በፈረንጆቹ 2021 የሳይበር ወንጀለኞች ፊታቸውን ወደ “ራንሰምዌር” ጥቃት በስፋት እንደሚያዞሩ ተነገረ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጸሙ ግዙፍ የሚባሉ የሳይበር ጥቃቶች ትኩረታቸው እንደቀድሞዉ የደንበኞችን ሚስጥራዊ መረጃዎች መበርበር ላይ አንደማይሆን የማንነት ስርቆት የመረጃ ማዕከል (Identity Theft Resource Center) ገለፀ፡፡

ከዚህ ይልቅ የመረጃ መንታፊዎች ፊታቸውን ወደ ፊሺንግ (Phising) እና ራንሰምዌር (Ransomeware) የተሰኘ ጥቃት እንደሚያዞሩ የግል እና የመንግስት ተቋማት ላይ ሊቃጡ በሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች የሚደርስ የወንጀል ተፅዕኖን ለመቀነስ የተቋቋመው የማንነት ስርቆት የመረጃ ማዕከል ይፋ ማደረጉን የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የሳይበር ወንጀለኞች ከዚህ በፊት የግል መረጃ ስርቆት ላይ የነበረውን ትኩረታቸውን በመቀየር የሳይበር ጥቃቶችን ለመፈጸም “ደካማ የሸማች ባህሪያት” ላይ በማድረግ የይለፍ-ቃሎቻቸውን  ወደ መጠቀም ፊታቸውን እንዳዞሩ ተጠቁሟል፡፡

ወንጀለኞቹ የተቋማትን ኔትወርክ ጥሰው ለመግባት ወይም የቢዝነስ ኢ-ሜይሎችን ለመመንተፍ የሎግኢን (logins) እና የይለፍ-ቃል ላይ ትኩረታቸውን እንዳደረጉ ማዕከሉ ገልጿል፡፡

እነዚህ ጥቃቶች አነስተኛ ጥረት የሚጠይቁ፣ በአብዛኛው አውቶማቲክ የሆኑ፣ የመያዝ አደጋቸው አነስተኛ የሆነ እና የግለሰቦችን አካውንት በመመዝበር ከሚገኘው ገቢ አንጻርም እጅግ የላቁ መሆናቸውን ማዕከሉ አሳውቋል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 ይከሰታሉ ተብለው ከሚጠበቁ የግለሰባዊ “የፊሺንግ ጥቃቶች” ባሻገር የኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ የማንነት ማጭበርበሮች እንደሚቀጥሉም የማንነት ስርቆት የመረጃ ማዕከል ጨምሮ ገልጿል፡፡

ራንሰምዌር የቫይረስ ዓይነት ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ሥርዓት ወይም ግላዊ ፋይል እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ እና መረጃዎቻቸውን መልሰው ለማግኘት ክፍያ የሚጠይቅ የጥቃት ዓይነት ነው፡፡

የፊሺንግ ጥቃት ደግሞ ጥቃት ፈጻሚዎች የሚታወቅን ተቋምም ሆነ ግለሰብ ስምና ዝናን በመጠቀም በኢ-ሜይል መልዕክቶችን በመላክ ወይም በሌላ የግንኙነት ዘዴ በመጠቀም አንድን ግለሰብ ወይም ድርጅት ለጉዳት የሚዳርግ የማጭበርበር ዓይነት መሆኑን ከኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