ከሰሞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲጎበኙ እድል ተመቻችቶላቸው ነበር። በጉብኝቱ ከ29 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተን የፕሮጀክቱን የስራ እንቅስቃሴ ያለበት ደረጃ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ኤፍረም ወ/ኪዳንም ለመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያዎቹ በመጀመሪያ ግድቡ የሚገኝበትን ደረጃ ገለጻ ካደረጉ በኋላ፤ የግድቡን የተለያዩ የግንባታ ሂደቶች ባሉበት ደረጃ አስጎብኝተዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍረም ወ/ኪዳን ገለጻ መሰረት፤ የግድቡ ግንባታ ከዚህ ቀደም የጥልቅ ሸለቆ መፈጠር፤ የሀይድሮሊክና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች የዲዛይን እንዲሁም የተጣበበ የኮንትራት ጊዜ ችግር አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም አሁን ላይ በጥናት በመመስረትና ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ በመፍታት የግድቡ ግንባታ ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ የመገናኛ ብዙሃኑ የግድቡን አሁናዊ ደረጃ ተዘዋውረው በካሜራቸው እንዲያስቀሩ ፈቅደዋል።
ኢንጂነሩ ለሚዲያ ባለሙያዎች ባደረጉት ማብራሪያ መሰረት የግድቡ የሲቪል ስራ አፈጻጸም ችግሮች ካማጋጠማቸው በፊትም፤ አሁንም በመልካም የግንባታ ሂደት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ነገር ግን የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታ ብረት ስራዎች የተለያዩ የጥራት መጓደልና የመዘግየት ችግር ገጥሞት ቆይቷል በማለት አስረድተዋል። ምክትል ስራ አስኪያጁ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮችን፣ ችግሮቹ እየተፈቱበት ያለውን ሂደትና የችግሮቹን መጠን፤ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ሂደት አሁን ላይ ያለበትን ደረጃ ለመገናኛ ብዙሃኑ አብራርተዋል።
በኢንጂነሩ ማብራሪና እኛም በስፍራው ተገኝተን እንዳረጋገጥነው፤ በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውል ተይዞባቸው ይሰሩ የነበሩት የኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታብረት ስራዎች እንዲሁም የደን ምንጣሮ ስራዎች ላይ የጥራት ጉድለትና የመዘግየት ችግር በማጋጠሙ በአገሪቱ ሃብት ላይ ከባድ ኪሳራ፤ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ደግሞ መዘግየትን አስከትሏል። ይህም ከልጅ እስከ አዋቂ በነቂስ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን ሲያደርግ የነበረውን ህዝብ ቅስም የሰበረ እንደነበረ የቅርብ ትዝታ ሆኖ አልፏል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት አጋጥመው የነበሩ ችግሮች ተፈትተው አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ ያለማቋረጥ እየተከናወነ መሆኑ የተገለጸልን ቢሆንም፤ አጋጥመው የነበሩ ችግሮችም ለመገናኛ ሚዲያ ባለሙያዎቹ ይፋ ተደርገዋል። ለመገናኛ ብዙሃኑ በተደረገው ማብራሪያ የገዘፈው ችግር የተከሰተው በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውል ተይዞባቸው ግንባታቸው ሲከናወኑ የነበሩት የኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታ ብረት እንዲሁም የደን ምንጣሮ ስራዎች ናቸው።
