የሰኔ 15ቷ ምሽት

የሰኔ 15ቷ ምሽት     

ከሰሞኑ በአማራ ክልል በተደረገ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ሁለት የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ተሰውተዋል፡፡
ሰኔ 15/2011 አመሻሽ ላይ በተደረገው በዚህ ክስተት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ ተሰውተዋል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው የአዴፓ ስራ አስፈፈሚ ኮሚቴ አባላት በርዕሰ መስተዳድር ቢሮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር።

የክልሉ የሰላም፣ ፀጥታና ደህንነነት ቢሮ ሃላፊ በነበሩት ብ/ር ጄነራል አሳምነው ጽጌ አስተባባሪነት በተከናወነው በዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ዶ/ር አምባቸው እና አቶ እዘዝ በተተኮሰባቸው ጥይት ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ አቶ ምግባሩ ግን በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከሁለት ቀናት በኋላ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

ክስተቱን የፌደራል መንግስት፤ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን፤ አብዛኞቹን  የድርጊቱ ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር ማዋልም ጀምሯል፡፡

የድርጊቱ ዋነኛ ተጠርጣሪ የሆኑት ብ/ር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ በባህርዳር ወጣ ብላ በምትገኘውና ዘንዘልማ በሚባል አካባቢ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል ተብሏል፡፡

በዚሁ በሰኔ 15/2011 አመሻሽ በአዲስ አበባ ከተማ የኢፌደሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና በጄነራል ሰዓረ ቤት የነበሩ ጡረተኛው ሜ/ጄነራል ገዛኢ አበራ በጄኔራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት ውስጥ በግል ጠባቂያቸው ተገድለዋል፡፡ ይህኛው ግድያም ከባህርዳሩ ግድያዎች ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም ተብሏል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴ እና አቶ ምግባሩ ከበደ የቀብር ስነ ስርዓት ሰኔ 19 /2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

በተመሳሳይም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጄር ጄኔራል ገዛኢ አበራ የቀብር ስነ ስርዓት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመቐለ ከተማ ተፈጽሟል፡፡

በእነዚህ የሃገሪቱ ከፍተኛ የጦር እና የሲቪል አመራሮች ላይ የደረሰው ድንገተኛ ጥቃት የመላው ኢትዮጵያዊያንን ልብ የሰበረ ነበር፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በባህር ዳርና አዲስ አበባ በግፍ የተገደሉትን ከፍተኛ አመራሮች በተመለከተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ  የሀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

በሃዘን መግለጫቸውም እነዚህ ሰማዕታት እንደ አለት የፀኑ፣እንደ አልማዝ የጠነከሩ፣ ሀገራቸውን ከምንም በላይ የማገልገል ዓላማ ያነገቡ ፣ዓላማቸው ሳይሳካ አንገታቸውን ላለማዞር የቆረጡ፣ይህንንም በተግባር ያረጋገጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደ ነበሩ አስታውሰዋል።

ከዚያ በላይ ልብን የሚያደማው እነዚህ ሰማዕታት የለውጡ የምስራች ገብቷቸው፣ የሚገኘው ሀገራዊ ዋጋ ተረድተው ሌሎቻችን ሁሉ እነርሱ ወደታያቸው ራዕይ ሊወስዱን አቅም የነበራቸው ቀደሞ የለውጡ ተላሚዎች መሆናቸውን ስናስብ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ነገሩ ከምንገምተው ጊዜ የቀደመ፣ ከምናስበው ውጭ ልብ የሚያደማ ሆነብን እንጂ ሀገርን አንድ ማድረግ ፣ህዝብን በሰላምና በዴሞክራሲ ጎዳና መወሰድ ከባድ መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ ተረድተነው ነበር ያሉት ዶ/ር አብይ  ትግሉ ከሰውነት በታች ከወረዱ፣ ከስልጣን ውጭ ሌላ ከማይታያቸው፣ ከመግደል ውጭ ሌላ ዕውቀት ካልዞረባቸው፣ ከጉልበት ሌላ መፍትሔ ያለ ከማይመስላቸው ፣ከግል ጥቅም ባሻገር ለማየት ከማይችሉ ጋር እንደሚደረግ ተረድተነው ነበር ብለዋል።

ከዴሞክራሲ ህዝብ ያተርፋል፤ እነሱ ግን ይከስራ፤ ከስልጣኔ ህዝብ ይጠቀማል፤ እነሱ ግን ይጎዳ፤ ከህብረ ብሄራዊነት ሀገር ይበለፅጋል፤ እነርሱ ግን ይደኸያሉ፤ በፍቅር በይቅርታ ኢትዮጵያ ትታከማለች፤ እነርሱ ግን ይታመማሉ፡፡ ይህ ነው የጠላቶቻችን ትልቅ መለያቸው ብለዋል ዶክተር አብይ ።

