አፍሪካ በመጪው መጋቢት የኮቪድ-19 ክትባትን በዘመቻ ማዳረስ ልትጀምር ነው

 

አፍሪካ በመጪው መጋቢት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባትን በስፋት ልታዳርስ መሆኑ ተገለጸ።

የክትባቱ ዋጋ መናር፣ በኢኮኖሚ የበለጸጉ  ሃገራት ያለራሳቸው ብቻ ለመጠቀም ያሳዩት ፍላጎት  እንዲሁም የክትባት ማሰራጫ መሰረተ ልማቶች አለመኖር አፍሪካን ወደ ኋላ እንዳስቀራት  በተለያዩ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

የአለም ጤና ድርጅት ለዘርፉ ተዋናዮች ባደረገው ጥሪ መሰረት አፍሪካ ክትባቱን በፍጥነት ልታገኝ የምትችልበት መንገድ እየተፈለገ መሆኑም ተገልጿል።

አህጉሪቱ ሶስት ነጥብ 4 ሚሊዮን የቫይረሱ ተጠቂዎች፣ 2 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች  ያሉባት እንዲሁም 83 ሺህ የተጠጉ   ሰዎች ህይወት ማለፉን  የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያና ማእከል ገልጿል።

የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ሃገራት በተናጠል በሚያደርጉት እሽቅድምድምና የክትባት ዋጋ ንረት  አፍሪካ  ተነጥላ ኋላ እየቀረች መሆኑን አሳውቋል።

ጊኒ ድህነት ከተጫናቸው ሃገሮች የመጀመሪያዋ በመሆኗ ካሏት ዜጎች ውስጥ ለሃያ አምስቱ ብቻ ክትባቱን ስታቀርብ በአንጻሩ የተሻለ ገቢ ያላት ሲሼልስ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ቀድማ  የክትባት ዘመቻውን እንደጀመረች ተገልጿል።

በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሃገራት በሚያሳዩት ክትባቱን ለመውሰድ ባሳዩት እሽቅድምድም ምክንያት  ዘግይታ ክትባቱን የምትረከበው አፍሪካ በርካታ ድርጅቶችን ባካተተው አለም አቀፉ የክትባት ትብብር ማእቀፍ አማካይነት 9 መቶ ሚሊዮን የሚሆኑ ክትባቶችን እንደምታገኝ አረጋግጣለች ተብሏል ።

ዘመቻውን ለማስጀመር የሚሆን ክትባት በሚቀጥለው መጋቢት ወር በሰላሳ ሚሊዮን ክትባቶች ይፋ የሚደረግ መሆኑን ዘገባው አስረድቷል።

አለማቀፉ የክትባት ትብብር እስከ ፈረንጆቹ 2021 ማጠናቀቂያ ድረስ ሃያ በመቶ ለሚሆኑ አፍሪካውያን ክትባቱን ለማዳረስ እየሰራና በተጠቀሰው አመትም ሶስት መቶ ሚሊዮን አፍሪካውያን ሁለት ጊዜ ይከተባሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።