ካጋጠሙት ችግሮች መካከልም በግድቡ ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ጥልቅ ሸለቆ በማጋጠሙ፤ግድቡ ለሶስት ዓመታት ተገፍቷል። የኮንትራት ማሻሻያ በመደረጉ በሃይድሮ መካኒካልና የግድቡ የብረታብረት ዲዛይን ስራዎች ላይ መዘግየት ማስከተሉን ኢንጂነር ኤፍሬም አንስተዋል። ኢንጂነሩ አክለውም እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት ለዚያውም ዝርዝር ዲዛይን ሳይዘጋጅለት በአራት ዓመት ይጠናቀቃል ብሎ ማስቀመጥ ቀድሞውንም ትክክል እንዳልነበር ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የሜይቴክ ኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታ ብረት ስራዎች ዘግይተዋል። የተሰሩት ስራዎችም የጥራት ክፍተት ያጋጠማቸው በመሆኑ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ባጋጠሙት ችግሮች የደረሰው ጉዳት መጠን በገንዘብ ምን ያህል እንደሆነና የደረሰው ኪሳራ ምን ያህል እንደሆነ ጥያቄ ቢያቀርቡላቸውም፤ ምክትል ስራ አስኪያጁ የችግሩን መጠንና ኪሳራ በገንዘብ ስሌት ለመግለጽ አልደፈሩም።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድም በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር መንግስት ለሳሊኒ ኮንስትራክሽን ከ300 ሚሊየን ዩሮ በላይ ካሳ ተጠይቆ ከ125 ሚሊየን ዩሮ በላይ ካሳ በድርድር መክፈሉን መናገራቸው፤ የደረሰውን ኪሳራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ይህ ም በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተይዘው የነበሩ ስራዎች በመዘግየታቸውና በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ላይ መዘግየት በመፍጠራቸው የተከፈለ ዋጋ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በህዳሴው ግድብ ግባታ የተደረገው ማሻሻያ የባለፈውን ድካም የሚያሻሽል ውጤት ይጠበቅበታል በማለት መንግስት አጋጥሞት የነበረውን ችግር በማለፍ ሂደት ላይ መሆኑን ማረጋገጣቸውም አይዘነጋም።
በግድቡ ስፍራ ተገኝተን ባደረግነው ምልከታም መንግስት በአሁኑ ወቅት አጋጥመውት የነበሩ ችግሮቹን በጥናት በመፍታት የግድቡ ግንባታዎች ያለማቋረጥ እየተካሄደ ነው። አሁን ላይ ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የነበረው ውል ተቋርጦ፤ ኮርፖሬሽኑ እንደ ንዑስ ተቋራጭ በእቃ አቅራቢነት ያሰራቸው የነበሩ አምስት ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች ጋር ሙሉ የኮንትራት ውል በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም መሰረት አምስት ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የኤሌክትሮ መካኒካል እና ሃይድሮ መካኒካል ስራውን እንዲያከናውኑ በተሻሻለው አዲስ ውል ቅድመ ክፍያ ተፈጽሞላቸው በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በቅድሚያ ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ የተባሉት የዩኒት ዘጠኝ እና አስር የሃይል ማመንጫ የሃይል ማመንጫዎች የውሃ ማስተላለፊያ የምርት ሂደትና የማስተካከያ ስራዎች ሲጂጂሲ በሚባለው የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመሰራት ላይ ይገኛል።የቀሪዎቹ የሃይል ማመንጫ ዩኒቶች የምርት ሂደት ሲኒ ሃይድሮ ፍራንስ በሚባለው የፈረንሳይ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ በመሰራት ላይ ይገኛል። በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰራው የግድቡ የግርጌ ማስተንፈሻ እንደገ ተነቅሎ የማስተካከያ ስራዎቹ በሲጂጂሲው ተቋራጭ በመሰራት ላይ ይገኛል። በአብዛኛው በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰሩት ስራዎች የጥራት ጉድለት ያጋጠማቸው በመሆኑ የተሰሩትን በማስወገድና በመንቀል እንደገና የማስተካከል ስራዎች በአዲሶቹ ተቋራጮች እየተካሄደ መሆኑን አስተውለናል።
በተለይም ከዚህ ቀደም በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰራው የግድቡ የግርጌ የውሃ ማስተንፈሻ (ቦቶም አውትሌት) የብረታ ብረት ስራውን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ እየተቀየረ ሲሆን፤ የማስተካከያ ስራው እየተሰራ መሆኑን ለባለሙያዎች ተገልጿል። በአጠቃላይ የግድቡ የብረታ ብረት ስራ (የሀይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር) አፈጻጸም ገና 2.65 በመቶ መሆኑ ብቻ ነው። የግድቡ አጠቃላይ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች አፈጻጸም ቢሆንም ከ28.79 በመቶ አልዘለለም። ይህ ከዚህ ቀደም በነበረው ተቋራጭ መዘግየት ጋር የተፈጠረ ችግር በመኖሩ የተከሰተ መሆኑ የተገለጸልን ሲሆን፤ አሁን ግን ችግሮቹን በመፍታት በሙሉ አቅም ወደ ስራ መገባቱ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ተገልጿል።
