ሰላም ከማን ይጀምር?

ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ የሰላም ቁልፉ የሚገኘው በእያንዳንዳችን እጅ ላይ ነው። የሰላም ምንጮችና አደፍራሾች እያንዳንዳችን ነን፡፡ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ሰላም ለመጠበቅ እያንዳንዱ ሰው ለሠላም ያለው ቁርጠኝነት የሁሉም ነገር መነሻ ሊሆን ይገባል።

ሰላም ከግጭት ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን ማለት ሳይሆን በማንኛውም መልኩ ነፃ በሆነ መንገድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍ፣ በመወያየትና በመቻቻል በአንድነት መኖር መቻልና ችግሮች በሚፈቱበት ደረጃ ላይ ማድርስ መቻል ነው፡፡ የተሰራ አዕምሮ የፈረሰ ከተማን ይገነባል፤ ያልተሰራ አዕምሮ ደግሞ የተሰራ ከተማን ያፈርሳል እንደሚባለው ለሠላም የምንሰጠው ዋጋ ያለንን ለማቆየትና ሰርተን ለመበልጸግ ይረናዳል፡፡

ከአዲስ ዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉና በወጣቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማህበር መስራችና ባለቤት የሆኑት ወጣቶች የሰላም እጦት ሲከሰት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቀድሞ ተጠቂ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት መስራችና ፕሬዝዳንት ቢኒያም ጌታቸው የተለያዩ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች ይዘን ብንመጣ ያለ ሰላም ምንም ነው ይላል፡፡ ወጣቱ በስሜታዊነት ከመነዳት ይልቅ ቁጭ ብሎ በመነጋገር፣ በመመካከርና ሰከን ባለ መንገድ ወደ እርቅ መምጣት አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ለመጥፎ ዓላማ የሚማገዱበት ዋነኛ ምክንያት ዓላማና ራዕይ ሲያጡ መሆኑ ይነሳል። ታዲያ ዓላማ ያለውና አሻግሮ የሚመለከት ወጣት ማፍራት ለሀገር ግንባታ ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ይተያል የሚሉት ደግሞ አንድ ልብ ለትወልድ የህጻናት፣ ሴቶችና አረጋዊያን መርጃ ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ማራናታ ተክለሰንበት ናቸው፡፡

“አመጽና ችግር ውስጥ ያሉ ወጣቶችን አግኝተን ስንጠይቃቸው ምን እንደሆነ ሳያውቁ እንደገቡ ነው የሚናገሩት” እውቀቱም የላቸውም ያሉት ዳይሬክተሯ የሰላምን ዋጋ ከወጣቱ በላይ ማንም መረዳት የለበትም ወጣቱ ለሰላም ግንባታ የመጀመሪያውን ድርሻ መውሰድ እንዳለበትና ራዕይ ያላቸው ወጣቶች ሊበዙ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሰርቶ ለመግባት፣ ያቀድነውን ለማሳካት፣ ገበሬው የዘራነውን ለማጨድ፣ ወልዶ ለመሳም፣ ራስንም ሆነ አገርን ለመለወጥ የምንችለው ሰላም ሲኖር ነው። የሰላምን ዋጋ የምናውቀውና የምንረዳው ወጥቶ ለመግባት ፈታኝ ጊዜ ሲገጥመን ብቻ መሆን የለበትም።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት በተፈለገው ልክ የስራ እድል ፈጠራው ውጤታ እንዳይሆን እያደረገው መሆኑ ይገለጻል፡፡

ከአዲስ ዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉ በአማራ ክልል የስራና ክህሎት ቢሮ አማካሪ ድረሴ እሸቱ በክልሉ የተከሰተው የሠላም ዕጦት በወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል ያሉ ሲሆን በክልሉ ከታቀደው 1 ሚለዮን የስራ ዕድል ፈጠራ ማሳካት የተቻለው 50 በመቶውን ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ነስረዲን ቃዲ በበኩላቸው የሰላም እጦት የሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ እክል እንደጠረ ገልጸው ለእድገታችን ትልቁ ማነቆ እንዳንድ አከባቢዎች የተፈጠረው የሰላም እጦት ነው ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ሰላም ከሌለ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ የሰላም እጦት በሃይማኖት፣ በህክምናው፣ በንግዱ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በትምህርት፣ በስራ እና በሌሎች ተቋማት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

በመሆኑም ወጣቶች ብዙ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ያለባቸው ክህሎትና እውቀት የሚያገኙበት ቦታ ላይ መሆን አለበት፡፡ ይህም ሲሆን ሀገራቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ራሳቸውን መጥቀም ያስችላቸዋል፡፡ በስሜት ተነድቶ ጥፋት ከመፈጸም ይልቅ ነጻነታችንን በአግባቡ በመጠቀም እና ሌሎችንም በማስተማር ትውልዱ ኃላፊነት በመውሰድ በተግባር ማረጋገጥ አለበት።

ማህራዊ ሚዲያን ለበጎ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ ጥላቻን ለመዝራትና ሀሰተኛ መረጃዎች ለማሰራጨት የሚጠቀሙት በርካቶች ናቸው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓለማ ብቻ በመጠቀም ለሀገሩ ዕድገት ሊሠራ ይገባል፡፡ ከከፋፋይና መጥፎ እሳቤዎችን ከሚነዙ መረጃዎች ተጠንቅቆ ምክንያታዊ በመሆን ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባልና፡፡

ኢትዮጵያዊያን የምንታወቀው በአንድነት፣ በመተዛዘንና በመተጋገዝ መኖርን እንጂ ለበቀልና ለጸብ ጊዜ ስናጠፋ አይደለም። በመሆኑም የመተሳሰብና ያለንን የማካፈል እሴቶቻችን ማጠናከር ይገባናል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገራችን የጀመረችውን ብልጽግና ጉዞ ፈጥነን እናሳካለን፡፡

በየኔወርቅ መኮንን