜጎች ደም ውስጥ እንደሚገኝ የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤች አይ.ቪ.ኤድስ ወረርሽኝ ቀንሷል በሚል በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረዉ መዘናጋት በሽታው በድብቅ እንዲስፋፋ አስችሎታል።

በ2009 ዓ.ም ብቻ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ27ሺ በላይ ነው፤ ይላል የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ያወጣዉ መረጃ። የቫይረሱ ስርጭት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፤ የስርጭት መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የሚለው መረጃው በተጨማሪም ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው ቦታዎች፣ አዲስ በሚመሰረቱ ከተሞች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የስርጭት መጠኑ እያደገ ነው ተብሏል።

በገጠር አካባቢ የሚኖሩና በአበባ እርሻ ሥራ ላይ ተቀጥረው ከሚሰሩ ሴቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ-ሥጋ ግንኙነት በመፈፀማቸው ፅንስ ለማቋረጥ ተዳርገዋል፤ ይላል  የጽህፈት ቤቱ ሪፓርት። ለቫይረሱ ተጋላጭነት የፆታ፣ የሥራ አይነት እና የኑሮ ደረጃ አስተዋፅኦ አንደሚያደርጉም ያወሳል። በሴቶች ላይ የሚከሰተዉ የኢኮኖሚ እና ህብረተሰቡ የሚያደርስባቸው ጫና ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸውና ሴተኛ አዳሪዎች ለቫይረስ ተጋላጭነታቸው መጨመሩንም እንዲሁ። ጫት ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች እና ማሳጅ ቤቶች ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር አስተዋፅኦ ማበርከታቸዉንም የዘርፉ ባለሙያዎችም ይገልጻሉ፡፡

ሃገሪቷ በ2030 የኤች.አይ.ቪ ቫይረስን ስርጭት ለመግታት እቅድ የያዘች ቢሆንም ባለው የስርጭት መጠን የእቅዱ መሳካት አጠራጣሪ እንደሚሆንም ባለሙያዎቹ ያብራራሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባከናወኗቸው ተግባራት በቫይረሱ ምክንያት ይከሰት የነበረን ሞት በ70 በመቶ መቀነስ ተችሎ እንደነበር የተገለፀ ቢሆንም በዚህ ስኬት ምክንያትም መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ህበረተሰቡ በአጠቃላይ ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ ይሰጡ የነበረውን ትኩረት ቀንሰዉ ቆይተዋል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስን ስርጭት ለመቀነስ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ የተመዘገበውን ስኬት ከግምት ውስጥ አስገብተው ሃገሪቷ በሽታውን በራሷ አቅም መቆጣጠር ትችላለች በማለት ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ማቆማቸዉን ነው የፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የሚያመለክተው። ጽህፈት ቤቱ መንግሥት በመደበው በጀት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ ተግባራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ በሌላ በኩል በዓለማችን በአሁኑ ወቅት 36.7 ሚሊዮን ሰዎች ከኤች አይ ቪ ጋር እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት ጸረ-ኤድስ ድርጅት ሠነድ ይገልጻል። እስከ ባለፈው ታህሳስ ወር ድረስ ለአንድ ዓመት በተደረገው ክትትል ደግሞ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው ሆነው ተመዝግበዋል።

እንደ አዉሮፓዉያኑ አቆጣጠር በ2015 ብቻ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ1.1 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከኤድስ ጋር በተያያዘ ህመም ሞተዋል። ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በዓለማችን ይበልጥ የተስፋፋው በአፍሪካ እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። በየቀኑ ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ ከሚገኝበት የዓለማችን ነዋሪ መካከል ከግማሽ በላይ ማለትም 66 ከመቶ ያህሉ የሚገኘው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ሃገራት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚቀጥሉት 14 ዓመታት ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መዛመትን ለማስቆም አቅዷል። ሆኖም የተሐዋሲውን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ዘመቻዎች መቀዛቀዝ እና የገንዘብ ልገሳው መቀነስ የዕቅዱ መሳካት ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል። የመንግሥታቱ ድርጅት ጸረ-ኤድስ  ዳይሬክተር ሚሼል ሲዲቤ ዕቅዱ እንደ በ2030 ስለመሳካቱ ስጋታቸውን ከዚህ በፊት መግለፃቸው ይታወሳል። አሁን በያዝነው አሠራር የምንቀጥል ከሆነ የኤድስ መዛመትን በ2030 ዓመት ማስቆም አንችልም ሲሉም ገልጸው ነበር።

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ዉስጥ 25.6 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ኤች.አይ.ቪ በደሙ ዉስጥ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። ቀደም ሲል ሰዎች ከበሽታዉ ራሳቸዉን እንዲከላከሉ የተደረጉ ጥረቶች በተሐዋሲዉ የሚያዙትንም ሆነ የሞቱትን ቁጥር ለመቀነስ እንዳስቻለ ሲነገር ቆይቷል።

በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የኤች አይ ቪ ኤዲስ ቀን አስምልክቶ ለሚዲያዎች መግለጫውን የሰጠው የፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ቤት ዘንድሮ አገሪቱ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኤች አይቪ ኤድስን ሥርጭት ለመከላከል  አስፈጻሚ አካላትና ህብረተሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን  እየተወጡ  ባለመሆኑ  የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ሥርጭት አሳሳቢ  ደረጃ ደርሷል ብለዋል።