ዓላማቸው ሶሰት ነገሮችን ማስከተል መሆኑ ወለል ብሎ ይታያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአንድ በኩል የለውጡን ሐዋሪያት በመግደል ለውጡን ማስቆም፣ በሌላ በኩል ህዝባችንን በተሳሳተ ምሰል በርሱ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ማድረግ፣ በሶስተኛ ደረጃም የፀጥታ አካሎቻችንን ሞራልና ክብር በመንካትና አንድነቱን በጎጥ በመከፋፈል ሀገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነበር። ግን አልተሳካም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አምላክ ለቅዠታቸውና ለእኩይ ተግባራቸው አሳልፎ አልሰጠንም። ወደፊትም አይሰጠንም በማለት ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

እነዚያን ጀግኖች እንዲህ በቀላሉ ማጣት እንደ እግር እሳት ይለበልባል፣ እንደ ጎን ውጋት ያስቃስታል ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እነርሱን ለማግኘት ስንት ደክማለች፣ ስንት ተስላለች፣ ስንት ወጥታ ወርዳለች፤ ይህን በማይረዱ የገዛ ልጆቿ ልጆቿን አጥታለች። በሀገር እየኖሩ፣ በሀገር እየከበሩ ሀገር በማይገባቸው የልጅ ደመኞች ውድ ልጆቿን ተቀምታለች ብለዋል።

ያን መሰል ሀገርን የካደ ሰንካላ ክፉ ምኞት ሲጀመርም የከሸፈና የተሸነፈ አስተሳሰብ በመሆኑ ሕዝባችን በተለመደ ሀገር ወዳድነትና በፅኑ የአርበኝነት መንፈስ በእንጭጩ አምክኖታል።

በሃገሩ እና በወገኖቹ ጥቃት የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአባቶቹ እንደለመደው ከሀገሩ ልጆች እና ከጀግኖቹ ጋር በአንድነት በመቆም ክፉውን ሴራ አክሽፎታልልም ብለዋል።

በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ፖለቲከኞቻችን በአብሮነትና በፅናት በመቆም ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሬ ወርቅ ተፈትኖ እንደ ጥሩ ወርቅ ነጥሮ እንደሚወጣ ዳግም ለዓለም አረጋግጠዋል። ክልሎች በጋራ በመቆም በትብብር በመደጋገፍ የመኖርን ፋይዳ አልቀው አሳይትዋል ብለዋል።

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የፖሊስ ሀይላችን እና የፀጥታ አካሎቻችን እዝና ተዋረዳቸውን በላቀ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ጠብቀው ተልዕኳቸውን በከፍተኛ ደረጃ በመወጣት አኩሪ ገድል በመፈፀም ዛሬም እንደ ትናንቱ እንድንኮራና እንድንመካባቸው ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መግደል መሸነፍ ነው ስንል የሀሳብ እና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሉአላዊ ሀሳብ እንጂ በጥይት እንደማይሸነፍ በመረዳታችን ነበር፤ መግደል መሸነፍ ነው::  እንደ እነርሱ የፀብ ብረት መወልወል እና ባሩድ መቀመም ስለማንችልበት አይደለም ነው ያሉት።

ታላቁ ጀግንነት ፍቅር እና ይቅርታ፣ እርቅና ሰላም ስለሆነ እንጂ መግደል እና መገዳደል፤ ጦርነትና ግጭት ምን አይነት መቀመቅ ውስጥ ሀገረን እንደሚከት ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚረዳው የለም ብለን ስለምናምን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃዘን መግለጫቸው።

ከመግደል ከመጨፍጨፍ፣ ከማሰርና ከማሳደድ የተለየ መንገድ እንከተል ብለን ወሰንን። ዝግ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር አሰፋን፤ ክፍትና አካታች በማድረግ፥ አቃፊና ደጋፊነቱን ለማረጋገጥ ጥረት አደረግን። የወኅኒ ቢሮቻችን ተከፍተው አእላፍ እስረኞች የነፃነት አየር ተነፈሱ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኃይል፣ ጉልበትና ጭካኔ ለፈጻሚው ቀላል ነው፤ ለሚፈጸምበት ግን ያማል ብለዋል። ትእግስት፣ ሆደ ሰፊነትና ሁሉን ቻይነት ደግሞ ከማንም በላይ አድራጊውን ያመዋል፤ እኛም የመረጥነው ሁለተኛውን ነበር በማለት ነበር ድርጊቱን የገለጹት።ትእግስትና ሆደ ሰፊነታችን ብዙ ትችትና ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ጫናም እንድናስተናግድ አደርጎ ነበርም ብለዋል።

