“የባዶ እግር ትሩፋቶች” በሚል አትሌቶች ሊዘከሩ ነው

የሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ ዓመት የሮም ኦሊምፒክ ድልን መነሻ በማድረግ አትሌቶችን የሚዘክር “የባዶ እግር ትሩፋቶች” የሚል መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ፌዴሬሸኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከታህሳስ 3 እስከ 5 ቀን 2013 ዓ.ም  የሚያከናውናቸውን መርሃ ግብሮች ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ መርሐ ግብሩ  በበቂ ሁኔታ ያልተዳሰሰውን የጀግኖች አትሌቶች ታሪክ የሚዘከር መሆኑን ገልፀዋል።

በመርሃ ግብሩ ከሜልቦርን እስከ ሪዮዲጄኔሮ ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ በመወከል አገር ያኮሩ ጀግኖች አትሌቶች፣ የልዑካን ቡድን አባላት እና ሌሎች አካላት ሽልማትና ምስጋና እንደሚቀርብላቸው አስታውቀዋል።

በሻምበል አበበ ቢቂላ፣ በሻምበል ማሞ ወልዴ እና በሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ስም የተዘጋጀ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወንም አቶ ቢልልኝ ጠቁመዋል።

በሻምበል አበበ ቢቂላ ስም የተሰየመና ለሴት አትሌቶችና አሰልጣኞች የሚሰጥ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል መርሐ ግብርም ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ያከናወናቸወ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመርሃ ግብሩ እንደሚጎበኙ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።