በግድቡ ግንባታ ጥሩ አፈጻጸም የሚስተዋለው በሲቪል ስራው ነው። ይህ ማለት የዋና ግድቡን ግንባታ ጨምሮ የኮርቻ ግድቡንና የግድቡን የሃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታን ይመለከታል። ስራውን የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ አሁንም ይኸው የኮንስትራክሽን ድርጅት ስራውን እንዲቀጥል ተደርጓል።
የዋና ግድቡ ግንባታ 145 ሜትር ከፍታና 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 80.12 በመቶ ተጠናቋል። ከዋናው ግድብ ግርጌ በቀኝና በግራ በኩል ሁለት የሃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፤ የቀኝ ሃይል ማመንጫ ቤት 63.76፤ የግራ ሃይል ማመንጫ ቤት ደግሞ 74.82 በመቶ መጠናቀቁ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል። በግራ ሃይል ማመንጫ ቤት የሚገኙት ሁለት የሃይል ማመንጫ እ.ኤ.አ 2020 ታህሳስ ወር ውስጥ ሃይል ማመንጨት እንዲችሉ ታቅዶ ግንባታቸው በመፋጠን ላይ መሆናቸውን ለእይታ ክፍት ተደርገውልን ተመልክተና። እነዚህ ሁለቱ ዩኒት ዘጠኝ እና ዩኒት 10 የሃይል ማመንጫዎችም ሲጠናቀቁ ግድቡ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቀው የውሃ መጠን ልክ በመጀመሪያ 260 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሲሆን፤ በቀጣይም እንደ ግድቡ የውሃ ከፍታ መጠን የሚያመነጩት የኤሌክትሪክ ሃይል እስከ 750 ሜጋ ዋት የሚደርስ ይሆናል ተብሏል።
ከግድቡ በታች ለሚለቀቀው ውሃ የሚያገለግለው ከዋናው ግድብ በስተግራ በኩል መዝጊያ ያለው የጎርፍ ማስተንፈሻ (ጌትድ ስፒልወይ) 96.03 በመቶ ተጠናቋል። እንዲሁም ግድቡ የታቀደለትን ውሃ መያዝ እንዲችል እና የውሃውን ፍሰት ወደ ዋናው ግድብ እንዲሆን የሚያደርገው የግድቡ ክፍል የኮርቻ ቅርጽ ያለውና የኮቻ ግድብ በሚል የሚጠሩት (ሳድል ዳም) 95.24 በመቶ ተጠናቋል።የስዊችያርድ የሲቪል ስራዎች 66.69 በመቶ መጠናቀቁ ተገልጾልናል።
በአጠቃለይ በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ እየተሰራ ያለው የሲቪል ስራ በመገባደድ ላይ ያለ መሆኑና በተቋራጩ እየተገነባ ያለው አጠቃላይ የሲቪል ስራም 84 በመቶ ደርሷል።
በአጠቃለይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አሁን ላይ የሲቪል ስራ 84 በመቶ፤ የኤሌክትሮ መካኒካል 28.79 በመቶ እና የብረታብረት ስራው ገና 2.65 በመቶ መሆኑን ተመልክተናል። ይህም ማለት የፕሮጀክቱ ግንባታ አሁን ላይ በአማካይ 67.97 በመቶ መሆኑን የፕሮጀክቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ በጉብኝቱ ላይ ለተገኘነው የሚዲያ ባለሙያዎች ገለጻ አድርገውልናል።
ሌላው በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተቋራጭነት የተሰራው የደን ምንጣሮ ነበር። በአጠቃላይ 123ሺ 189 ሄክታር ይመነጠራል። ከዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በብረታብረትና ኢንጂነሪን ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች ልኬት መሰረት 39ሺ 155 ሄክታር መሬት መመንጠሩ ሪፖርት ተደርጎ እንደነበር እንጂነሩ አስታውሰዋል። ይህም በአጠቃላይ የሚመጠረውን 31 በመቶ አፈፃፀም እንዳለው ግምት ተወሰዶ ነበር ብለዋል።ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ጂኦስፓሽያል ኢንፎርሜሽን ኤጀነሲ ባለሙያዎች ልኬት መሰረት 32ሺ 734 ሄክታር ማለትም 26.57 በመቶው መመንጠሩ ነው የተረጋገጠው። የታየው የአራት በመቶ ልዩነት በኢንቨስተሮችና ለአርሻ የተመነጠሩትን ቅናሽ በማድረጉ ነውም ተብሏል።