አዲስ መንገድ አዲስ ፈተና ያመጣል፤ በምክንያት የማይመሩት የስልጣን ጥመኞች ይህ ስለማይገባቸው በጀብደኛና እብሪተኛ እርምጃ የጥፋት ሰይፋቸውን በጠራራ ፀሀይ፣ በአደባባይ መዘው የደማቅ ጌጦቻችንን ውድና ክብር ህይወት ቀጥፏል ብለዋል።

የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲስቱን የተስፋ አድማስ፣ የአፍሪካ ፈርጥና ተምሳሌት ማድረግ እንጂ ኢትዮጵያን የሀዘን ማቅ ማልበስ አይደለም ነበር ያሉት።

ሀገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር እስከተረዳን ድረስ እየመረረንም ቢሆን የምንቀበለው ሀሳብ ይኖራል፤ በሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዘላቂ ጥቅምና ክብር ላይ ግን ድርድርም ሆነ ትእግስት ፈፅሞ አይኖረንም፤ከኢትዮጵያ የሚበልጥ፣ ከህዝብ የሚቀድም ምንም ነገር የለም፤ ለዴሞክራሲና ለሰላም ስንል እንታገሳለን፤ ለሀገርና ለህዝብ ስንል ደግሞ መራር ውሳኔ እንወስናለን ብለዋል።

እያለቀስን ብንቀጥል የጓዶቻችንን ዓላማ አናሳካም፤ ተስፋ ብንቆርጥ የጓዶቻችንን ሰንደቅ ከፍ አናደርገውም። ለምን እንዲህ ሆነ? ድክመታችን ምን ነበር? ምን ማድረግ ነበረብን? የሚሉትን በትክክልኛ ጥናት እንለያለን በማለት ወደ ፊትን ተልመዋል።

ካጋጠሙን ፈተናዎች እንማራለን፤ እንዳይደገም አደርገን የህገ ወጥነትን ቢሮዎችን እንዘጋለን፤ ለአፍታም ከጉዟችን አንገታም፤ ከዓላማችን አንዛነፍም መንገዳችንንም አንቀይርም በማለት ጽኑ አቋማቸውን በመግለጫቸው አስቀምጠዋል።

የአገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ድርጊቱ በተፈጸመበት ወቅት በስራ ምክንያት በውጭ ሀገር እንደነበሩና ወደ አቀኑበት ሀገር ከመድረሳቸው ያስተናገዱት የስልክ ጥሪ ለማመን የሚከብድ ነበር በማለት ሀዘናቸው ጥልቅ መሆኑን ገልጸዋል። ህይወታቸውን ያጡ አመራሮችን ወደ ውጭ ከመውጣታቸው ከሰዓታት በፊት ከሶስቱም ጋር በተከታታይ ስለመጪው ስራዎቻቸው ሊሰሯቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች  ምክረ-ሀሳቦቻችንን በስልክ ተወያይተን ነበር በማለት በባህርዳሩ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአስከሬን ሽኝት ወቅት ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሰሞኑ በባህርዳር የተከሰተው ድርጊት የህዝቡን ታሪክ የማይመጥንና ያለፍነውን የመጠፋፋት ባህል ዳግም ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ሁሉም በነቂስ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል በማለት ድርጊቱን አውግዘዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አስከሬን ሽኝት ባደረጉት ንግግር፤ ሲቃ እየተናነቃቸው ከሰሞኑ በባህርዳር የተከሰተው ጥቃት በህይወትና ማህበራዊ ገጽታው ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦች ለትግል አጋሮቻቸው እጅግ የሚከብድ ነው ብለውታል።

ድርጊቱ የህዝቡን ታሪክ የማይመጥን በጭካኔ የታጀበ አረመኔያዊ ድርጊት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሃገሪቷ ከስልጣንና ጋር በተያያዘ የነበሩ የመጠፋፋት ባህሎች ዳግም ወደ ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ሁሉም በነቂስ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ ዓላማ ተጋምደው፣ በአመራር ቋንቋ ተላምደው፣ በጓዳዊ አስተሳሰብ ተራምደው፤ በሙሉ ተስፋ የተሰለፉትን የቁርጥ ቀን ልጆች በእንዲህ ዓይነት ጭካኔ ማጣት ለሁሉም የላቀው ፈተናና ጸጸት ነው ብለዋል።

