ለሕክምና ባለሙያዎች ስፔሻሊቲ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል የብቃት ምዘና ፈተና እየተሰጠ ነው

ለሕክምና ባለሙያዎች ስፔሻሊቲ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል የብቃት ምዘና በመላ ሀገሪቱ እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

4 ሺህ 800 ለሚሆኑ የመጀመሪያ ዲግሪ የሕክምና ባለሙያዎች በ22 ማእከላት ፈተና በዛሬው ዕለት እየተሰጠ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሰው ሀብት ልማት ሜዲካል ትምህርት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ቴኒ ገልጸዋል።

ፈተናውን በብቃት የሚያልፉ 1 ሺህ ሐኪሞች በ22 የሕክምና የትምህርት መስኮች በ16 የሕክምና ተቋማት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል ብለዋል።

የስፔሻሊቲ ሥልጠናው የሰው ኃይል በሚፈለግባቸው የትምህርት መስኮች የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሻሻል ከሚተገብራቸው ፕሮግራሞች አንዱ መሆኑንና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትንም ማሟላት እንደሚያስችል መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።