በዚያም ሆነ በዚህ የተመነጠረው መሬት እንደገና ምንጣሮ የሚፈልግ መሆኑ ተገልጾልናል። ይህም ሌላው በአገር ላይ የደረሰ ኪሳራ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በከፍተኛ ወጪ የደን ምንጣሮ የተካሄደበት አካባቢም የተመነጠሩት ዛፎች እንደገና አድገው ያስተዋልንበት ሁኔታ ነበር። ይህ ማለት ዳግም ምንጣሮና ሌላ ወጪ የሚያስከትል መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን አሁን ላይ ችግሮቹን በማለፍ የግድቡ ግንባታ ያለማቋረጥ እየተሰራ መሆኑን አስተውለናል። ይልቁንም በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጾልናል። ነገር ግን የህዝብ ተሳትፎው ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት መቀዛቀዝ ተስተውሎበታል። በመሆኑም ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙም ለግድቡ ግንበታ ህያው መሆን ችግሮችን በማለፍ አሁንም ህዝቡ ድጋፍን እንዲያደርግ ተጠይቋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ አብርሃም እንደሚሉት፤ ጉብኝቱ ከግድቡ ጋር ተያይዞ በህዝብ ዘንድ የተፈጠረዉን ብዥታ ሚድያዎች በአካል ተገኝተዉ ከተመለከቱ በኋላ እንዲያጠሩ ነዉ ብለዋል፡፡
የህዝብ ተሳትፎና ድጋፍ መቀዛቀዝ ቢያሳይም አሁንም ድጋፉ ያልተቋረጠ መሆኑን ገልፀዉ፣ በዘንድሮ ዓመት አስር ወራት ብቻ ከ860 ሚልየን ብር በላይ የህዝብ ድጋፍ መደረጉን አስታዉቀዋል፡፡ በአይነትም የህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር አሁን ላይ ያለውን የአገሪቷን 4269 ሜጋ ዋት አቅም ወደ 10ሺ 200 ሜጋ ዋት ከፍ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።በአካባቢው በ1680 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ 44 ሜትር ጥልቀትና 74 ቢሊዩን ኪቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሰራሽ ሃይ ስለሚፈጠር አዲስ የዓሳ ልማት ዕድልም ይፈጥራል ተብሎ በባለሙያዎች ተነግሯል። ይህ ማለት በተፈጥሮአዊ መንገድ ብቻ በዓመት ከ5000-10000 ቶን ዓሳ ማምረት ይቻላል። ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ሊሆን እንደሚችልና ለአካባቢው ማህበረሰብም ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ማሰብ አይከብድም።
በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ግድቡ ከሚያመነጨው ግዙፍነት የተነሳ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ተርፎ ለጎረቤትና ለሌሎች ሀገራት በሽያጭ የሚተላለፍ በመሆኑ ከተለያዩ ሀገራት ጋር እየተፈጠረ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረያጃ ሸጋግረዋልም። የሀይል አቅርቦትን ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ግድቡ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉትና ለታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጉልህ ጉዳት የማያስከትል መሆኑም ተገልጿል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ሚናው ከዚህም የዘለለ ነው።
በአባይ ዘመናትን የዘለቁት ቁጭቶች የሚቋጩበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎችን በስፍራው አስተውለናል። እርግጥ ነው የባከነው የአገር ሃብትና ጊዜ ባልተገባ ነበር። የሆነው ሁሉ ሆኖ በግንበታ ሂደቱ መሰል ችግሮች እንዳያጋጥሙ የመንግስት ክትትልና ቁጥጥሩ መጠናከር ይኖርባቸዋል። አሁን ላይ ያጋጠመው ችግር በአብዛኛው የተፈቱ ሲሆን፤ የግንባታ ሂደቱ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጾልናል። በህዝቡ ዘንድ ብዥታ መፈጠሩ እና የድጋፍና ተሳትፎው መቀዛቀዝ ተፈጥረው ከነበሩት ችግሮች አንጻር ለምን ሆነ የማይባል ቢሆንም፤ አሁን ላይ በግድቡ ግንባታ ሂደት ዙሪያ ግልጽነት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት መቀጠል ይገባዋል። የህዝቡም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።