በመሆኑም መንግስትና መሪ ድርጅቱ ከህዝብ ጋር በመሆን ድርጊቱን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን፤ የተሰውትን ጀግኖች ዓላማና በዘመን የማያልፍ አበርክቶቻቸውን ዳር እንዲደርስ ሁላቸንም በጽናት መጓዝ፣ መራመድና ማሳካት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

በአገርና በክልል የተያዘውን የለውጥ አጀንዳ አጠናክሮ ለመቀጠል ዋነኛ ስራም የህግ የበላይነት በማስከበር ሰላምን በመገንባትና የኢኮኖሚ ማነቆዎቸን በመፍታት ልማቱን ማፋጠን ይገባል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ነገር ግን እኝህ ወሳኝ ስራዎችና ሌሎች አጀንዳዎችን ለመፈጸም ብዙ እድሎች እያሉ፤በተግባር ከእድሎቻችን እየራቅን የችግሮቻችነን እድድሜ እያራዘምን እንገኛለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ከስሜታዊነት፤ ከጀብደኛነት፤ ከግለኝነትና ራስን ብቻ ከማዳመጥ ወጥተን ወደ ከፍታ የሚወስዱንን ጥበቦች መከተል ማለትም ምክንያታዊነትን፤ በሌላው ጫማ ላይ ሆኖ ማሰብን ህግና ሰርዓትን ማክበርን አርቆ ተመልካችነትን መላበስ ይኖርብናል ብለዋል።

የአማራ ክልል ህዝብም ከዚህ አኳያ ታሪኩን የሚመጥን ምህዋር ላይ በመሳፈር በውስጡ አቃፊነቱን በመላው ዓለም ላይ ተከባብሮ ሰፍቶና ሞልቶ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ከዚህ ውጪ የሚራመዱ ሃሳቦችና አስተምሮዎች ህዝባችንን ከከፍታው የሚያወርዱት መሆኑን አውቆ በጥንቃቄ ሊያቸውና ሊመክታቸው ይገባልም ነው ያሉት።

በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስና እንዳይከሰት በሂደትም በቁጥጥር ስር እንዲውል ላደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የጸጥታ አካላትና የመንግስት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፤ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህግና ስርዓት እንዲነግስ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በህይወት ያጣናቸው ወንድሞቻችን፤ ጀግኖቹ! ለቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ጊዜ ሳይሰጡ፤ ስለመጪው ሀይወታቸው ሳያስቡ፤ በተለያዩ አጀንዳ ውስጥ ሆነው በድንገት ወድቀዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሟች ልጆቻቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ተስፋ ከቶውንም ቢሆን ሊጨልም አይገባውም ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ፣ መንግስትና የለወጥ አጋሮች ከጎናችሁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ለሀገር አቀፍና ለክልል አቀፍ ተልዕኮዎች መሳካት ከልጅነታቸው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ሲሰሩ የነበሩ የመከላከያ የጦር መኮንኖች ህልፈትና በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸው ላለፈው የድርጅታቸው ከፍተኛ አመራሮች ህልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

በሰኔ 15ቱ አመሻሽ ጥቃት የሁሉም ክልሎች መንግስታትና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድሮች ድርጊቱን በተለያዩ ሚዲያዎች አውግዘውታል። ድርጊቱን ካወገዙት መካከል የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካል ድርጉቱ በአገሪቷ ላይ የተቃጣ ከፍተኛ ወንጀል ነው ብለውታል። መንግስትን የማንበርከክ ሙራም ነው ብለውታል።

ድርጊቱን የፈጸሙትም ስልጣንን በህገ-መንግስቱ መሰረት መያዝ እንደማይችሉ ያረጋገጡ በባህርዳር በፈጸሙት ወንጀል አይተናል በማለት የድርጊቱን ኢ-ህገመንግስታዊነት ተናግረዋል። በዚህ ድርጊት የተሳተፉ፣ ከኋላም ያስተባበበሩ ፍርድ እንዲያገኙ እንጠይቃለንም ብለዋል ዶ/ር ደብረጽዮን። በድርጊቱ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችን መላው የዐማራ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተው፤የጀመርነውን የፌደራል ስርዓቱ ተጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ የትክራይ ክልል መንግስት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው።  

በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ተጠርጣሪነት በአማራ ክልል ከተፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ጥቃት ያደረሱ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።

ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ በባህርዳር ዘንዘልማ በሚባል አካባቢ በጸጥታ ሃይሎች በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ሰኔ 19/2011 በላሊበላ ከተማ በቤተጊወርጊስ የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈጽሟል።

የፀጥታ ሃይሉም ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል እየተሰራ ሲሆን፤ ህብረተቡም አንድነቱን በማጠናከር አካባቢውን ከምንጊዜውም በላይ ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።